Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 February 2012 12:16

“ዓምዱን ያለመተቸት መብትና ነፃነት የናንተ ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአሜሪካ - ህዝብ በመሪዎቹ ላይ ይቀልዳል!

በአፍሪካ - መሪዎች በህዝቡ ላይ ይቀልዳሉ!

አንድ የአሜሪካ የባህር ሃይል ወታደር ፔንታጐን ከርሞ ወደ ቤቱ እየተጓዘ ነበር - በመኪና፡ መንገዱ ከወትሮው በተለየ በትራፊክ ተጨናንቆ ጉዞው የኤሊ ሆኗል - መሳብ ብቻ!! ለየለትና የትራፊክ እንቅስቃሴው ከነአካቴው ተገታ፡፡ ባህር ሃይል ወታደሩ መኪና ውስጥ ተቀምጦ ሲቆዝም አንድ ፖሊስ ወደሱ አቅጣጫ እየገሰገሰ ሲመጣ ተመለከተ፡፡ አጠገቡ ሲደርስም ወታደሩ ችግሩ ምን እንደሆነ ፖሊሱን ጠየቀው፡፡ ፖሊሱም፤ “ወንድሜ ትልቅ ችግር ላይ ነን፤ ሚ/ር ቢል ክሊንተን ክፉኛ አዝነው መንገድ ዘግተው ቆመዋል፡ ለጠበቆቻቸው ያልከፈሉት የ33.5 ሚ. ዶላር እዳ እላያቸው ላይ አናጦባቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ቤተሰቦቻቸው ጥልት አድርገዋቸዋል፡፡ በእነዚህ ድርብርብ ችግሮችም የተነሳ እላዬ ላይ ነዳጅ አርከፍክፌ ራሴን በእሳት አጋያለሁ እያሉ ነው” ሲል አስረዳው፡፡

የባህር ሃይል ወታደሩ፤ “እና አሁን አንተ እዚህ ምን እየሰራህ ነው?”

ፖሊሱ፤ “ፕሬዚዳንቱ በጣም ስላሳዘኑኝ በየመኪናው እየዞርኩ እርዳታ እየጠየቅሁላቸው ነው”

ወታደር፤ “እስካሁን ምን ያህል አገኘህ?”

ፖሊሱ፤ “እስካሁን 33 ሊትር አግኝቼአለሁ፤ በጣም ብዙ ሰዎች ግን አሁንም ከመኪናቸው ላይ ነዳጅ እየመጠጡልኝ እንደሆነ መረጃ ደርሶኛል፡፡”

አይገርምም? እኔ እኮ ዕዳቸውን ሊከፍልላቸው የገንዘብ እርዳታ እያሰባሰበ መስሎኝ ነበር፡፡ ንግግሩ እንደዛ ይመስላላ! አቶ ፖሊስ ግን ፕሬዚዳንቱ ራሳቸውን የሚያጠፉበትን ነዳጅ ነበር የሚሰበስበው፡፡ መቼም በነፍስ ማጥፋት ወንጀል መጠየቁ አይቀርም! (አገሩ አሜሪካ እኮ ነው!)

ከላይ ተርጉሜ የተረኩላችሁ በአሜሪካው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ላይ የተፈጠረ ቀልድ የተገኘው ከኢንተርኔት ነው፡፡ ኢንተርኔት የፈጠረው ግን አይደለም፡፡ ራሳቸው አሜሪካውያን የፈጠሩትን ቀልድ ነው ኢንተርኔት ላይ የለቀቁት፡፡   እኔ እንግዲህ በራሴ ላይ በጣልኩት የሃሳብ ቁጥጥር (Self censorship) ብዙም ያልጨከነባቸውን ቀልድ መርጬ ነው እንጂ ፕሬዚዳንቱ ከሞቱ በኋላ ገነትና ሲኦል ደጃፍ ላይ በሚገጥማቸው ነገር ሁሉ ሳይቀር ይቀልዳሉ - አሜሪካውያኑ፡፡ (ሴንሰርሺፕ ያልነካው ነፃነት ማለት ይሄ ነው!) አያችሁ በአሜሪካና በአውሮፓ ህዝብ በመሪዎቹ ላይ ይቀልዳል፡፡ ባልታደሉት አፍሪካና በሦስተኛው ዓለም ደግሞ መሪዎች በህዝባቸው ላይ ይቀልዳሉ፡፡ እኛስ ግዴለም… ከሦስተኛው ዓለም ልንወጣ ትንሽ ነው የቀረን፡፡ ትንቢት ወይም ቅዠት እንዳይመስላችሁ! ሦስተኛው ዓለም የተባልነው “ኢኮኖሚያችን ሎው” በመሆኑ አይደል? (ባትሪ ሎው እንደሚባለው) እንደምንም በኢህአዴግ ወኔ ከድህነት ማጥ ወጥተን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ስንሰለፍ… ከሦስተኛው ዓለም ወጥተን ወደ ሁለተኛው ዓለም ከፍ እንላለን፡፡ ሁለተኛ ዓለም የሚባሉ አገሮች አሉ እንዴ? ኖሩም አልኖሩም ግን ከሦስተኛ አለም መውጣታችን አይቀሬ ነው፡፡ (ታዲያ ለኢህአዴግ ዕድሜ እንዲሰጠው ከፀለይን ብቻ ነው) ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን ሳይሆን ድህነትን ብቻ ለማጥፋት ቆርጦ መነሳቱን ለማወቅ ቀላሉ መንገድ ምን መሰላችሁ? ከላይ ላልኩት ነገር የሚሰጠውን አስተያየት መስማት ብቻ ነው፡፡ “ዕድሜ ተሰጠኝም አልተሰጠኝም ድህነትን ማጥፋቴ አይቀርም” ካለ… በቃ ያለጥርጥር ቃሉን ይፈጽማል ማለት ነው፡ (የግል መላምት ነው!)

እኔ የምለው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዴት አለፈ? በአሁኑ ጉባኤ ብንጐሳቆልም እንኳ አንድ መለሎ የሆነ ህንፃ ከቻይና አግኝተናል፡፡ (ይቅርታ ለካ ህንፃው የአፍሪካ ህብረት ነው) የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በመጣ ቁጥር ትዝ የምትለኝ አንድ ቀልድ አለች - እዚሁ ጋዜጣ ላይ ከጥቂት ዓመታት በፊት ያነበብኳት፡፡ በጉባኤው ሰሞን ነው አሉ፡፡ መሪዎቹ ሲመጡና ሲሄዱ “ፊትዎን ወደ ግንቡ ያዙሩ” የሚል ወከባ የደረሰባቸው እናት፣ መሪዎቹ ከመዲናዋ ጥንቅቅ ብለው እስኪወጡ ጠበቁና እንዲህ አሉ፤ “ሰዎቹን የሚከላከሏቸው ከጥይት ነው ከቡዳ?” (ወደ መሪዎቹ አትዩ ስለተባሉ እኮ ነው!) ከአፍሪካ ህብረት ሳንወጣ አንዲት ወዳጄ ታዝባ የነረችኝን ላካፍላችሁ፡፡ በየዓመቱ የህብረቱ ስብሰባ ሲካሄድ በኢቴቪ የሚቀርቡትን የተለያዩ ጥንታዊ የአፍሪካ አገራት ዘፈኖችን የተመለከተ ነው፡፡

ኢቴቪ አንድም አዲስ የአፍሪካውያን ዘፈን ማሳየት እንደተሳነው የተረዳችው ወዳጄ፤ “ምነው መሪዎቹ አንዳንድ የዘፈን ሲዲ እያመጡ ለኢቴቪ ቢሰጡት?” የሚል ገንቢ ጥቆማ ሰጥታኛለች፡፡ ጥቆማው ለኢቴቪ ይሁን ለመሪዎቹ ስላልገባኝ ፈልጌ እጠይቃታለሁ፡፡ እስከዛው ግን “የዓመቱ ምርጥ ትዝብት” ብየዋለሁ፡፡

እኔ የምለው ግን አዲሱ አፍሪካ ህብረት ህንፃ ግቢ ውስጥ የንክሩማህ ሐውልት ሲቆም ምነው የአባባ ጃንሆይ ሃውልት ተዘለለ? የተለመደችው የአህጉራችን የምርጫ መጭበርበር በጃንሆይ ሃውልትም ተደገመች ማለት ነው? (ጥያቄና ጥርጣሬ ነው) መቼም የአፍሪካ አባት በሚል የሚሞካሹት ንጉሱ፤ ሃውልታቸውን ለማስቆም የሚያበቃ ውለታ ለህብረቱ አልሰሩም ብሎ የሚክድ አፍሪካዊ አለ ብዬ አላምንም፡፡ (ህብረቱ ውለታቢስ እንዳይሆን ብዬ እኮ ነው!)

የሌሎችን ትዝብት ሳቀርብ የእኔን ትዝብ ዘነጋሁት አይደል፡፡ የስብሰባው ሰሞን (ባለፈው ሳምንት ማለቴ ነው) አንድ የኢቴቪ ጋዜጠኛ አሪፍ ዘገባ ሲያቀርብ ነበር፡ ሆቴሎችን፣ የጉባኤው ተሳታፊዎችንና ጋዜጠኞችን ሳይቀር አነጋግሯል፡፡ ይሄ የኢቴቪ ጋዜጠኛ የውጭ እንግዶችን በእንግሊዝኛ ሲጠይቅ (ለምዶበት ሳይሆን አይቀርም) “Ya men!...” እያለ ነበር የሚጀምረው፡ ወንዶቹን ቢሆን እናልፈው ነበር፡፡ ችግሩ ግን ሴቶቹንም ነበር “Ya men!” ሲላቸው የታዘብነው፡ መቼም የአሁኑማ አንዴ አልፏል፡፡ ለሌላው ጊዜ ይታሰብበት ለማለት ያህል ነው!

ስለጋዜጠኛ ካነሳሁ አይቀር ትችት ብቻ እንዳይሆን አንድ የአድናቆት አስተያየት እነሆ፡  በአዲስ አበባ መስተዳድር የቲቪ ፕሮግራም ላይ የሚቀርብ ቶክ ሾው ነው - “ዝክረ ሃሳብ” ይባላል፡ የዚህ ፕሮግራም አቅራቢ ጋዜጠኛ “ጥይት” ነው (የሚገድለው ግን አይደለም) ባለፈው ረቡዕ ምሽት የተከታተልኩት ውይይት “በመንግስት ፋይናንስ ላይ ያለውን የግልፅነትና የተጠያቂነት አሰራር” በተመለከተ የተዘጋጀ ሲሆን የአዲስ አበባ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎች ተሳትፈውበታል፡ ኢንተርቪው እንዳይመስላችሁ… “ግምገማ” አከል ውይይት ነው፡፡ የዚህ ጋዜጠኛ ልዩ ችሎታ ምን መሰላችሁ? የፈለገ ባለስልጣን ቢሆን የተጠየቀውን አድበስብሶ እንዲያልፍ አይፈቅድለትም - ያፋጥጠዋል፡  ሁሌም “እናጥራት” ባይ ነው፡፡

ለአንዳንድ የቤት ሥራቸውን ሰርተው ለማይመጡ የቢሮ ሃላፊዎችና ባለስልጣናት ላይመች እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ (አይመቻ!) በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ሃላፊዎች አንዱ ለምሳሌ እንዲህ አሉ “የተጀመሩ ነገሮች ጥሩ ናቸው፤ ግን በቂ አይደሉም” ተርቡ ጋዜጠኛ በዋዛ አላለፋቸውም (ያልፈጠረበትን!) “በቂ አይደሉም፤ በቂ አይደሉም ይባላል… ማነው በቂ የሚያደርጋቸው?” (“ተገቢው ጥያቄ ለተገቢው ሃላፊ” ይሏል ይሄ ነው) እንዴት አንጀቴን እንዳራሰኝ አልነግራችሁም፡፡

እኔ የመስተዳድሩ ቲቪ ሃላፊ ብሆን ኖሮ ይሄን ጋዜጠኛ የት እንደምልከው ታውቃላችሁ? ኢትዮ ቴሌኮም ሃላፊዎች ቢሮ፡፡ ከዚያም ለምን ሂሳብ ወደሞባይላችን አልገባ እንዳለ አፋጦ ይመጣልኛል፡ ያኔ ግልጽነትና ተጠያቂነት የምር ይሆኑ ነበር፡፡ እኔ የምለው ግን ኢትዮ ቴሌኮምም እንደ ኢህአዴግ ሆነ አይደለም እንዴ? በሌላ አነጋገር ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት መከላከል አቃተው አይደለም ወይ እያልኩ ነው፡ ኢህአዴግ እንኳ ቢያንስ ግለሂስ ያደርጋል፡፡ ቴሌኮም ግን “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ብሎ ክችች ነው፡፡

ወደ ቀጣዩ አጀንዳዬ ከመሸጋገሬ በፊት የሥራ ባልደረባዬ ያጫወተችኝን ወግ ላስቀድም፡፡ እሷም ወጉን የሰማችው ከአንዲት የቀድሞ የመንግስት ሃላፊ ነው፡፡ እንስቷ ሲጋራ አጫሽ ስትሆን በውጭ አገር የተማረችና ከዘመናዊ ሴቶች ተርታ የምትሰለፍ ዓይነት ናት፡፡ እቺ እንስት እንደነገረቻት፤ “ሲጋራ ማጨስ ክልክል ነው!” (No Smoking) “ባለማጨስዎ እናመሰግናለን!” ወዘተ የሚሉ አይነት ትዕዛዝ - አከል ማሳሰቢያዎች ያጨሳታል (ከሲጋራው የበለጠ) ይሄን በለጠፉ ካፌዎች እግር ጥሏት ከገባች አጭሳ እንደምትወጣ እርግጠኛ ናት፡፡ ለዚህች እንስት እንዲህ ያሉት የክልከላ (የገደብ) ማስታወቂያዎች የተጠቃሚን መብት የሚጋፉና ትህትና የጐደላቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ነው እልህ ውስጥ የምትገባው፡፡

እኔ ደሞ ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ካፌ ውስጥ ተለጥፎ ያየሁትና እስከ ዛሬም ትዝ ሲለኝ ንድድ የሚያደርገኝ አንድ ማስታወቂያ አለ፡፡ “ጋዜጣ ማንበብ ክልክል ነው!” የሚል፡፡ የፈለገውን ዓይነት አሳማኝ ምክንያቶች ቢደረደሩልኝ ከዚህ ማስታወቂያ ጋር ፈጽሞ እርቅ ልፈጥር አልችልም፡፡ ጋዜጠኛ ስለሆንኩ እንዳይመስላችሁ! ንባብን የሚከለክል ግለሰብም ይሁን ተቋም ጤና የጐደለው ስለሚመስለኝ ብቻ ነው፡፡

ወደ መጀመሪያው ወግ ልመልሳችሁ፡፡ የጠቀስኩላችሁ እንስት ለወዳጄ እንዳወጋቻት አውሮፓ ሄዳ አንድ ካፌ ውስጥ ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ ለየት ያለ ማስታወቂያ አንብባለች፡፡ “You have all the freedom not to smoke!” ይላል፡፡ በትህትና ሆነ እንጂ ባያጨሱ ደስ ይለናል እንደማለት ነው፡ ቁምነገሩም ያለው ትህትናው ላይ ይመስለኛል፡ እንስቲቱ ይሄን ማራኪ ማሳሰቢያ ካነበበች በኋላ ደስ ብሏት ሳታጨስ ከካፌው እንደወጣች ለወዳጄ አጫውታታለች፡፡

አሁን አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ እንስቷ በአውሮፓ ካፌ ባየችው ለየት ያለ የ”አታጭሱ” ማሳሰቢያ ለምን ተደመመች? ለእኔ እንደገባኝ ከሆነ በ”ፖዘቲቭ ቲንኪንግ” የተቃኘ በመሆኑ ነው፡፡ በእኛ አገር የለመድነው “ማጨስ አይቻልም!” “ማጨስ ክልክል ነው!” የሚሉትን ማስፈራሪያዎች ነዋ! በአውሮፓ እንስቷ አየሁት ያለችው ማሳሰቢያ ወደ አማርኛ በቀጥታ ሲመለስ “ሲጋራ ያለማጨስ መብቱና ነፃነቱ በሙሉ የእርስዎ ነው” እንደማለት ነው፡፡ ቀዳሚዎቹ ማሳሰቢያዎች በአሉታዊ ስሜት የተቃኙ ሲሆኑ ይሄኛው በአዎንታዊ (ቀና) ስሜት የተቃኘ ነው፡፡

ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ከዓመት በፊት “The secret” የተሰኘ መጽሐፍ ሳስቃኛችሁ ቀና አመለካከትን ማዳበር በህይወታችን ላይ የሚያሳድረውን አዎንታዊ ተጽእኖና ስኬታማ ለመሆን እንዴት እንደሚያግዘን ዳስሼላችሁ ነበር፡፡

መጽሐፉ እንደሚለው “ፖዘቲቭ ቲንኪንግን” ለማዳበር አስተሳሰባችንን ከመቀየር ባሻገር ለንግግር የምንጠቀማቸውን ቃላት በጥንቃቄ መምረጥ አለብን፡፡

ለምሳሌ ጠዋት ጠዋት ቢሮው እያረፈደ የሚገባ ሰው “ሁለተኛ አላረፍድም” በሚል ምሎ ከሚገዘት ይልቅ “ካሁን በኋላ በጊዜ ቢሮዬ እገባለሁ” ቢል ይሻለዋል- ይላል “The secret” የተባለው ራስን ማጐልበቻ መጽሐፍ፡፡ “መደህየት እጠላለሁ” የሚለውም አባባል ተመራጭ አይደለም፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ “መበልፀግ እፈልጋለሁ” በሚል እንድንተካው ትመክረናለች፡፡ እዚህ ላይ ኢህአዴግ ከ97 ምርጫ በፊት ተቃዋሚዎችን አስመልክቶ የተናገረውን መጥቀስ እንችላለን፡፡ “ጠንካራ ተቃዋሚዎች እንዲፈጠሩ እፈልጋለሁ” ሲል የማይታመን ተስፋ ሰጪ ንግግር ተናግሮ ነበር፡፡ ይሄን አዎንታዊ ስሜትን የሚያንፀባርቅ ዓ.ነገር ሊባል ይቻላል፡፡ ከ2002 ምርጫ በኋላ በኢህአዴግ ልሳን መጽሔት ”አዲስ ራዕይ” ስለተቃዋሚዎች የሰፈረው ደግሞ አሉታዊ ዓ.ነገር ተብሎ ሊፈረጅ የሚችል ነው፡ ለምን ቢሉ… “ተቃዋሚዎችን ዳግም እንዳያንሰራሩ ማድረግ” የሚል ስሜት የሚያንፀባርቅ ነበርና!

ለምሳሌ ኢህአዴግ “ድህነትን ተረት ባላደርግ ፓርቲ አትበሉኝ” ብሎ መነሳቱን እናውቃለን፡፡

ደራሲዋ ብትሰማው ኖሮ ግን በሚከተለው ዓ.ነገር እንዲተካው መወትወትዋ አይቀርም ነበር፡፡

“እዚህች አገር ላይ ብልጽግናን አሰፍናለሁ” በሚል፡ በተመሳሳይ መልኩ “ድንቁርናንና መሃይምነትን አጠፋለሁ” ከማለት ይልቅ “ዕውቀትንና ሥልጣኔን አስፋፋለሁ” መባል አለበት ባይ ናት - ደራሲዋ፡፡

በነገራችን ላይ ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች በሚያወጧቸው መግለጫዎች፣ መፈክሮች፣ ማሳሰቢያዎችና አንዳንዴም ማስጠንቀቂያዎች አዎንታዊ አንደምታ ያላቸውን ቃላትና ዓ.ነገሮች ሊጠቀሙ ይችላሉ (መብቱ የእነሱ ነው!) ለምሳሌ በሽብርተኝነት ዙሪያ ያለውን ስጋት ለተቃዋሚዎች መግለጽ ሲፈልግ “You have all the freedom not to engage in terririsom act!” ሊል ይችላል (በሽብርተኝነት ተግባር ላይ ያለመሳተፍ ሙሉ መብት አላችሁ እንደማለት ነው) ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የጋዜጠኞች ወይም የፖለቲከኞች መታሰር ስጋት ከፈጠረባቸው ለኢህአዴግ በሚያወጡት መግለጫ “You have all the freedom not to intimidate or detain Journalists and political activists” ማለት “መብታቸው” ነው (ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ ታጋዮችን ያለማስፈራራትና ያለማሰር መብት አለህ ይሉታል - ኢህአዴግን) ኢህአዴግም ደጋግሞ በተቃዋሚዎች ላይ የሚሰነዝረውን ማስጠንቀቂያ (ማስፈራሪያ) በአዎንታዊ መንፈስ ልንቃኘው እንችላለን፡፡

“ህገመንግስት በሃይል በመናድ ሥልጣን መያዝ አይቻልም” የሚለውን “ህገመንግስት በሃይል ባለመናድ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን የመያዝ መብት አላችሁ” በሚል መቀየር ይቻላል (ሙሉ መብቱ ግን የአድራጊው ነው!) ወደ ማህበራዊ ህይወትም ስንመጣ ነገሩ ይሰራል፡፡ ህገወጥ የዘፈን ሲዲዎች ህዝቡ እንዳይገዛ ግንዛቤ የሚፈጥር ማሳሰቢያ ማስተላለፍ የምንፈልግ ከሆነ “ህገወጥ ሲዲ የገዛ 100ሺ ብር ይቀጣል” ወይም “10 ዓመት ወህኒ ቤት ይከረቸማል” ከማለት ይልቅ “ኦሪጅናል ሲዲ ገዝቶ የማዳመጥ ሙሉ መብትና ነፃነት የናንተ ነው!” ቢባል የበለጠ ጆሮ - ገብ መልዕክት ይወጣዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እስካሁን የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች አዋጆችንና ህጐችን የሚመለከቱ እንዳልሆኑ ልጠቁም እወዳለሁ፡፡ ፕሮፖዛል ሆነው እስኪረቀቁም ተግባራዊ አይሆኑም፡፡

በመጨረሻ ለውድ አንባቢያን አንድ ማሳሰቢያ አለኝ:-

“ይሄን መጣጥፍ ካነበባችሁ በኋላ ያለመተቸት መብትና ነፃነቱ የናንተ ብቻ ነው!!” መብትና ነፃነት የሚሰፋበት ብሩህ ዘመን ከች እንዲልልን እመኛለሁ! (በምኞት አይሆንም ብባልም አልሰማ አልኩ አይደል?)

 

 

Read 4280 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:20