Saturday, 15 August 2015 16:07

በ2020 ከኤች አይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ...

Written by  ዮዲት ባይሳ (ከኢሶግ)
Rate this item
(2 votes)

 የኤች አይቪ ቫይረስ በአለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነታቸው ከሚታወቁ የማህበረሰብ ጤና ችግሮች መካከል ቀዳሚውን ስፍራ እንደያዘ ይገኛል፡፡ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2014/ ብቻ 1.2/ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
አፍሪካ በተለይም ደግሞ ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የችግሩ ከፍተኛ ተጠቂዎች ሲሆኑ 25.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፡፡ ይህም ከአለም 70%
የሚሆነውን ቁጥር ይሸፍናል፡፡ በተመሳሳይ በእነዚህ ከሰራ በታች ባሉት የአፍሪከ ሀገራት በየአመቱ 300.000/ አዳዲስ ህፃናት በቫይረሱ እንደሚያዙ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡
መንግስት በጤናው ዘርፍ የምእተ አመቱ ግብ ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል በፈረንጆቹ 2020 ከኤች አይቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ማፍራት የሚለው አንዱ ነው፤ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው በተግባር ላይ ውለዋል ከእነዚህም መካከል፡-
በጤናው ዘርፍ ከሚሰሩ ፖሊሲ አውጪዎች ጋር በጋራ መስራት
የህክምና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኤች አይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የPMTCT አገልግሎትን እንዲሰጡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ
አገልግሎቱን በሚመለከት ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ
ዋናዋናዎቹ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የኤች አይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን የህክምና ክትትል PMTCT(Prevention of mother-to-child transmission) አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የግል እንዲሁም የመንግስት የህክምና ተቋማት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
በፈረንጆቹ 2007 አመተ ምህረት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው 977.397 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 75.402 የሚሆኑት ነብሰጡር እናቶች ናቸው፡፡
የኤች አይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ በዋናነት የሚተላለፈው በወሊድ ግዜ እንዲሁም ጡት በማጥባት ሲሆን ይህንን ለመከላከል የሚሰራው ስራም Prevention Mother to Child Trans mission (PMTCT) ወይም ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል በሚል በስራ ላይ ከዋለ ጥቂት የማይባሉ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእኛም ሀገር ይህ አይነቱ አገልግሎቱ በፈረንጆቹ 2001 የተጀመረ ሲሆን አገልግሎቱ ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ 79.4% የሚሆኑ እናቶችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር (ኢሶግ) በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ለሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ይህን አገልግሎት ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ይሰጡ ዘንድ የስልጠና፣ የቁሳቁስ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ ይገኛል፡፡
በዛሬው ፅሁፋችንም በአዲስ አበባ ከተማ አገልግሎቱን እየሰጡ ከሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት መካከል የሶስቱን ተሞክሮ ልናስነብባችሁ ወደናል፡-
በቅድሚያ የተገኘነው በሴማህ የእናቶች እና የህፃናት የህክምና ማእከል ነበር፡፡ ማእከሉ አገልግሎቱን በተደራጀ መልኩ ለመስጠት እንዲቻል እራሱን የቻለ ክፍል ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ በክፍሉ ውስጥ በስራ ላይ ያገኘናት ሲስተር ጎንደሪት ነጋሽ ትናገራለች፡፡
“...አሁን በእኛ ማእከል ያለው ነገር በጣም ጥሩ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሶስት ወር ግዜ ውስጥ ያለውን እንኳን ብንመለከት የኤችአይቪ ምርመራ አድርገው ክትትላቸውን እያደረጉ ያሉ ሁለት እናቶች አሉን፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ውጤታቸውን አውቀው ለእርግዝና ክትትል እኛ ጋር የመጡ ሶስት እናቶች አሉን። ስለዚህ መጀመሪያ አንዲት እናት ለእርግዝና ክትትል እኛ ጋር ስትመጣ በቅድሚያ ኤች አይቪን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ ምርመራዎችን እንድታደርግ ይደረጋል፡፡ ባጠቃላይ አሁን ላይ ያለው ነገር አበረታች ነው፡፡ ሰዉም ከድሮው የተሻለ ግንዛቤ አለው፡፡...”
ሁሉም እናቶች የኤች አይቪ ምርመራውን ከማድረጋቸው አስቀድሞም በቂ ገለፃ እና የምክር አገልግሎት እንደሚደረግላቸው ትገልፃለች፡፡
“...ምርመራውን ከማድረጋቸው በፊት ለሁሉም እናቶች የምክር አገልግሎት እንሰጣቸዋለን፡፡ ጤናማ የሆነ ልጅ እንዲወልዱ ተመርምረው እራሳቸውን ማወቅ እንዳለባቸው እንነግራቸዋለን፡፡ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ አብዛኞቹ እናቶች ፈቃደኛ ሆነው ምርመራውን ደርጋሉ፡፡ ውጤታቸውን ካወቁ በኋላም ያለማቋረጥ ክትትላቸውን ያደርጋሉ፡፡...”
ሲስተር ሄለን በበፀጋ የእናቶች እና የህፃናት ሆስፒታል በPMTCT ክፍል ውስጥ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይም ሆነ በተጠቃሚዎች ቁጥር ላይ ብዙ መሻሻሎች አሉ ትላለች፡፡
“...ድሮ ከነበረው ጋር ስናነፃፅረው በእኔ አመለካከት አሁን ላይ ብዙ ለውጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለእርግዝና ክትትል ወደ ሆስፒታላችን የሚመጡ ሁልም እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ አንዲት እናት ለክትትል ስትመጣ መጀመሪያ የሚያስፈልጉ ምርመራዎችን ሁሉ ጨርሳ ወደ እኛ ጋር ትላካለች የምክር አገልግሎት ከሰጠናት በኋላም ምርመራውን ታደርጋለች ማለትነው፡፡ ስለዚህ ከምናየው የተገልጋዩ ብዛት በመነሳት ለውጥ አለ ማለት እንችላለን፡፡...”
ሁለቱም ባለሙያዎች አብዛኞቹ እናቶች ምርመራውን ለማድረግ ያላቸው ተነሳሽነት ጥሩ የሚባል እና በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማቸውም ይናገራሉ፡፡    
“...በእኛ ተቋም በPMTCT በኩል እናቶች ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት ሁሉ እንሰጣለን። ነገርግን ብዙ ግዜ ምርመራውን አድርገው ውጤቱ ፖዘቲቭ ከሆነ በጣም ይደነግጣሉ፡፡ በቀጣይ ያለውን ህክምና ለመጀመርም ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ አንዳንዴ እንደውም ክትትላቸውን አቋርጠው የሚጠፉብንም አሉ። ይህ ሲሆን በአድራሻቸው ፈልገን ጠርተን የምክር አገልግሎት ሰጥተን መድሀኒት እንዲጀምሩ እናደርገለን፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እኛም የቻልነውን እያደረግን ነው በተጠቃሚዎችም በኩል ጥሩ ተነሳሽነት አለ፡፡...”
ያለችን ደግሞ በማሪስቶፕስ እስፔሻላይዝድ የማህፀን እና ፅንስ ህክምና ማእከል የነጋገርናት ሲስተር ሰናይት ብርቄ ነች፡፡
በአለም የጤና ድርጅት በተደረገ ጥናት ተገቢው ህክምና ካልተደረገ የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድሉ ከ15-45 ፐርሰንት ይደርሳል፡፡ ይህም፡-
በእርግዝና ወቅት 5-10%
በወሊድ ግዜ 10-15% እንዲሁም
ጡት በማጥባት 5-20% ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ እድል ይኖረዋል፡፡
አገልግሎቱ በማይሰጥበት ሁኔታም ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ የሚኖረው መተላለፍ እንደየ ሀገራቱ ሁኔታ ሊለያይ የሚችል ሲሆን የመከላከሉ ስራ ውጤታማ ከሆነ ግን ስርጭቱ እስከ 5% ይወርዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር አንዲት እናት ቫይረሱ በደሟ ሲገኝ መድሀኒት ከመጀመሯ በፊት የሲዲፎር መጠኗ እንዲታይ ይደረግ የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን የትኛዋም እናት ፖዘቲቪ መሆንዋ ከታወቀ ግዜ አንስቶ መድሀኒት እንድትጀምር እንደሚደረግ ሲስተር ብርቄ ትገልፃለች፡፡
“...አንዲት እናት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ መሆኗ ከታወቀ ወዲያውኑ መድሀኒት እንድትጀምር እናደርጋለን፡፡ እንደ ድሮ ቅድሚያ ሲዲፎር ይሰራ አንልም፡፡ በፊት ሲዲፎር አይተን ነበር መድሀኒት የምናስጀምረው አሁን ግን ፖዘቲቭ መሆኗን ካወቀች እና የምክር አገልግሎት ከወሰደች በኋላ በማንኛውም ሰአት መድሀኒቱን እናስጀምራታለን...”    
ይህም መንግስት የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡       
ዩኒሴፍ በ2012 ያወጣው መረጃ በሀገራችን የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ከሚገኝ እናቶች መካከል 24 ፐርሰንት የሚሆኑት ብቻ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ የሚሰጠውን ህክምና እንደሚያገኙ ጠቁሟል፡፡
ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ የትዳር አጋሮች የሚኖራቸው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ሶስቱም ባለሙያዎች ይስማማሉ። ነገርግን በስራቸው ላይ ካስተዋሉት በመነሳት የትዳር አጋሮች ተሳትፎ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ እና በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ እንዳይሆን ተግዳሮት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡
ሲስተር ሄለን ከብዙ ገጠመኞቿ መካከል አንዱን እንዲህ አጫውታናለች፡-
“...እናቶች መጀመሪያ ለእርግዝና ለክትትል ሲመጡ በቀጣይ ቀጠሮ የትዳር አጋሮቻቸውን ይዘው እንዲመጡ እና እነሱም እንዲመረመሩ እንነግራቸዋለን፡፡ ነገርግን ብዙዎቹ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ስለማይሆኑ የቻልነውን ያህል ግፊት እናደርጋለን፡፡ አንድ ግዜ አንዲት እናት ለክትትል መጥታ በቀጣይ ቀጠሮ ስትመጣ ባሏን ይዛ እንድትመጣ እና እሱም እንዲመረመር ነገርኳት ...አንድግዜ ስራ ይበዛበታል... አድ ግዜ ሀገር ውስጥ የለም ስትለኝ ቆየች... እኔም ጥያቄን አላቆምኩም በመጨረሻ ይዛው መጥታ ሲመረመር ውጤቱ ፖዘቲቪ ሆነ... እንዲህ አይነት ሁኔታዎች በየግዜው ይገጥሙናል፡፡...”

Read 3506 times