Saturday, 15 August 2015 16:22

ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና አስፈላጊ የላብራቶሪ ምርመራ ተጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ወሳኝ የሆነ አዲስ የላብራቶሪ ምርመራ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት (ፓስተር) የተጀመረ ሲሆን ምርመራው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በቅርቡ እንዲጀመር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ኢንስቲቲዩቱ ቀደም ሲል በአገሪቱ ያልነበሩና በውጭ አገር እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስወጡ  የላብራቶሪ ምርመራዎችን ለማድረግ በሚያስችል መሣሪያና የሰው ኃይል እንደተደራጀ ታውቋል፡፡
ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተደረገለት የ13 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ በተደራጀው የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት፤ የጥቁር አንበሳ፣ የቅዱስ ጳውሎስ፣ አለርት፣ ቅዱስ ጴጥሮስና የአማኑኤል የአዕምሮ ህክምና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የተገለጸ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች በሆስፒታሎቹ ለሚቋረጡ የላብራቶሪ ምርመራዎችም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት በጥቁር አንበሳ፣ በጳውሎስና በአማኑኤል ሆስፒታሎች የሙከራ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የገለፁት የኢንስቲቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አምሃ ከበደ፤ በቅርቡ በአምስቱ ሪፈራል ሆስፒታሎች አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከአምስቱ ሆስፒታሎች ተወካዮች ጋር የስምምነት ሰነድም ተፈራርመዋል፡፡
ኢንስቲቲዩቱ እስከዛሬ በአገሪቱ ያልነበሩ፣አዳዲስ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚያስችል ዘመናዊ መሳሪያዎችና ባለሙያዎች መደራጀቱን የገለፁት የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፤ ወደፊት ሁሉም አይነት የላብራቶሪ ምርመራዎችን በአገር ውስጥ ለማድረግ ጥቂት ሥራዎች ብቻ እንደሚቀሩና እነዚህን በማሟላት ሙሉ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል ዲያሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን አበበ በሰጡት አስተያየት፤#የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናን በአገሪቱ ለመጀመር የሚደረገውን ጥረት የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቱ በእጅጉ ያግዘዋል; ብለዋል፡፡

Read 3561 times