Monday, 24 August 2015 09:28

ግብጽ የኢትዮጵያን ስጋ በቅናሽ ዋጋ ለመግዛት እየተንቀሳቀሰች ነው

Written by 
Rate this item
(12 votes)

      የግብጽ የአቅርቦትና የንግድ ሚኒስትር ካሊድ ሃናፊ፤ የኢትዮጵያን የስጋ ምርት አሁን ከሚሸጥበት ባነሰ ቅናሽ ዋጋ ለመግዛትና ለዜጎች ለማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት  እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ባለፈው ረቡዕ ማስታወቃቸውን ዘ ካይሮ ፖስት ዘገበ፡፡ግብጽ የኢትዮጵያን የስጋ ምርት በቅናሽ ዋጋ በመግዛት በቶጎና በሌሎች የምዕራብ አገራት ለሚገኙ ግብጻውያን ማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር ከሆኑት አቡ በከር አል ሃናፊ እና በቶጎ የግብጽ አምባሳደር ከሆኑት ሞሃመድ ከሪም ሸሪፍ ጋር መወያየታቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ግብጽ ከኢትዮጵያ ስጋ ለመግዛት ያሰበችበትን አዲሱን የቅናሽ ዋጋ በተመለከተ ሚኒስትሩ ያሉት ነገር ባይኖርም፣ በአገሪቱ ወቅታዊ ገበያ አንድ ኪሎ ስጋ ከ9.58 እስከ 11.1 ዶላር እየተሸጠ እንደሚገኝ ዘገባው ጠቁሟል፡፡ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በሁለቱ አገራት ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸውንና በወቅቱም የግብጽ ባለሃብቶች በአገራቱ መካከል ያለውን የኢኮኖሚና የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኙ ለአገራቱ መሪዎች መግለጻቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለሃብቶቹ የኢንዱስትሪ ዞን እንዲቋቋም ወይም የትራንስፖርት ወጪን የሚቀንሱና የኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰዱ መጠየቃቸውንም
አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3568 times