Saturday, 15 August 2015 16:07

በወፍ ጎጆ ኢትዮጵያን ምን ይጠብቃታል?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ክፍል አንድ
15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሳምንት በኋላ በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ይጀመራል፡፡ 29ኛው ኦሎምፒያድን ከ7 ዓመት በፊት በድምቀት ባስተናገደው  ታላቁ የወፍ ጎጆ ስታድዬም ለሁለት ሳምንታት የሚካሄድ ነው፡፡ የወፍ ጎጆ የተባለው ዘመናዊ ስታድዬም ኦሎምፒክን  ያስተናገደው እስከ 80ሺ ተመልካች በመያዝ ነበር፡፡ ለዓለም ሻምፒዮናው ተስማሚ የአየር ንብረት እንዲኖር ሲባል  54000 ተመልካች ብቻ እንዲያስተናግድ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ተወስኗል። ብዙዎቹ ውድድሮች በምሽት መካሄዳቸው የውድድሩን ድምቀት ይጨምረዋል ተብሏል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው በአጭር ርቀት አሜሪካና ጃማይካ፤ በረጅም ርቀት ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚያደርጉት ትንቅንቅ ይደምቃል፡፡
በተለያዩ የውድድር መደቦችን ሚኒማዎችን ያሟሉ፤ ከ2 ዓመት በፊት ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ የወሰዱ፤ የ2014 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች፤ የየአህጉሩ ሻምፒዮኖች መሳተፋቸው ሻምፒዮናው ያለበትን ከፍተኛ ደረጃ ያመለክታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የሚገኝ ስኬት ከዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ውጤታማነት አመልካች ሲሆን በየውድድር መደቡ ሻምፒዮን ሆነው የወርቅ ሜዳልያ የሚያገኙት የሪዮዲጄኔሮ ትኬታቸውን በቀጥታ የሚቆርጡበት ይሆናል፡፡
ከ200 አገራት በላይ እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው የዓለም ሻምፒዮናው በ47 የውድድር መደቦች (24 በወንድ እና 23 በሴት)  ከ2000 በላይ አትሌቶች ይወዳደራሉ። በየሻምፒዮናው አጠቃላይ የሜዳልያ ሰንጠረዡን በመሪነት የመቆጣጠር ልምድ ያላቸው አሜሪካ፤ ጃማይካና ራሽያ ሙሉ ቡድናቸውን ሰሞኑን አሳውቀዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ሞስኮ ባስተናገደችው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አሜሪካ 6፤ ጃማይካ 6፤ ኬንያ 5፤ ጀርመን 4 እንዲሁም ኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ከ1 እስከ 6 ያለውን ደረጃ ይዘው መጨረሳቸው ይታወሳል፡፡በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ1 እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት እንዲሁም ለሌሎች የቡድን ውድድሮች የገንዘብ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን የዓለም ሪከርድ ለሚያስመዘግብ አትሌቶች የ100ሺ ብር ቦነስ ተዘጋጅቷል፡፡ ለወርቅ ሜዳልያ 60 ሺ ዶላር፤ ለብር ሜዳልያ 30ሺ ዶላር፤ ለነሐስ ሜዳልያ 20ሺ ዶላር ሲበረከት፤ ከ4 እስከ 8 ደረጃ ለሚያገኙት 15ሺህ፤ 10ሺህ ፤6ሺህ፤ 5ሺ እና 4ሺ ዶላር እንደቅደመተከተላቸው ይሸለማል፡፡
የኢትዮጵያ ቡድን ኬንያ እና ሌሎች
ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን 33 አትሌቶች ያሉበትን ቡድን የምታሰልፈው ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታዎች ከአራት በላይ የወርቅ እንዲሁም በድምሩ እስከ 12 ሜዳልያዎች እንደምትሰበስብ ተገምቷል።  የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ካለፈው የዓለም ሻምፒዮና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚቻል ተስፋ ማድረጉን የገለፀ ሲሆን፤ ብሔራዊ ቡድኑን  ላለፈው 1 ወር በአራራት ሆቴል አስቀምጦ ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርግ አስችሏል፡፡ አትሌቶች የቤጅንግ አየር ንብረትን ለመቋቋም እንዲያስላቸው ተግባራዊ በሆነው የልምምድ መርሃ ግብር ሰርተዋል፡፡ ከቃሊቲ እስከ ሶደሬ በሚገኙ የአገሪቱ ሞቃታማ አካባቢዎች በመዘዋወር ዝግጅታቸውን ሲያከናውኑ ከርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በሁለቱም ፆታዎች በ6 የውድድር መደቦች ተካፋይ ትሆናለች፡፡ በ800፤ በ1500፤በ5ሺ በ10ሺ፤ በ3ሺ መሰናክል እና በማራቶን ማለት ነው፡፡ ባለፈው የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ካስመዘገቡት በ10ሺ  የወርቅ ሜዳልያ የወሰደችው ጥሩነሽ ዲባባ በወሊድ እረፍት  እንዲሁም በ5ሺ የወርቅ ሜዳልያ ያገኘችው መሰረት ደፋር ባልታወቀ ምክንያት አለመሳተፋቸው ታውቋል፡፡ ከእነሱ ባሻገር የኢትዮጵያ ቡድን የዓለም ሻምፒዮና ፤ የዳይመንድ ሊግ እንዲሁም የትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ልምድ ባካበቱ አትሌቶች፤ በወጣት እና ተተኪ አትሌቶች የተሞላ ነው፡፡ ከቡድኑ አባላት መካከል በ800 ሜትር ለኢትዮጵያ በታሪክ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ከ2 ዓመት በፊት ያገኘው መሃመድ አማን ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ነው። በሴቶች ደግሞ የዓለም ሻምፒዮና ኮከብ አትሌት ሆኗ ተሳትፎዋ በጉጉት የሚጠበቀው ገንዘቤ ዲባባ ትነሳለች። በ1500 ሜትር ዘንድሮ የዓለም ሪከርድ ያስመዘገበችው ገንዘቤ ዲባባ በ5ሺ ሜትር እንድትወዳደር ፌደሬሽኑ ቢመርጣትም ገንዘቤ በ1500 ሜትር እና በ5000 ሜትር ደርባ መወዳደር ብትችል የብዙዎች ፍላጎት ነበር፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በ3 የዓለም ሻምፒዮናዎች የመሳተፍ እድል የነበራት ገንዘቤ የወርቅ ሆነ የሜዳልያ ውጤት ለማስመዝገብ  ብዙም አልሆነላትም ነበር።  በ5000 ሜትር በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስትሳተፍ በ2009 ላይ 9ኛ እንዲሁም በ2011 8ኛ ደረጃ አግኝታ የነበረ ሲሆን  በ2013 እኤአ ደግሞ በ1500 በመካፈል ስምንተኛ ነበረች፡፡ በተጨማሪም ከ2 ዓመት በፊት በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ የብር ሜዳልያ ያገኘችው አልማዝ አያና፤ በ10ሺ የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው በላይነሽ ኦልጅራ፤ በ5ሺ የብር ሜዳልያ ያገኘው ሐጎስ ገብረህይወት፤ በ3ሺ መሰናክል የነሐስ ሜዳልያ የወሰደችው ሶፍያ አህመድ ልምዳቸውን በመጠቀም ውጤታማ እንደሚሆኑ ተስፋ የተጣለባቸው ናቸው፡፡ በ10ሺ ለወርቅ ሜዳልያ የሚጠበቁት በሆላንድ በተደረገው የማጣርያ ውድድር አስደናቂ ውጤት ያስመዘገቡት ሙክታር ኢድሪስ እና ገለቴ ቡርቃ ይሆናሉ። ከወጣት ተተኪ አትሌቶች ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ የተደረገው በ5000 ሜትር ወንዶች የሚጠበቀው ወጣቱ ዮሚፍ ቀጀልቻ ነው፡፡  በኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ያለው ደጀን ገብረመስቀል ደግሞ በ10ሺ ሜትር በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ከኢትዮጵያ የራቀውን የወርቅ ሜዳልያ ድል እንደሚመልስ ተገምቷል፡፡
የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያ 47 አትሌቶችን በማስመዝገብ ትሳትፋለች፡፡ ለኢትዮጵያ እና ለኬንያ ከመካከለኛ ርቀት እስከ ማራቶን ባሉ ውድድሮች የአሜሪካ፤ የእንግሊዝ፤ እና የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች እየተጠቀሱ ናቸው፡፡ በረጅም ርቀት በተለይ በወንዶች ለእንግሊዙ ሞፋራህ  ከፍተኛ ግምት ሲሰጥ፤ በ800 ሜትር የቦትስዋናው ኒጄል አሞስ፤ የአሜሪካዎቹ ጋለን ሩፕና ራያን ሂል በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የሜዳልያ ተስፋ ፉክክር እንደሚፈጥሩ ተነግሮላቸዋል፡፡ ኬንያ በ200 በወንዶች፤ በ400ሜ በሁለቱም ፆታዎች እና በ400 መሰናክል በወንዶች፤ በጦር ውርወራ በወንዶች በ5 የውድድር መደቦች ከኢትዮጵያ የተሻለ ተሳትፎ ይኖራታል፡፡ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ባሻገር የደቡብ አፍሪካው ዋይዴ ቫን በ200 ሜትር፤ ናይጄርያ በ400 ሜትር  ሌሎች የአጭር ርቀት ውድድሮች ኡጋንዳ እና ኤርትራ ደግሞ በረጅም ርቀት የአፍሪካን ተሳትፎ ያጠናክሩታል ተብሏል፡፡

Read 2400 times