Monday, 24 August 2015 09:29

“ዲሞክራሲያዊ ወይም ልማታዊ ዘረኝነት”፣ “አገራዊ ወይም ነፃ አውጪ ዘረኝነት” ... የዘረኝነት መልኮች

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(16 votes)

.  የዘረኝነት ወረርሽኝ ለኢትዮጵያ አስፈሪ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። እርስበርስ፣ “አንተ ነህ ዘረኛ”፣ “አንቺ ነሽ ዘረኛ” እያሉ ይወነጃጀላሉ። ብዙዎቹ የሚያቀርቧቸው አማራጮች ግን፣ በቅፅል ብቻ የሚለያዩ የዘረኝነት መልኮችን ነው።
.   ኢህአዴግ፣ ተቃዋሚዎቹን ያወግዛል - “የሁለት ተማሪዎችን ፀብ፣ የብሔረሰብ ፀብ አስመስለው ያራግባሉ” በማለት። ተጠያቂዎቹ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሆኑ፣ ስልጣን ላይ ከሃያ አመት በላይ የቆየ ፓርቲ፣ ይህን በሽታ ማቃለል ለምን አቃተው?
.   በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ኢህአዴግን ይኮንናሉ - “የብሄረሰብ ፖለቲካን አስፋፍቷል፤ የቀበሌ መታወቂያ ላይ ይመዘግባል” በማለት። ግን፣ ኢህአዴግ ስልጣን ባልያዘበት በአሜሪካ፣ በዳያስፖራ ፖለቲካና በፌስቡክስ ዓለም ለምን ዘረኝነት ገነነ?
.   በዚህ መሃል ግን፣ የዘረኝነት ወረርሽን ከአመት አመት እየተባባሰ፣ አገሪቱ እየተንሸራተተች ናት።    
   ምንም እንኳ፣ ኢትዮጵያ በብዙ አይነት የጥፋት ፈተናዎች ውስጥ፣ ህልውናዋን ሙሉ ለሙሉ ሳታጣ ያለፈች አገር ብትሆንም፣ የበርካታ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ዝንባሌን ስትታዘቡ፣ የበርካታ ምሁራንና ዜጎች አዝማሚያ ስትመለከቱ... ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ፣ የዚህች አገር ነገር፣ተስፋ ያስቆርጣል። ከአመት አመት፣ የዘረኝነት ወረርሽኙ እየባሰበት፣ አገሪቱ ወደለየለት የጥፋት አዘቅት እንዳትሰምጥ አትሰጉም? በእርግጥ፣ አልፎ አልፎ፣ የዘረኝነት በሽታው፣ ለአፍታ ጋብ ሲልለት... እሳቱም ትንሽ ሲበርድለት እያየን፣ የእፎይታና የተስፋ ስሜት እናገኛለን። ግን፣ እፎይታው ብዙም አይቆይም። እንደገና በሽታው ያገረሸበታል። ማገርሸት ብቻ አይደለም። ከእያንዳንዱ እፎይታ በኋላ፣ ወረርሽኙ ባገረሸ ቁጥር፣ ከቀድሞው እጅጉን ብሶበት እናገኘዋለን። ተስፋ አስቆራጩና አስፈሪው ነገር ደግሞ ምን መሰላችሁ? የዘረኝነት ወረርሽኙን ለማስቆም የሚያስችል፣ አስተማማኝ መላ ምን እንደሆነ በግልፅ ጎልቶ አለመታየቱ ነው። ዙሪያው ሁሉ በጨለማ የተዋጠ ጉዞ ይመስላል።
የዘረኝነት ወረርሽኝ፣ ተስፋ አስቆራጭና አስፈሪ የጨለማ ጉዞ የሚሆነው፤ ነገሩ ያን ያህል ውስብስብ ጉዳይ ስለሆነ አይደለም። ሰሞኑን ጠ/ሚ ኃይለማሪያም  ደሳለኝ፣ የተናገሩትን መጥቀስ ይቻላል። በተለይም፣ በዩኒቨርስቲዎች የሚታየው የዘረኝነት አስተሳሰብ አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል።
አንድ የአማራ ተወላጅና አንድ የኦሮሞ ተወላጅ፣ ወይም አንድ የትግራይና አንድ የሶማሌ ተወላጅ ... በሆነ ምክንያት ቢጣሉና ቢደባደቡ፤ “አማራና ኦሮሞ ተደባደቡ”፣ “ትግሬና ሶማሌ ተጣሉ” ተብሎ ይራገባል። እንዲህ፣ የዘረኝነት አስተሳሰብ፣ በየቦታውና በየጊዜው መስፋፋቱ፣ በተለይም በዩኒቨርስቲዎች መባባሱ አሳሳቢ እንደሆነ የተናገሩት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፤ አንዴ ከእጃችን ካመለጠ፣ የጥፋት መዘዙ መመለሻ የለውም ብለዋል። ማብቂያ ወደሌለው የጥፋት እሳት የገቡ አገራት፣ ምንኛ እንደተንኮታኮቱ ማየት እንደሚቻልም ጠቅሰዋል - አቶ ኃይለማሪያም። ትክክል ብለዋል። “ታዲያ፣ ይሄ ከኢህአዴግ የብሄረሰብ አደረጃጀት ጋር እንዴት ይሄዳል?” የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።  አዎ አይሄድም። ነገር ግን፣ የዘኝነትን ምንነት የገለፁበት አነጋገር ትክክለኛ ነው።
የሁለት ሰዎች ፀብም ሆነ ወዳጅነት፣ ድብድብም ሆነ ጋብቻ፣ ዝርፊያም ሆነ ግብይት... በቃ የሁለት ሰዎች ድርጊትና ፍላጎት ነው። የሚወገዝ አልያም የሚደነቅ ከሆነም፣ አድናቆትና ውግዘቱ፣ ከእነዚሁ ሰዎች ውጭ መዝለል የለበትም። ማለትም... ነገርዬም፣ የዘር ፀብ ወይም የዘር ወዳጅነት አይደለም። የጎሳ ድብድብ ወይም የጎሳ ጋብቻ አይደለም - የሆኑ ሰዎች ናቸው የሚደባደቡት ወይም የሚጋቡት። የብሄረሰብ ዝርፊያ ወይም የብሄረሰብ ግብይት አይደለም - የሆኑ ሰዎች ናቸው የሚዘርፉት ወይም የሚገበያዩት።
የተደባዳቢዎቹ ወይም የተጋቢዎቹ ቁጥር፣ የዘራፊዎቹ ወይም የገበያተኞቹ ቁጥር... አስር፣ ከዚያም አልፎ መቶና ሁለት መቶ፣ ወይም እልፍና ሚሊዮን ቢሆን እንኳ፣ እውነታውን አይቀይረውም። “የዘር፣ የብሄር፣ የጎሳ” ጉዳይ አይደለም። ተፈፅሞ ሊሆን አይችልም። ለምን?
በቃ፣ የሰው ተፈጥሮ እንደዚያ አይደለም። የጋራ የሆነ (የብሄረሰብ ወይም የጎሳ) አንጎልና አእምሮ የለም። ኖሮም አያውቅም። እውቀትና አስተዋይነት፣ አልያም ጭፍን እምነትና ስሜታዊነት... በዘር አይወረስም። የጋራ እጅ እና አፍ የለም። የብሔረሰብ፣ የጋራ ረሃብና ጥም የለም። ለብሔረሰብ፣ “መጉረስ” እና “መጎንጨት” ብሎ ነገርም የለም። እያንዳንዱ ሰው፣ የተመገበውንና የጠጣውን ያህል ነው፤ የእያንዳንዱ ሰው ረሃብና ጥም የሚቃለለው። የብሔረሰብ ወይም የጎሳ፣ “የጋራ አካል” የለማ። ከሁሉም በላይ ግን፣ የጋራ አንጎል ወይም የጋራ አእምሮ የለም። ይህንን መካድ ነው፤ ዘረኝነት ማለት። ያን ያህል ውስብስብ ጉዳይ አይደለም።
ብዙ መራቀቅና ርቆ መጓዝም አያስፈልግም። በወንድማማቾች፣ በእህትማማቾችን ወይም በእህት ወንድሞች መካከል፣... የእውቀት፣ የአስተዋይነት፣ የዝንባሌ፣ የፍላጎት፣ የድርጊት ልዩነትን ማየት በቂ ነው። “እህቴ ታዋቂ ሃኪም ናት” የሚል ማስረጃ ብቻ በማቅረብ፣ ወንድሟ፣ የሃኪምነት ሙያንና ማዕርግን ማግኘት አለበት እንዴ? እንደ እህቱ መማርና ማጥናት ይቅርና፣ እግረመንገድ ስለ ሰውነት ክፍሎች ልታስረዳው ከሞከረች፣ ራስምታት የሚነሳበት ሰው፣ እንዴት ሃኪም ነኝ ይላል? አዎ፣ ይችላል - እውቀትና ሙያ፣ በዘር የሚተላለፍ ከሆነ።
በተቃራኒው፣ ወንድሟ የራሱን ሕይወት ቢያጠፋ ደግሞ አስቡት። “ሞትና ሕይወት የጋራ ስለሆነ፣ እህት ወንድሞቹንም እንቅበራቸው” እንላለን እንዴ? ማንነት የጋራ ከሆነ ግን፣ የግድ ነው።
“እህትሽ፣ ለትዳሯ ታማኝ አይደለችም” በሚል ሰበብ፣ ሚስቱን የሚፈታ ሙሽራንም አስቡት። “ቅድመ አያትህ፣ ቤተሰባቸውን ጥለው እንደጠፉ ሰምቻለሁ” ... በሚል ምክንያት፣ ከባሏ ጋር የምትፋታ ሙሽሪትስ? ተጠያቂነት በዘር የሚወረስ ከሆነ፤ ይሄም የግድ ነው።
ዘረኝነት፣ የዚህን ያህል የለየት እብደት ቢሆንም፣ በሩቅ በሩቅ ዝምድና ይቅርና፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳ የማይሰራ ቢሆንም፣ የዘረኝነትን አባዜ በቀላሉ አሽቀንጥረን ለማስወገድ አልቻልንም። አስገራሚ ነገር ነው። ጭራሽ፣ በዝምድና የሚገናኙ መሆን አለመሆናቸው የማይታወቁ ሰዎችን (የአንድ ብሔረሰብ ተወላጆችን) በጅምላ እንፈርጃለን። ይሄም አልበቃም። ጭራሽ፣ ከመቶ ዓመት በፊት፣ ... ከአምስት መቶ ዓመት በፊት፣ ከሚሌኒዬም በፊት የነበረ ንጉስና አልጋ ወራሽ፣ ወይም ደጃዝማቾችና ፊታውራሪ፣ አልያም ሰባኪና ፀሃፊ፣ ሽፍታና ዘራፊ... እየጠቀስን፣ አሁን በሕይወት ያሉ ሰዎችን፣ የጥፋትና የበደል ወራሽ እንዲሆኑ በዘር እየፈርጅንና እያቧደንን፣ አገሩን ቀውጢ ስናደርግ ይታያችሁ? እብደቱ፣ በሽታውና ወረርሽኙ የዚህን ያህል ከፍቷል።
ተስፋ አስቆራጩ ነገር፣ ... የጥንት ሰዎችን ድርጊትና ንግግር እየጠቀሱ ዘረኝነትን ማራገብ፣ እንደ ክፉ እብደት ሳይሆን እንደ አዋቂነት ሲቆጠር ታያላችሁ። ደህና ጤናማ የሚባሉ ሰዎች እንኳ፣ “ይሄ ታሪክ እውነት ነው ወይስ ሃሰት?” እያሉ ከመጠየቅ ያለፈ ነገር አያደርጉም። ከአምስት መቶ አመት በፊት፣ “እውነትም፣ እገሊት እንደዚያ ተናግራ ቢሆን፣ እገሌም ያኔ እንዲያ የፈፀመው ድርጊት ቢኖር”... አሁን በሕይወት ካሉ ሰዎች ጋር ምን አገናኘው? በአምስት መቶ አመታት ርቀትና ከሃያ የትውልድ ሃረግ ቆጠራ በኋላ ይቅርና... ያኔ ከአጠገባቸው የነበሩ የቤተሰብ አባላት እንኳ፣ ተጠያቂ ወይም ተሸላሚ መሆን የለባቸውም - በእህታቸው ንግግር ወይም በወንድማቸው ድርጊት። በየፊናቸው የተናገሩትና ያደረጉት ነገር ካለ፣ እንደ የስራቸው እንመዝናቸዋለን እንጂ። ጭራሽ፣ የምዕተዓመት ታሪክ እየጠቀሱ፣ ሰዎችን በዘር ለማቧደን መሞከር ግን... በቃ ልዩ በሽታ ነው።
ለነገሩ፣ የምዕተ ዓመታት ታሪክ እየጠቀሱ፣ “የዘር ወዳጅነት፣ የብሄረሰብ መፈቃቀር...” ለመፍጠር መከራቸውን የሚያዩም አሉ። የዘር ጥላቻን ወይም የብሄረሰብ ፀብን መስበክ ዘረኝነት የመሆኑን ያህል፣ የዘር መፈቃቀርን ወይም የብሄረሰብ ወዳጅነትን መስበክም... ያው ዘረኝነት ነው። ለዚህም ነው፣ “የብሄረሰብ ወዳጅነትን እናስፋፋለን” ብለው፣ ብዙ ታሪክ እየጠቀሱ ከምር የሚጣጣሩ ሰዎች፣ ቅንጣት ታህል ሲሳካላቸው የማናየው። ምኞታቸው ቀና ቢሆንም፣ በአላዋቂነት፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን ለማስፋፋት እያገዙ እንደሆኑ አይገነዘቡትም። የዘር ወዳጅነት የሚኖር ከሆነ፣ የዘር ጥላቻም ይኖራል። የጋራ ጉርሻ ካለ፣ የጋራ ረሃብም ይኖራል። መፈቃቀርን ለማስፋፋት፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን መስበክ አያዋጣም። እናም፣ የዘረኝነት ወረርሽኝን ለመከላከል የምናቀርባቸው “ቀና ሰዎች”፣ ከዚህ ያለፈ አቅም ከሌላቸው፣ ከአመት አመት ዘረኝነት ሲባባስ ማየታችን እንዴት ይገርማል?
በበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ የሚስተዋል ሌላ አዝማሚያም እንዲሁ ተስፋ ሰጪ አይደለም። ከፊሎቹ፣ እንደ ኢህአዴግ፣ በብሄረሰብ ቅኝት የተደራጁ ስለሆነ፣ ዘረኝነትን ከማስፋፋት በስተቀር፣ የዘረኝነት ወረርሽኝን ለማብረድና ለመግታት ይረዳሉ ብሎ ማሰብ፣ ከጭፍን ምኞት የተለየ ትርጉም አይኖረውም። እንደማንኛውም ሰው አስተሳሰባቸውን እያስተካከሉ እንዲሻሻሉ መመኘት ነው የሚሻለው።
“በብሔረሰብ ቅኝት መደራጀት ተገቢ አይደለም” የሚሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ?
አንዳንዶቹ፣ የብሔረሰብ ወይም የጎሳ ዘረኝነትን፣ በ“አገራዊ ዘረኝነት” ለመተካት የሚሟሟቱ ናቸው። በትክክለኛው አሰያየም፣ “ብሔረተኛ” (nationalist) በሚል ልንጠራቸው እንችላለን። “የግል ማንነት” በማጣጣል፤ “አገራዊ ማንነት ይቅደም” ይላሉና። “ኢትዮጵያዊነት” እና “አንድነት” የሚሉ መፈክሮችን ከሚያዘወትሩ ከእነዚሁ ፓርቲዎች መካከል ብዙዎቹ፣ “አገር ትቅደም” የሚሉ ብሔረተኞች ቢሆኑም፣ በተደጋጋሚ እንዳየነው ግን፣ “ብሔር ብሔረሰብ ይቅደም” በሚሉ ፓርቲዎች ይዋጣሉ። ለምን? የግል ማንነትን ሲያጣጥሉና ሲያሳንሱ፣ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፣ “ዘረኝነትን” ስለሚያጠናከሩ ነው። “አገራዊ የጋራ ማንነት፣ አገራዊ የጋራ አእምሮና ህልውና” ካለ፤ “ብሄረሰባዊ የጋራ ማንነት፣ ጎሳዊ የጋራ አእምሮና ህልውና” ለምን አይኖርም? ለዚህ ጥያቄ፣ አሳማኝ ምላሽ ሊያቀርቡ አይችሉም። እናም፣ “አገራዊ ዘረኝነት”ን ለማስፋፋት በተጣጣሩ ቁጥር፣ በዚያው መጠን “ብሔረሰባዊ ወይም ጎሳዊ ዘረኝነትን” ለማስፋፋት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ - አውቀውም ይሁን ሳያውቁ። ይሄ የአንዳንዶቹ ዝንባሌ ነው።
ሌሎቹ ደግሞ፣ “አገራዊ ማንነት ይቅደም” የሚል መፈክር ቢይዙም፤ ለጊዜው፣ ብዙውን ሕዝብ ለተቃውሞ ለማነሳሳት፣ “የብሄረሰብና የጎሳ ማንነት” የሚል የዘረኝነት ስሜትን ለመቀስቀሻነት ለመጠቀም ይሞክራሉ። በእርግጥ፣ የዘረኝነት ስሜትን የሚያራግቡት፣ “ለጊዜው ነው”፣ “ድል እስክናደርግ ድረስ ነው”፣ “ስልጣን ለመያዝ ያህል ብቻ ነው”... በማለት ራሳቸውን ያታልላሉ። ወይ ጉድ! ኢህአዴግም፣ “የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ”፣ ጊዜያዊ መሳሪያ ነው እንደሚል አያውቁም? እንዴት ላያውቁ ይችላሉ? የህገመንግስት መግቢያ ላይ በፅሁፍ አስፍሮታል። ዘላቂው አላማዬ፣ “አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ መፍጠር ነው” ይላል።
ለነገሩ፣ ኢህአዴጎች በፈርቀዳጅነት የሚያሞግሱት፣ “ዋለልኝ መኮንን”ም ከዚህ የተለየ ነገር አላለም። በ1960ዎቹ ዓ.ም፣ በዩኒቨርስቲ ኮሙኒስት ተማሪዎች ዘንድ፣ ጎልተው ከወጡት “ጀብደኛ መሪዎች” መካከል አንዱ የሆነው ዋለልኝ መኮንን፣ በብሔረሰብ ስም የተመሰረቱ ድርጅቶችንና ፓርቲዎችን መደገፍ አለብን በማለት ባቀረበው ፅሁፍ ነው እጅጉን የገነነው። መገንጠል የሚፈልጉ ድርጅቶችን ጭምር መደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ በትጥቅና በስንቅ ማገዝ እንደሚያስፈልግ የገለፀው ዋለልኝ፣ የዚህ አስፈላጊነት ግን “ለጊዜው” ያህል ብቻ እንደሆነ ያስረዳል። ማለትም... ሕዝብን በስሜት ለማነቃነቅና መንግስትን ለማዳከም። ለጊዜው? ከጊዜ በኋላስ? ከዚያ በኋላማ፣ ግንባር ቀደሙ ኮሙኒስት ፓርቲ ስልጣን ሲይዝ፣ የብሄረሰብ ድርጅቶች እንደሚከስሙ ይገልፃል - ዋለልኝ። የዋለልኝ አድናቂዎች፣ ይህንን አስተሳሰብ፣ “ዲሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት” ብለው ይጠሩታል። “ልማታዊ ብሄረተኝነት” ሲሉትም ያጋጥማል። ዋነኛው የዋለልኝ አድናዊ፣ ኢህአዴግ መሆኑን አትርሱ። በሌላ በኩልስ?
“ኢህአዴግ፣ ዘረኝነትን አስፋፍቷል” ብለው የሚያወግዙና፣ “ለጊዜው የዘረኝነት ቅስቀሳዎችን ብናካሂድ፣ ኢህአዴግን ለማዳከም ይጠቅመናል” ብለው የሚያስቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ? “ነፃ አውጪ፣ የአገራዊነት ጠበቃና የአንድነት ሃይል ነን” ሊሉ ይችላሉ። ግን፣ አስተሳሰባቸው፣ ከኢህአዴግና ከዋለልኝ በምንድነው የሚለየው?
“ዲሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት”፣ “ልማታዊ ብሔረተኝነት”፣ “አገራዊ ብሔረተኝነት”፣ “ነፃ አውጪ ብሔረተኝነት”... በሚሉ ስያሜዎች መካከል፣ የቅፅል ልዩነት መኖሩ እውነት ቢሆንም፣... “ለጊዜው ብቻ ነው”፣ “ለመሸጋገሪያነት ያህል ነው” የሚሉ ማመካኛዎችን ቢለጠፉም፤ የሁሉም መዘዝ ተመሳሳይ ነው - የዘረኝነት ጥፋት። አንዳንዴ የኢትዮጵያ ነገር፣ ተስፋ አስቆራጭ ይመስላል የምለውም በዚህ በዚህ ምክንያት ጭምር ነው።                    

Read 3882 times