Saturday, 15 August 2015 15:49

“…ላትደርስበት አልነግርህም!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

አንድ ቀልድ ትሁን እውነት ገና ያልለየላት ሚዲያ ላይ በተለያየ መልክ የምትቀርብ ነገር አለች፡፡ አንደኛው ምን ይላል…ሰውየው በእርጅና ምክንያት ከወደ ትከሻቸው ጎበጥ ብለው የሚሄዱት በዱላ እርዳታ ነው። እናላችሁ… አንድ ‘ጠጉር የሚያበቅልበት ቦታ የበዛበት’ ጎረምሳ ሊያሾፍባቸው ምን ይላቸዋል…
“አባባ ለምን ጎበጡ?”  ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም ምን ቢሉት ጥሩ ነው…
“ላትደርስበት አልነግርህም…” አሉት አሉ፡፡ እውነትም ትሁን ፊክሺን አባባሏ የምር አሪፍ ነገር ነች፡፡
እናማ… “ላትደርስበት አልነግርህም…” የምንልባቸው ነገሮች በዝተዋል፡፡
በዛ ሰሞን ሉካንዳ ነጋዴዎች ቤታቸውን ዘግተው ነበር አሉ፡፡ (የምር ግን ሀሳብ አለን…ዓለም ላይ ከሉካንዳ ቤት የተጀመረ ሬቮሉሽን የሚያውቅ ካለ ይንገረንማ!  ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ… የሥጋ ዋጋ እንዲሁ ጣራ እየነካ ከሄደ… አለ አይደል… ወደፊት ምን ይመስለኛል መሰላችሁ፡ በቁርጥ ቤት አጠገብ ስናልፍ በሦስት ጉንጭ የሚበላውን አንዱን…
“ወንድሜ የሥጋ ጣዕም ምን፣ ምን ይላል?” ስንለው…አለ አይደል…ምን የሚል ይመስለኛል መሰላችሁ…
“ላትቀምሰው አልነግርህም!”  ቂ…ቂ…ቂ…
ለምሳሌ በ‘ፈርኒቸር’ ቤት አጠገብ ስናልፍ አሪፍ… አለ አይደል… የአንድ ወረዳ በጀት የሚያወጣ ሶፋ እናይና…
“እዚህ ወንበር ላይ መቀመጥ ምን ስሜት ይሰጣል?” ብለን ስንጠይቅ ምን ይባል መሰላችሁ… “ላትቀመጥበት አልነግርህም!”
የምር ግን… “የምንቀመጥባቸው ወንበሮች በብዛትም በጥራትም እያነሱብን ሄዱ” ብለው የሚያማርሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብሎ ማሰብ አይከፋም፡፡ (እነ እንትና ‘የቃላት አብዶ’ ያላችሁኝ አነጋገር እንዴት ነበር?”  
ለምሳሌ አሪፍ እንትናዬ አለች፡፡ እንትናዬዋን እንደው ሌላ ነገር አይምሰልብኝና እሷዬዋ ላይ ‘‘ኪሶሎጆ’ ማጦፍ ምን ስሜት ይፈጥራል?”  ስትሉት ምን ይል መሰላችሁ…  
“ላትስማት አልነግርህም!” እሱን እንኳን ተወው! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…ዘንድሮ እኮ ሰዉ ሲደርስ እንጂ ሲሄድ አልታይ ብሎን ተቸግረናል፡፡ በሱፐርሶኒክ አውሮፓን ይሁን፣ በቀደም በፕሉቶ አጠገብ አለፈች የተባለችው መንኮራኩር ይሁን አይታወቅም …በመስከረም ‘እዛ ታች’ ያያችሁት ሰው በህዳር ‘አናት ላይ’ ወጥቶ ፊጥ!
እናማ… “ሰውየው እዛ ጫፍ እንዴት ወጣ?” ስትሉ  መልሱ…
“ወጥተሀ ላትደርስበት አልነግርህም?” ነው፡፡
እናማ… እኛም አሁን፣ አሁን ‘ከተሞክሮ’ ተምረናል፡፡ የማይሆን ጥያቄ ከመጠየቃችን በፊት ለራሳችን መልሱን እንሰጣለን፡፡ አለ አይደል… በአሪፍ ሆቴል አጠገብ ስናልፍ (የአሪፍ ሆቴል አበዛዙ!) “እዚህ ሆቴል ምሳ መብላት ምን ስሜት ይሰጥ ይሆን?” ልንል እናስብና ቶሎ ብለን… “ላልደርስበት አልጠይቅም…” ብለን እናቆማለን፡፡
ትናንት… “አንተ በቃ ፉል እንኳን አልጋብዝም አልክ!” ይል የነበረ ወዳጃችን ግድግዳ ላይ ያለውን ‘ካላንደር’ እንኳን ሳንለውጥ ደርሶ ላይ ፊጥ ሲል… አለ አይደል… “ምን ቢሠራ ነው እንዲህ ብር በብር የሆነው?” ብለን ልንጠይቅ እናስብና…
“ላልደርስበት አልጠይቅም…” ብለን ዝም፡ ጭጭ እንላለን፡፡
እግረ መንገዴን፣ ይቺን ስሙኝማ…በአንድ ወቅት ኮሚኒስት የነበረች አገር መሪ የማሻሻያ ፕሮግራም…
1. ሰዎችን ደስተኛና ሀብታም ማድረግ፡፡
    አባሪ
    ‘ደስተኛና ሀብታም የሚደረጉት ሰዎች ዝርዝር’
ይላል አሉ፡፡ አሪፍ ነው፡ ህዝቤ ቁርጡን ያውቃላ!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ… ባልና ሚስት ‘ኩሼ’ ብለዋል፡፡ (‘አራድነት’ እንዳይጠፋ ብዬ ነው፡፡) ሚስትየዋ የሆነ ህልም ታይና ደንግጣ ትነሳና ታማትባለች፡፡ ትንሽ ቆይቶ ማልቀስ ጀመረች። ባልም እያጽናናት…
“ምን ያስለቅስሻል?” ይላታል፡፡ እሷም ምን ትላለች…
“በህልሜ አንድ ቅልጥ ያለ ሀብታምና መልከ መልካም ወንድ ከአንተ ላይ ነጥቆ አግቶኝ ሲወስደኝ አየሁ፡፡”
ባልም “አይዞሽ፣ አታልቅሺ፡፡ ህልም ነው እኮ!” ይላታል፡፡    
ሚስት ምን ብትል ጥሩ ነው…
“እኔን ያስለቀሰኝ ታዲያ ህልም መሆኑ አይደለም!” ብላው እርፍ አለች፡፡
እንትናዬዎቻችሁ ሌሊት ቢያለቅሱባችሁ ህልሙ እውነት ስላልሆነ ይሆናል ብላችሁ ጠርጥሩማ፡፡
እኔ የምለው…እግረ መንገዴን… ‘የቼ መንፈስ’ ሉካንዳ ገባ እንዴ! (ቂ…ቂ…ቂ…) በቀደም ባለሉካንዳ ቤቶች ሱቆቻቸውን ዘግተው ነበር ምናምን ሲባል አልነበር! “አንደኛውን ክርችም ብለው ጉዳችን በታየ…” ስትል የነበርከው ወዳጃችን፣ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ “ከዚህ ቁረጥ፣ ከዚያ ቁረጥ... ስትል ታይተሀል የሚባለው ስምህን ሲያጠፉ ነው እንዴ!
የምር ግን…ከተማ ውስጥ እየተነዱ ሲሄዱ አንዳንዴ የሚቀውጡት ኮርማዎች… አሉ አይደል…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… “ሪቮሉሽን እያስነሱ ሊሆን ይችላል፣” እያልን ያላሰብነው አንዳንዴም ማሰብም ‘ትከሻችንን እየከበደን’ ስለቸገረን ነው። ልክ ነዋ…. “የሚቀርብህ ሰንሰለትህ ነው…” እንደሚባለው… አለ አይደል… ከብቶቹም…“የሚቀርብህ ቢላዋ ነው…” ብሎ ሹክ ያላቸው ሊኖር ይችላል፡፡
ዋናው ነገር…‘የሥጋ ቤት’ ነገር ለብዙዎቻችን… አለ አይደል… “ላትደርስበት አልነግርህም…” ወደሚባል ደረጃ እየደረስን ስለሆነ… “አይሞቀንም፣ አይበርደንም…” ለማለት ምንም አልቀረንም፡፡   
የምር ግን ከተማችን ውስጥ የሚከፈቱት ካፌና ሬስቱራንቶች ገና ከደጅ… “እዚሀ እገባለሁ ብለህ አስበህ እንዳይሆን…” የሚሉን ይመስለናል። ልክ ነዋ…በረንዳ ቁጭ ብሎ ከእግር እስከ ራስ የሚገመግም ‘ተገልጋይ’ የሞላበት ዘመን ነው፡፡ እናላችሁ... እኛ ከተገዛች አሥራ ምናምነኛ ሻማዋን የተኮሰች ‘አቅም ተኮር’ና እንደ ሰው ‘የምታስኮንን’ ጫማ አድርገን… አለ አይደል… ጸጉረ ልውጥነት የማይሰማንሳ!
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የተለመዱ ‘ደንበኞች’ የሚሞሏቸውና ስትገቡ የ‘መጤነት’ አይነት ስሜት እንዲያድርባችሁ የሚያደርጉ ቦታዎች አሉ፡፡ አሀ… የአሳላፊዎቹ ፈገግታ እንኳን እናንተ ዘንድ ሲደርስ የኃይል ማነስ ይገጥመዋል፡፡ ኮሚክ እኮ ነው…ቁም ነገር የሚያወራ የሚመስለውም፣ ሞባይሉን እያሽከረከረ አፍ አውጥቶ… “አይፎኔን አታዩልኝም እንዴ!” ሊል ምንም የማይቀረውም… በዓይናቸው ከእግር እስከ ራሳችሁ ‘ያበጥሯችኋል’፡፡
እናላችሁ… “…ላንደርስበት አንሞክረውም…” የሚያስብሉ መአት ነገሮች አሉ፡፡
እግረ መንገዴን…ይሄ የውጪ መስተንግዶ መስጠትን ሙሉ ለሙሉ ከከተማዋ መጥፋት የማን ‘ተሞክሮ’ ነው! ልክ ነዋ…በየፊልም እንደምናየው፣ እንደሚነገረንም የውጪ መስተንግዶ የዘመናዊ ከተማ ማሳያ ነው፡፡
እናላችሁ… “ላትደርስበት አልነግርህም…” ያሉት አዛውንት በምቁነት ሳይሆን የጎረምሳው የዓይን ቀለም ‘እንደማይደርስ’ ነግሯቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የምር ግን… የዓይን ቀለም ሁልጊዜም የሚታየው… አለ አይደል… ዓይኖች ላይ ብቻ እንዳልሆነ ልብ ይባልማ!
“…ላትደርስበት አልነግርህም…” ከመባል ያድነንማ!
“…ላልደርስበት አልሞክረውም…” ከማለትም ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2805 times