Saturday, 15 August 2015 16:19

ቡሄ

Written by  ደ.በ
Rate this item
(6 votes)

  ቡሄ ጨፋሪ ልጆችን ለመምረጥ የተለያየ ሃሳብ አቅርበን ነበር፡፡ “እገሌ ይረብሻል----ድምፁ ያስጠላል----ሣንቲም ያጨናብራል!” ወዘተ እያልን ብዙ ተናቆርን፡፡ የማታ ማታ ግን ከመሃላችን እንደ ትልቅ ሰው የምናየው ባህሩ፣ አስታረቀንና ስምንት ልጆች ቡድን ሠራን፡፡
ስምንት መሆናችን የምንካፈላትን ሣንቲም ያሳሳል ብለው የሰጉ ነበሩ፡፡ እነሱ ስድስት እንድንሆን መከሩ። ግን ከምርጫው ሊወገዱ የታሰቡት ዳኜና ሻውል ዓይናቸውን ሲያቁለጨልጩ አሳዘኑን፡፡
“በቃ - ይሁኑ - ይሁኑ!” አልን፡፡
በቀለ ግን እንድናስገባው ቢጐተጉተንም በአንድ ድምፅ እምቢ አልነው፡፡ ብናስገባው ገንዘብ ያዥ ካልሆንኩ ይላል፡፡ ገንዘብ ያዥ ሲደረግ ደግሞ፣ ብር ሠርቆ ወይ ካልሲ ውስጥ አሊያም የውስጥ ሱሪው ውስጥ ይወሽቃል። ያኔ ጭቅጭቅ ይፈጠርና ጭፈራችን ይበላሻል፡፡ ከዚህ በፊት ሁለቴ እንዲህ አድርጎናል፡፡
ልጆች ከተመራረጥን በኋላ ደህና ገንዘብና ጥሩ ሙልሙል የሚሰጡንን ሰዎች ቤት ለየን፡፡ ማን ጥሩ እንደሚሰጥ፣ ማን እንደሚሰስት ከልምድ እናውቀዋለን፡፡ የስፖርት ሣንቲም ስንጠይቅና በሆያ ሆዬ ብዙ ተምረናል።  
የመጀመሪያ ምርጫችን ጋሽ ሰብስቤ ነበር፡፡ ጋሽ ሰብስቤ መቼም ቢሆን ልጆች ከጠየቁት ብሩን መዥርጦ የሚሰጥ ቸር የጓደኛችን አባት ነው። በክላሰር ላይ የአሥራ አንድ ተጫዋቾችን ሥዕል ደረታችን ላይ እንደ አኮርድዮን ዘርግተን ስንሄድ፣ አምስት ብር ስለሚሰጠን እሱ ሲገጥመን እንደ ሎተሪ ነው የምንቆጥረው፡፡ ሌላው የቡሄ ጭፈራ ምርጫችን የእትዬ የውብዳር ግሮሠሪ ነው፡፡ እትዬ የውብዳር ግሮሠሪ፣ በተለይ በበዓል ሰሞን አዝማሪ ስለሚኖርና የከተማው ትልልቅ ሰዎች ስለሚሰበሰቡ አንዱ አንዱን እያየ ብሩን እንደሚመዝ አሳምረን እናውቃለን፡፡ ሥጋታችን ምናልባት ዛሬም በቀለ እየተከታተለ እንዳይረብሸን ነው፡፡ በቀለ ተንኮለኛ ስለሆነ ሸር እንዳይሠራብን በሚል እኔ ገንዘብ ያዥ ሆንኩ፡፡ ግጥም አውጪ ፈለቀ ሆነ፡፡ እኔ ጠንቃቃ በመሆኔ፣ ፈለቀ ደግሞ ምርጥ ድምጽ ስላለው ተመረጥን፡፡
እኔ ግን ልቤ አልተረጋጋም፡፡ በቀለን አውቀዋለሁ። ተንኮል ሲሸርብ የሚችለው የለም፡፡ ከእጅ ላይ እንኳ ሲቀማ እንደ ጭልፊት ነው፡፡ ሩጫማ… ሰጐን ነው። የልቡን ለማድረስ ልስላሴው አያድርስ ነው፡፡ እንደ ዔሊ አንገቱን ቀብሮ ሲረግጡት እንኳ ድንጋይ ይሆናል፡፡ ችግሩ የሚገለጠው ከተፈፀመ በኋላ ነው። የሆኖ ሆኖ ብቻ ቡድናችን ተናካሽ ውሻ ከገጠመን የምንከላከልበትን በትር ይዞ፣ የሙልሙል ከረጢቱን ታጥቆ ተነሣ፡፡ ብርዱን ለመከላከል ሁላችንም ያለንን ሙቀት የሚሰጥ ልብስ ለበስን፡፡
ከተማችን ተፈሪ ኬላ፣በብርሃን እሣት ነድዳለች፡፡ ገና ችቦ ሲለኮስማ ጉድ ነው፡፡ በፊልም የምናውቃቸውን የአውሮፓ ከተሞች መምሰሏ የማይቀር ነው፡፡ ሻይ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች፣ ጠላ ቤቶችና አረቄ ቤቶች በራሳቸው ሙዚቃ ናላቸው ዞሯል፡፡
እኔ ከረጢቴን ተቀበልኩ፡፡ ሣንቲምና ብር መያዣ እንዲሆነኝ የጂንስ ሱሪዬን ኪስ አመቻቸሁ፡፡ ይሄ ካነሰ የደረብኩት ጃኬት ኪስ አንድ ዶሮ መደበቅ ይችላል፡፡ ከተማው መሀል ላይ ካለችው የአድባር ዛፍ ሥር ከባህር ዛፍ እንጨት በተሠራው ቦታ ተቀምጠን ድምፃችንን ሳልን፣ አቅማችንን ሞከርን፡፡ የፈለቀ ድምጽ ዛሬ ብሶበታል፡፡
ቡሄ - ቡሄ በሉ
ል - ጆ- ች ሁሉ!
ቡሄ መጣ ያ - መላጣ
ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ!
ሁላችንም ለፈለቀ አጨበጨብንለት፡፡ ይህን ጭብጨባ ተከትሎ ግን ድንገት በቀለ ወደ እኛ ሲመጣ አየነው፡፡ የፈራሁት ደረሰ!
“የምን ድርቅና ነው - አንፈልግም ካልን ለምን ይመጣል?” አለኝ ዳኜ፤ወደ ጆሮዬ ተጠግቶ፡፡
“ምን ቸገረህ ይምጣና ይገተር፣ ሣንቲም እንደሆን አያገኛት!; አለ ሌላው፡፡
አጅሬው ቀጥ ብሎ መጣ፡፡ ቢሆንም ሁላችንም ፊት ነሣነው፡፡
መጀመሪያ ወይዘሮ አበበች ጠጅ ቤት ሄድን፡፡ መሀል ከተማ ነው፡፡ እትዬ አበቡ ዶቃ መልክ ያለውን የጠጅ ማንቆርቆሪያ ይዘው በፈገግታ ተቀበሉን፡፡ አጠር ያሉ፣ ደርባባ ሴት ወይዘሮ ናቸው፡፡ ትልልቅ ዓይኖቻቸውን እያበሩ፣ እኛ ደግሞ የአምፑሉን ብርሃን እየሸሸን ተፋጠጥን፡፡
“ይሄ የአበበ ልጅ አይደለም? ይሄ የእገሌ ልጅ አይደለም?” ሲሉ ግጥሙ ጠፋብን፡፡ ሣንቲም  እንደሚሰጡን ገምተን ነበር፡፡ ልክ የለበሷት ጋዋን ኪስ ውስጥ እጃቸውን ሲሰዱ ፈለቀ ግጥሙ መጣለት፡፡
   “ዓመት ዓውዳመት
ድገምና ዓመት፤
የእትዬ አቡን ቤት
ወርቅ ይዝነብበት!”   
…እያልን አስነካነው፡፡ በትራችን የሊሾውን ወለል እንዳይጐዳ አድርገን፣ ገና ሳንቲሙ ሳይሰጠን  ምርቃቱን አቀላጠፍነው፡፡ ማመን አቃተን፡፡ አሥር ብር አሻሩን። ኡ…ኡ…ኡ…ማለት ነው የቀረን። ቀወጥነው፡፡ እትዬ አበቡ በትልልቅ ዓይኖቻቸው አዩን፡፡ ከዚያ በኋላ ጋሽ በላይ ማንቆርቆሪያቸውን እንደያዙ መጡና አሥር ብር ጨመሩልን፡፡  ከሁላችንም የበለጠ የተደሰተው ዳኜ ነው። አባቱ ናቸው፡፡
ፉጨቱ አገር ሞላ፡፡ በቃ አሁን ጋሽ ሰብስቤን እንኳ ባናገኝ ግድ የለም፡፡ ወደ ሌላ ሰው ቤት  ስንሄድ በቀለ ከኋላችን ሲከተለን ነበር፡፡ ነገረ ሥራውን ፈጽሞ አልወደድነውም፡፡ እትዬ የውብዳር ቤት ነበር የሄድነው። የእሷ ግሮሠሪ ከተማው እንብርት ላይ ነው፡፡ ከሺኢቾ፣ ከሆንቾና ከባለወልድ የሚመጡ መንገዶች መገናኛ!
እዚያም ጨፈርን፡፡ እትዬ ውቤ መጣች፡፡ የከተማዋ ጣቢያ አዛዥም ብቅ አለ፡፡ ፊቱ እንደ ሮማን ከብልል ያለና ሙሉ ነው፡፡ ሞቅ ብሎታል። አፉን ያዝ እያደረገው፣ “ግጥሙን አስተካከሉ” አለን። ሁላችንም ዝም አልን፡፡
“እናቴ ቤት አለኝ ለከት
አክስቴ ቤት አለኝ ለከት” ነው የሚባለው፤የዛሬ ልጆች ዝም ብላችሁ ሣንቲም ብቻ! ወይኔ በኛ ጊዜ!” አለና ሁለት ብር አውጥቶ ሰጠን፡፡ እትዬ የውብዳር በፈገግታ ተሞልታ፤ “እናንተ በዚህ ጨለማ ውሻ እንዳይነክሳችሁ!..በጊዜ ግቡ!” አለችን፡፡ እኛ ግን ምክሯን አልነበረም የፈለግነው፡፡ ብሯን ነው፡፡ ወደ ባንኮኒዋ ስትሄድ የሁላችንም አይን ተከትሏት ነጐደ።
“በሉ በደንብ ጨፍሩ!” አለችን በሚያምር ፈገግታ። የሷን ስምና የልጅዋን ሥም እየጠራን አሞጋገስናት፡፡ አምስት ብር! የከበርቴነት ስሜት ተሠማን፡፡ ፈለቀ ድምፁ ጨመረ፡፡ እንደ ፏፏቴ አንቆረቆረው፡፡ ከረጢታችንን ሙልሙል ሞላው። ብሮቹን በጂንስ ኪሴ ውስጥ ጠቀጠቅኩ፡፡ ሁሉን አዳርሰን ስናበቃ፣ለክፍፍል ተቀመጥን። ያኔ ሁላችንም በሚደርሰን ገንዘብ የምንበላው የምንጠጣውን --- ለስላሳ… ብርቱካን… ብስኩት… በዓይነ ህሊናችን መሳል ጀመረን፡፡  
ከተማው በየቦታው በተለኮሰ ችቦ ውጋጋን ደምቋል፡፡ አበባ የሚመስሉ ነበልባሎች በየደጁ ፈክተዋል፡፡
እጄን ወደ ቀኝ ኪሴ ከተትኩ፡፡ ሁሉም አዩኝ። እኔም አየኋቸው፡፡ እንደገና እጄን ወደ ከረጢቱ ሰደድኩ፡፡ ዓይኔን ማመን አቃተኝ፡፡ ያገኘሁት ጠፍጣፋ ድንጋዮች ነበር፡፡
“እናንተ…እናንተ” አልኩና አዙሮኝ ወደቅሁ፡፡ ለካስ ኪሴ ቀዳዳ ነበር፡፡ አንድ ሁለቱ የቡሄ ጓደኞቼ ግን “በቀለ የሆነ ነገር አድርጐ ሲሮጥ አይተነዋል!” በማለት እሱ ወደሮጠበት አቅጣጫ አስነኩት፡፡ እኔ ከወደቅሁበት ስነሳ ከተማው በሙሉ የገሀነም እሣት ይመስል ነበር፡፡

Read 3966 times