Monday, 24 August 2015 09:31

በሽብር የተከሰሱት የተቃዋሚ አመራሮች በነፃ ተሰናበቱ

Written by 
Rate this item
(14 votes)

    አቃቤ ህግ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል
    ከአንድ አመት በፊት በሽብር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 10 ተከሳሾች መካከል  የቀድሞ የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌውን ጨምሮ አራት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አንድ ሌላ ግለሰብ በቀረበባቸው ክስ ላይ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍ/ቤቱ ከትናንት በስቲያ በይኗል፡፡ ቀሪዎቹን 5 ተከሳሾች ይከላከሉ ብሏል - ፍ/ቤቱ፡፡ አቃቤ ህግ ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል፡፡
ፍ/ቤቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹን፡- ሀብታሙ አያሌው፣ የሸዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሺ እንዲሁም አብርሃም ሰለሞን የተባለውን ግለሰብ ነው በነፃ ያሰናበተው፡፡ ዘላለም ወ/አገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ሰለሞን ግርማ፣ ባህሩ ደጉና ተስፋዬ ተፈሪ የተባሉት ተከሳሾች ደግሞ ተከላከሉ ተብለዋል፡፡
አቃቤ ህግ፤ ግለሰቦቹ ከ2000 ጀምሮ ግንቦት 7 ከተባለ የሽብርተኛ ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች መረጃ በመለዋወጥ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአረቡ ዓለም የተከሰተውን አመፅ ለመተግበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማድረጋቸውንና ከሽብር ድርጅቱ የሚላክላቸውን ገንዘብ እስከመቀበል መድረሳቸውን በመጥቀስ ነው በአራት የሽብር ወንጀሎች ክስ የመሰረተባቸው፡፡የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ሀብታሙ አያሌው ላይ አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች፣ አንድ ሳምሰንግ
ሞባይል ስልክና ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተገኙ የተባሉ ተከሳሹ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ያስተላለፋቸው መልዕክቶችና የስልክ ልውውጦች ሲሆኑ የአቃቤ ህግ ምስክሩም በፍተሻ ወቅት ሳምሰንግ ሞባይል በቤቱ እንደተገኘና በስልኩ ውስጥ ምን እንዳለ እንደማያውቅ ለፍ/ቤት አስረድቷል፡፡ ፍ/ቤቱም ማስረጃዎቹንና ምስክሩን መርምሮ በሰጠው ብይን፤ ግለሰቡ ሳምሰንግ ሞባይል ብቻ መያዙ ሽብርተኛ አያስብልም ብሏል፡፡
በማስረጃነት የቀረቡትን ሰነዶችም የመረመረው ፍ/ቤቱ፤ ንግግር አድርጓል በሚል የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያስረዱት የአንድነት ድርጅት የመረጃ ኃላፊ መሆኑን ብቻ ነው በማለት ክሱ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያልተደገፈ በመሆኑ በነፃ እንዲሰናበት በይኗል፡፡ ሌላው ተከሳሽ የአንድነት ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ ዳንኤል ሺበሺም ሁለት ሳምሰንግ ሞባይል እንደተገኘበትና በሞባይሉ ውስጥ ምን እንዳለ አለማየታቸውን የአቃቤ ህግ ምስክሮች ማስረዳታቸውን የጠቀሰው ፍ/ቤቱ፤ ከብሔራዊ ደህንነት መረጃ የተገኘው ሰነድም
ክሱን በበቂ የሚያስረዳ አይደለም ሲል ግለሰቡን በነፃ አሰናብቷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሸዋስ አሰፋና የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታም በተመሳሳይ ሁኔታ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን፤ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ በተጨማሪ ሌላው ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞንንም ፍ/ቤቱ በነፃ አሰናብቷል፡፡ በነፃ ከተሰናበቱት ተከሳሾች መካከል ሀብታሙ አያሌውና አብርሃም ሰለሞን በሌላ ጉዳይ የማይፈለጉ ከሆነ ከሐሙስ ጀምሮ ከማረሚያ ቤት እንዲለቀቁ ፍ/ቤቱ ያዘዘ ሲሆን የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሺ ከዚህ ቀደም ፍ/ቤት በመዳፈር  እስከ 1 ዓመት ከ4 ወር በሚደርስ  እስራት የተቀጡ በመሆኑ ቅጣታቸውን ሲጨርሱ እንዲፈቱ በይኗል፡፡ ተከላከሉ በተባሉት 5 ተከሳሾች ላይ ፍ/ቤት ምስክሮቻቸውን ለመስማት ለህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡ የፍርድ ቤቱን ብይን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ስለሺ ፈይሣ፤ የፓርቲያቸው አመራር
አባል አቶ የሺዋስን ጨምሮ ፖለቲከኞቹ ነፃ መባላቸው ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ “አስቀድሞም እነዚህ ሰዎች ሽብርተኞች አልነበሩም፤ በሰላማዊ ትግል የሚያምኑ ሰላማዊ ታጋዮች ናቸው” ብለዋል፡፡
በእነ የሸዋስ ላይ ምንም ማስረጃ አልተገኘም መባሉ የተፈረደባቸው ሌሎቹ እስረኞች ማስረጃ ተገኝቶባቸዋል ማለት እንዳልሆነ አቶ ስለሺ አክለው ተናግረዋል፡፡ በነፃ ከተሰናበቱት የአንድነት አመራሮች ጋር በአንድ ካቢኔ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩት የፓርላማ አባሉ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ በሰጡት
አስተያየት፤ በፍ/ቤቱ ውሳኔ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እንዲህ ያሉ የፍ/ቤት ውሳኔዎችን ማበረታታት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡  መንግሥት በጀመረው መንገድ ሌሎች የህሊና እስረኞችንም መፍታት አለበት ብለዋል - አቶ ግርማ፡፡

Read 3716 times