Monday, 24 August 2015 09:24

በዘንድሮ ክረምት በአዲስ አበባ 14 ሰዎች በውሃ አደጋ ሞተዋል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

     በዘንድሮው ክረምት ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማ 14 ሰዎች በውሃ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ባለፈው ዓመት ክረምት ከደረሰው አደጋ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠር ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ኪዳነ አብርሃ ለአዲስ አድማስ
እንደገለፁት፤ ክረምቱ ከገባበት ሰኔ 1 ጀምሮ እስከ ትናንት በስቲያ 15 የውሃ አደጋዎች ደርሰው የ14 ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል፡፡ አብዛኞቹ በኩሬና በወንዞች ውስጥ ለመዋኘት ሲሞክሩ ሰጥመው መሞታቸውን አቶ ኪዳነ ገልፀዋል፡፡ አደጋዎቹ በብዛት ያጋጠሙት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማሪያም አካባቢ በሚገኙ ሁለት ኩሬዎች ውስጥ ሲሆን በእነዚህ ኩሬዎች 6 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል፡፡ በጀሞ የኮንዶሚኒየም ሳይት ለቤቶች ግንባታ ለሚውል ጠጠር ማምረቻ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ በተጠራቀመ የኩሬ ውሃ ደግሞ 3 ሴት ህፃናት ገብተው መሞታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል፡፡ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት 21 የውሃ አደጋዎች አጋጥመው የ8 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ፣ ዘንድሮ 15 አደጋዎች አጋጥመው የ14 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡  ዓምና ክረምት ላይ መንገድ ዳር በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ የሞተ ሰው እንደሌለ የጠቆመው የባለስልጣኑ ሪፖርት፤ ዘንድሮ በዓለም ባንክና በቱሉ ዲምቱ አካባቢ የ60 እና የ65 ዓመት አዛውንቶችን ጨምሮ 3 ሰዎች ጉድጓድ ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን ገልጿል፡፡ ክረምት ት/ቤት የሚዘጋበት ወቅት በመሆኑ ህፃናትና ታዳጊዎች ዋና ለመለማመድ በሚል ወንዝና ኩሬ ውስጥ እየሰመጡ የሚሞቱ ሲሆን ወንዝ ይዞ የሚመጣን ቁሳቁስ ለመለቃቀም ሲሞክሩም በውሃ የመወሰድ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ አቶ ኪዳነ ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ በተለይ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ወደነዚህ ቦታዎች እንዳይጠጉ በማድረግ አደጋውን መከላከል ያሻል ያሉት አቶ ኪዳነ፤ ጎርፍ አቅጣጫውን ስቶ ወደ መኖሪያ ቤቶች እንዳይገባም ቱቦዎችን  ከደረቅ ቆሻሻ መጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ማናቸውም የመንግስት አካላትም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ለተለያዩ ዓላማዎች የቆፈሩትን ጉድጓድ መልሰው እንዲደፍኑ ያሳሰቡት
የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ፤ ሁሉም ሃላፊነቱን በመወጣት አደጋውን መቀነስ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡  





Read 3109 times