Saturday, 15 August 2015 16:00

የሰ/ ኮርያው ም/ ጠቅላይ ሚኒስትር በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ መገደላቸው ተነገረ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ፕሬዚዳንቱ ያስገደሏቸው ባለስልጣናት 70 ደርሰዋል ተብሏል
   አምና በሰኔ ወር ስልጣን ላይ የወጡት የሰሜን ኮርያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቾ ዮንግ ጎን በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን ትዕዛዝ ባለፈው ግንቦት ላይ እንደተገደሉ መነገሩንና ደቡብ ኮርያም ጉዳዩን እያጣራች እንደሆነ መግለጧን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ዮንሃፕ ኒውስ የተባለ የዜና ምንጭ የስለላ ተቋማትን መረጃ ዋቢ በማድረግ ባወጣው ዘገባ፣ የ63 አመቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን የምከተለውን የደን ልማት ፖሊሲ ተችተዋል በሚል አስገድለዋቸዋል፡፡
የግንባታና የግንባታ መሳሪያ ኢንዱስትሪዎች ምክትል ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉትና ወደ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ያደጉት ቾ ዮንግ ጎን ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ከህዝብ እይታም ተሰውረው መቆየታቸውና እሳቸውን በተመለከተ ምንም አይነት የዜና ሽፋን ተሰጥቶ አያውቅም ብሏል ዘገባው፡፡
ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን ስልጣን ከያዙ በኋላ በእሳቸው ትዕዛዝ የተገደሉና የገቡበት ጠፍቶ የቀሩ የሰሜን ኮርያ ባለስልጣናት ቁጥር 70 ያህል ደርሷል ያለው ዘገባው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቾ ዮንግ ጎንም የፕሬዚዳንቱን አስተዳደር በመተቸታቸው እንዲገደሉ ተደርገዋል የሚል ዘገባ መውጣቱን ገልጧል፡፡
የደቡብ ኮርያ ብሄራዊ አንድነት ኢንስቲቲዩት ባለፈው ወር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በሰሜን ኮርያ በ2012 ብቻ 21 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ኪም ጁንግ ኡን በ2013 የገዛ አጎታቸውን ማስገደላቸውንና በዚህ አመትም የመከላከያ ሚኒስትሩን ዮን ያንግ ቾልን በአሰቃቂ ሁኔታ በሞርታር ማስረሸናቸውን አስታውሷል፡፡

Read 2762 times