Saturday, 15 August 2015 16:23

ስለ ጉንፋን ነገሬ የማንላቸው አንዳንድ ነጥቦች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(22 votes)

  የበር እጀታ የጉንፋን ቫይረስን ሊያስተላልፍ ይችላል
                        
       ጉንፋንን ከቅዝቀዜና ብርድ ጋር በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም እንዲህ እንደ አሁኑ ክረምት በሚሆንበት ወቅት ብዙዎቻችን ለጉንፋን መጋለጣችን አይቀሬ ነው፡፡ ዝናብ፣ ብርድና መጥፎ ሽታ ለጉንፋን መከሰት የራሳቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ ቢሆንም ዋናው የጉንፋን መንስኤ ግን ቫይረስ ነው፡፡ ጉንፋን ለማስያዝ የሚችሉ ከ200 በላይ የቫይረስ ዝርያዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ቫይረሶች መካከል በመተላለፍ አቅማቸውና በስፋት በመታየታቸው ቀዳሚነቱን የሚይዙት ራይኖ ቫይረስ የተባሉት ጉንፋን አምጪ ቫይረሶች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ለጉንፋን አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው? ህክምናስ አለው? መከላከያዎቹስ? እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ Journal of Medicine በቅርቡ ለንባብ ያበቃውን መረጃ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
የጉንፋን መንስኤ
ጉንፋንን ሊያስይዙ የሚችሉ የቫይረስ ዝርያዎች 200 ይደርሳሉ፡፡ በስፋት የሚታወቀውና ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የመተላለፍ አቅም ያለው ቫይረስ፣ጉንፋን አምጪ ቫይረስ ነው፡፡ ጉንፋን የላይኛው የመተንፈሻ ስርዓታችን አካል የሆኑትን አፍንጫና ጉሮሮ የሚያጠቃ ህመም ነው፡፡ ጉንፋን ራሱ የሚተውና ቶሎ የሚድን ህመም ቢሆንም የአፍንጫና የጉሮሮ ቁስለቱ፣ ራስ ምታቱና የመገጣጠሚያ ህመሞችን ማስከተሉ፣ ታማሚውን ምቾት የሚነሳ ሲሆን አንዳንዴ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን አልጋ ሊያስይዝ የሚችል ህመም ነው፡፡
ጉንፋን የዕድሜና የፆታ ልዩነት ሳያደርግ ሁሉንም ሰው ሊይዝ የሚችል ህመም ቢሆንም ከአዋቂዎች ይልቅ ልጆች በጉንፋን ቶሎ ቶሎ የመያዝ ዕድሉ አላቸው፡፡ አዋቂዎች በአብዛኛው በዓመት አራት ጊዜ ያህል በጉንፋን ሲያዙ፣ ልጆች በዓመት ደግሞ 10 ጊዜ ያህል  በጉንፋን የመያዝ አጋጣሚ ይኖራቸዋል፡፡
የጉንፋን ቫይረስ ወደ ሰውነታችን ውስጥ የሚገባው በአፍና በአፍንጫችን በኩል ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በመጨባበጥና እንደ ስልክ፣ ፎጣ፣ የበር እጀታ ያሉ በጋራ ጥቅም ላይ በሚውሉ ቁሳቁሶችም አማካይነት ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ጉንፋንን በማስተላለፍ ረገድ ከትንፋሽ የበለጠ መጨባበጥ ከፍተኛውን ስፍራ እንደሚይዝም Journal of Medicine ይጠቁማል፡፡ በጉንፋን የተያዘ ሰው ከአፍንጫው የሚወጣውን ፈሳሽ ያስወገደበት እጁ ላይ ጉንፋን አምጪው ቫይረስ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ፣ ይህንን በጉንፋኑ ቫይረስ የተበከለ እጅ የጨበጠ ሰው በቀላሉ በበሽታው የመያዝ ዕድል ይኖረዋልና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
ጉንፋን የሚያስከትለው የጤና ችግር
ጉንፋን አብዛኛውን ጊዜ እንደ ቀላል የሚታይና በቀናትና በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሊድን የሚችል በሽታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ጉንፋን ህመምተኛውን አልጋ ከማስያዝም በላይ ሌሎች ጠንቆችንም ሊያስከትል የሚችል የጤና ችግር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ በተለይም በህፃናትና በልጆች ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን በጉንፋን የተያዙ ልጆች የጆሮ ኢንፌክሽን ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ይታያል፡፡ ይህም በከባድ ራስ ምታት፣ በጆሮ ህመም ስሜት፣ በትኩሳትና አረንጓዴ ፈሳሽ በአፍንጫ በኩል በማውጣት ይገለፃል፡፡ ጉንፋን በተለያዩ መንገዶች የቤት ውስጥ ህክምና በማድረግና እረፍት በመውሰድ ሊድን የሚችል ህመም ሲሆን ቶሎ የማይድን ጉንፋን ለሳይነስ፣ ለጉሮሮ ኢንፌክሽን፣ ለኒሞኒያና ብሮንካይትስ የማጋለጥ ዕድል አለው፡፡
ጉንፋን ለምን ደጋግሞ ይከሰታል?
የሰው ልጅ በሽታን የመከላከል አቅም ከሚለካባቸው ቀላል ህመሞች አንዱ ጉንፋን ነው፡፡ በየጊዜው በጉንፋን እየተያዙ የሚተኙ ሰዎች በሽታን የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ነው፡፡ በእርግጥ በጉንፋን በተደጋጋሚ ለመያዝ ዕድሜ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ከአዋቂዎች ይልቅ ልጆች በጉንፋን የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ሰዎች በተፈጥሮአቸው ዕድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ፣ ለአብዛኛዎቹ የጉንፋን ቫይረሶች መቋቋሚያ የሚሆን አቅምን እያደረጁ ይሄዳሉ። ስለዚህም በጉንፋን የመያዝ ዕድላቸው ይቀንሳል። እንደ ስኳር፣አስምና ኤችአይቪ ያሉ ህመሞች ያሉባቸው ሰዎች፣ በጉንፋን ቶሎ ቶሎ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን በቶሎ ለመዳንም ይቸገራሉ፡፡
ጉንፋን መድኀኒት አለው?
ጉንፋንን ሊያድን የሚችል መድኀኒት አለመኖሩን Journal of Medicine ጠቁሟል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች በጉንፋን በሚያዙበት ወቅት ፀረ ባክቴሪያ መድኀኒቶችን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ግን ውሉን የሳተ ነው፡፡ ለምን ቢሉ? የጉንፋን መነሻው ቫይረስ እንጂ ባክቴሪያ አይደለም፡፡ ስለዚህም እንደ አሞክሳሲሊን ባሉ ፀረ - ባክቴሪያ መድኀኒቶች ጉንፋንን ለማከም መሞከሩ ብልህነት የጎደለው መሆኑን ጆርናሉ ያመለክታል፡፡ በጉንፋን ህመም ወቅት የሚወሰዱ የተለያዩ የህመም ማስታገሻ መድኀኒቶች ከጉንፋን ጋር በተደራቢነት ያሉትን እንደ ራስ ምታት፣ ትኩሳት የመሳሰሉት  የሚያስከትሉትን የህመም ስሜት ለማስታገስ ከመርዳታቸው ውጭ ለጉንፋን ህመሙ የሚሰጡት አንዳችም ፋይዳ የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ በቤት ውስጥ የሚደረጉ ህክምናዎች በሽታውን በቶሎ ለማዳን ያስችላሉ፡፡
ሰዎች በጉንፋን በሽታ በሚያዙበት ወቅት በቂ እረፍት ማድረግ እንደሚገባቸው የሚጠቁመው ጆርናሉ፤ ይህም ለታማሚዎቹ ብቻ ሳይሆን ከታማሚዎቹ ጋር አብረው የሚሰሩና በተለያዩ ምክንያቶች የሚገናኙ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ ለማድረግ እንደሚረዳም ገልጿል፡፡
ጉንፋንን የማከሚያ መንገዶች
በጉንፋን ሲያዙ በቂ እረፍት በሚያደርጉበት ቤትዎ ውስጥ ሆነው በሽታዎን በተለያዩ መንገዶች ማከም ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ የጉንፋን በሽታ ማከሚያ መንገዶች መካከል፡- ብዙ ፈሳሾችን መውሰድ፣ ውሃ፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች፣ ሾርባ፣ ሻይና አጥሚት መሰል ትኩስ መጠጦችን ቶሎ ቶሎ መጠጣት የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም በላብና በአፍንጫችን የሚወጡ ፈሳሾችን ለመተካትና የሰውነትን የውሃ ሚዛን ለመጠበቅ ይረዳል። ካፌይንና አልኮልነት ያላቸው መጠጦች በሰውነታችን ውስጥ የሚገኘውን ውሃ የመምጠጥ ባህርይ ስለአላቸው በጉንፋን በተያዙ ወቅት እነዚህን መጠጦች ከመጠቀም ይቆጠቡ። ትኩስ መጠጦችን በተለይ ሾርባዎችን (የዶሮ ሾርባ) መጠጣት የጉንፋንዎን ዕድሜ ለማሳጠር ይጠቅማል። አንዳችም ሳይንሳዊ ህክምና፣ መድኀኒትና ክትባት ያልተገኘለት የጉንፋን በሽታ፤ በቀላሉና የግል ንፅህናን በአግባቡ በመጠበቅ ብቻ ልንከላከለው የምንችለው በሽታ ስለሆነ ሁልጊዜም ለንፅህናዎ ትኩረት ይስጡ። በሚስሉና በሚያስነጥሱ ጊዜ መሃረብ ወይም ሶፍትን መጠቀም አይዘንጉ፡፡ እጅዎን ከመታጠብዎ በፊት ፊትዎንና አፍንጫዎን ከመነካካትም ሆነ ወደ ገበታ ከመቅረብ ይቆጠቡ፡፡  

        ጉንፋንዎን በቤትዎ ያክሙ

   ነጭ ሽንኩርት
ከፀረ ባክቴሪያና ፀረ ፈንገስ ባህሪው በተጨማሪ በጉሮሮ አካባቢ የሚከሰቱ ቁስሎችን ለማከም ይረዳል፡፡ ነጭ ሽንኩርት አስም፣ የአፍንጫና የጉሮሮ ህመሞችን ያስታግሳል፡፡ ነጭ ሽንኩርትን መቀቀል መድኀኒትነት ያለውን ኦሊሲን የተባለ ንጥረ ነገር ስለሚያጠፋው በጥሬው ከትፈው ቢወስዱት የጉሮሮ ህመምና ጉንፋንዎን ድራሹን ሊያጠፋልዎት ይችላሉ፡፡

      ቀረፋ
ቀረፋ ጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛን በመፈወስ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡ ጥቂት የቀረፋ ዱቄትን በሞቀ ውሃ ውስጥ ጨምረው ይጠጡት፡፡ ከጉንፋንዎና ኢንፍሌዌንዛዎ እፎይታን ያገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ መጠን ያለውን ቀረፋ መጠቀም ችግር ሊያስከትልብዎ ይችላልና ይጠንቀቁ፡፡ በተለይም ነፍሰጡር ሴቶችና የሚያጠቡ እናቶች ቀረፉን በፍፁም መጠቀም የለባቸውም፡፡



     ዝንጅብል
ደረት ላይ ለሚሰማ ጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ በግማሽ ሊትር ውሃ ውስጥ 3 ማንኪያ የዝንጅብል ዱቄት መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ጨምረው ይታጠቡ፡፡ በጉንፋንዎ ሳቢያ የምግብ መዋጥ ችግር ካጋጠምዎ ዝንጅብል አፍልተው ይጠጡበት፡፡ የማቅለሽለሽ ስሜትን በማጥፋት የአፍና የጉሮሮዎ አካባቢ ምግብ እንዲቀበል ያደርግልዎታል፡፡


      የዶሮ ሾርባ
የዶሮ ሾርባ ለጉንፋንና ለኢንፍሉዌንዛ በሽታዎች ፍቱን መድኀኒት ሆኖ ለዓመታት ዘልቋል፡፡ በአትክልቶችና ቅመሞች ተከሽኖ የተሰራ የዶሮ ሾርባ በጉንፋን ሳቢያ የሚከሰተውን የአፍንጫ መዘጋት ይከፍታል፡፡

          ማር
ማር፣ ሎሚና ሙቅ ውሃ ከፍተኛ ህመም ያለውን የጉንፋን በሽታና ሳልን ለማስታገስ ይረዳል፡፡ ማርን በትኩስ ወተት መጠጣት ህመሙ እንዲታገስና እንቅልፍ እንዲወስድዎ ያግዛል፡፡

        ሎሚ  
ሎሚ ለተለያዩ የጤና ችግሮች ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ጉንፋንዎ በአፍንጫዎ ላይ ጉዳት ካስከተለና አፍንጫዎ ችግሩን ቀጭን ፈሳሽ በማውጣት እየገለፀልዎ ከሆነ በአንድ ብርጭቆ የፈላ ውሃ ውስጥ ሁለት ሎሚዎችን ጨምቀው በትኩሱ ይጠጡበት፡፡ ጉንፋንዎ መሻሻልን እንዳሳየ አፍንጫዎ ፈሳሹን በማቆሙ ሊረዱት ይችላሉ፡፡ ሎሚ ለአስም፣ ለጉንፋንና ለብሮንካይትስ ህመሞች ማስታገሻነት ያገለግላል፡፡

Read 28285 times