Monday, 24 August 2015 09:44

“የኪስ ቦርሳዬ እንደ ሽንኩርት…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ለጿሚዎች እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ፡፡
በልክ ይበላማ!
እኔ የምለው…. በፍልሰታ ጾም መያዣ ዋዜማ  አዲስ አበባ የእውነትም የጉድ አገር ሆና ነበር። የምር እኮ… በተለይ ወደ ማታ ላይ ትልቅም ሆነ አነስ ያለ ምግብ ቤት ገብታችሁ ዘና ብሎ መብላት ብሎ ነገር የለም፡፡ ገና የመጨረሻዋን ጉርሻ ከሳህን አንስታችሁ ሳትጨርሱ አሳላፊ መጥቶ ይወስደዋል። ቦታ እስኪለቀቅለት የሚጠብቅ ሰው መአት ነበራ! የታወቁ ክትፎ ቤቶች ገና አንድ ሰዓት ሳይሞላ “ክትፎ አለቀ…!” የተባለበት ቀን ነበር፡፡
የምር ግን…አለ አይደል…ትርጉም ያላቸው በዓላት ትርጉማቸውን ሲያጡ የሆነ የሚበላሽባችሁ ነገር አለ፡፡
ይቺን ስሙኝማ…አዲስ አስተናጋጅ ነች አሉ። ብዙም ስለ ምግብ ቤት አታውቅም፡፡ እና የሆነ ተመጋቢ ይገባል፡፡
“ጌታዬ ምን ልታዘዝ?” ትላለች፡፡ እሱም..
“መጀመሪያ ሜኑውን ላንብበው…” ሲላት ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ጌታዬ ለማንበብ ከፈለጉ ወደ ላይብረሪ ቢሄዱ ጥሩ ነው…” ብላው አረፈች፡፡
ስሙኝማ…የአስተናጋጅ ነገር ካነሳን አይቀር፣ ነገሬ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ምግብ ቤቶች አሳላፊዋ የ‘በያይነቱ’ን ትሪ አንዴ ከወረወረችላችሁ በኋላ ብቅ ማለት ዘበት ነው… በእሷ ቦታ የበቀደሞቹን የአማሪካን ውሾች የሚያክል ድመት ስምንት ጊዜ ይመላለሳል፡፡
የምር ግን… በመቶ ‘ፐርሰንት’ የባንክ ብድር ምግብ ቤት ልከፍት ካሰብኩ የትም አፈላልጌ ነው የማገኛት፡፡ አሀ…ምን የሚያካክሉት ካፌዎች እንኳን ልክ ‘ባለማጨስዎ እናመሰግናለን’ እንደሚባለው ‘ጋዜጣ ባለማንበብዎ እናመሰግናለን’ ብለው እየለጠፉ አይደል! ስለዚህ ገብቶ “ምንቸት አብሽ…” “ቋንጧ ፍርፍር…” እያለ ይዘዝ እንጂ “ሜኑ ላንብብ…” ቅብጥርስዮ የሚባለው…የእኔ ምግብ ቤት የንባብ ባህል ማዳበሪያ ነው፡፡  ቂ…ቂ…ቂ…
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የምግብ ቤት ባለቤቶቹ ችግር ቢገባኝም  “ጋዜጣ ማንበብ ክልክል ነው…”  “ከእኩል ሰዓት በላይ ማንበብ ክልክል ነው…” ምናምን የሚሉ ማስታወቂያዎች ስታነቡ አታዝኑም!  ለነገሩማ… አንዳንዱ እኮ አንዲት ስኒ ሻይ ይዞ ከቁርስ እስከ ምሳ ሰዓት ተቀምጦ (የ‘ጨዋ’ ቃል ለመጠቀም ያህል!) የሚውለውን ስታዩ ባለቤቶቹስ ምን ያድርጉ ያሰኛችኋል።
ስሙኝማ…የበዓል ነገር ካነሳን አይቀር…‘የበዓል መንፈሳችን’… አለ አይደል… “ከአፍሪካ አንደኛ፣ ከዓለምም አንደኛ” ምናምን ነገር ቢባል አይገርምም።
ዘንድሮ እኮ የአብዛኞቹ በዓላት ‘ዋዜማ’ የሚጀምረው ገና ሁለት ሳምንትና ከዛ በላይ ሲቀረው እየሆነ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ይኸው “እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህ/ሽ…” መባባል ጀምረን የለ!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በዓል ሲቃረብ በማስታወቂያውም፣ በ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ነገርዬውም ‘ታዋቂ ሰዎች’ ቴሌቪዥናችንን መሙላታቸው አይቀርም፡፡ እንኳንም ‘ታዋቂ’ ሆኑልንማ!
እኔ የምለው…የ‘ታዋቂነትን’ ነገር ካነሳን አይቀር…እዚህ አገር እኮ የራስን ታሪክ ‘ለመከለስ’… አለ አይደል… ‘ታዋቂ’ መሆንን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ልክ ነዋ…ታሪካችሁን በፈለጋችሁ መንገድ ለመተርክ ‘መብቱ’ አላችኋ!
“ገና የኔታ ዘንድ ሀ ሁ መቁጠር ሳልጀምር ጀምሮ ነው ኖቤል ሽልማትን የማግኘት ምኞት ያደረብኝ…” ሲባል “ወራጅ አለ…” “የረገጣዎች ሁሉ እናት!” “ለምን ይዋሻል!” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም የእኔ ቢጤው ጥያቄ አቅራቢ… “ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ኖቤል ሽልማትን በማሸነፍ ፍቅር የተነደፈ…” ምናምን ብሎ ያሳምረዋል፡፡
‘ታዋቂው’ የፊልም ተዋናይ…እንዴት ‘የፊልም ፍቅር’ እንዳደረበት ሲናገር…“ልጅ እያለን አባታችን ሁልጊዜ የዲቪዲ ፊልም እየያዘልን ይመጣ ነበር…” ምናምን ነገር ይላል፡፡
አባትየው እኮ አይደለም የዲቪዲ ፊልም ይዘው ሊመጡ…ቴሌቪዥን ከጥቁርና ነጭ ወደ ቀለም መለወጡን ሳያውቁ ነው ከዚህ ዓለም የተሰናበቱት፡፡
ስሙኝማ…የዚህ አገር የ‘ታዋቂነት’ ነገር ምን ደስ ይልሀል አትሉኝም… አብዛኞቹ ‘ታዋቂ’ ሰዎች ታዋቂ እንደሚሆኑ የሚያውቁት ገና የተወለዱ ዕለት ጀምሮ ይመስላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
“ልጅ እያለሁ ጀምሮ አንጀሊና ጆሊን መሆን እመኝ ነበር፡፡” ይሄኔ እኮ… አለ አይደል…እሷ ‘ልጅ እያለች’ አንጀሊና ጆሊ ትወና አልጀመረችም!
‘ታዋቂው’ ፖለቲከኛ (‘ታዋቂ ፖለቲከኛ’ ምን ማለት ነው!) ነው የሚባለውም…“ከልጅነቴ ጀምሮ የሰው ጥቃት ማየት አልወድም፡፡ ማንም ሰው ሲጠቃ ሲያይ ቀድሜ የምገባው እኔ ነኝ…” ይላል፡፡ ከትንሹም ከትልቁም እየተጋጨ ወላጆቹ በየሦስት ቀኑ ቀበሌ ይጠሩ ነበር፡፡ እናላችሁ…ታዋቂ መሆን አሪፍነቱ…ባዮግራፊን ‘ኤዲት’ ማድረግ ይቻላል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በአሁኑ ጊዜ “ሀብት ከማግኘቴ በፊት ሳምቡሳ እሸጥ ነበር…” ምናምን የሚሉ ሰዎች መሰማት ናፍቆናል፡፡ የምር…ልክ ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ ‘አፉ ውስጥ የብር ማንኪያ ጎርሶ’ የተወለደ ይመስል…“ይገርምሀል ነፍስ ከማወቄ በፊት እንኳን የቢዝነስ ችሎታው ነበረኝ…” ይባላል፡፡
‘ታዋቂው’ የሆቴል ቤት ባለቤትም…“ገና ልጅ እያለን ሁልጊዜ ትልቅ ሆቴል እንገባ ስለነበር በሆቴል ሥራ የመሰማራት ሀሳቡ ነበረኝ…” ይላል፡፡ እሱዬው ልጅ እያለ እኮ አይደለም ትልቅ ሆቴል…ነስሩ ፓስቲ ቤት የገባበት ጊዜ እንኳን በጣት የሚቆጠር ነው፡፡ ልክ ነዋ…ታዲያ እንዲህ አይነት ‘ኤዲቲንግ’ አለ እንዴ!
“አበባየሁ ወይ…” ከሚጨፍሩ ልጆች ጋር ታይተሻል እየተባለች ‘ቀሚስ ተገልቦ’ ስትጠበጠብ የነበረችው ‘ታዋቂ’ ዘፋኝ… “ልጅ እያለሁ ጀምሮ ድምጻዊ እንድሆን ቤተሰቦቼ ከፍተኛ እገዛ አድርገውልኛል…” ማለት ነው፡፡
እናላችሁ…‘ታዋቂ’ ሆናችሁ፣ ወይንም “ታዋቂ ነኝ ብላችሁ አስባችሁ…” ለቃለ መጠይቅ ከቀረባችሁ…ብልጥ መሆን ነው፡፡ አንድ ሲንግል ለቆ… “የዘፈን ችሎታ እንዳለህ ያወቅኸው መቼ ነው?” ሲባል… “ገና ስወለድ ለቅሶዬ በዜማ ነበር አሉ…” ማለት ነው ልክ ነዋ፡፡
“የስነጽሁፍ ፍቅር ያደረብህ መቼ ነው?” ሲባል… አለ አይደል… “ገና አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላኝ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፉን ይዤ አልለቅም ብዬ አለቅስ ነበር…” ማለት ነው፡፡  
ዘፋኝ ነው አሉ፡፡ እና የሆነች ከተማ ኮንሰርት ለማቅረብ ይሄዳል፡፡ ክፍያውን ከፍ ለማድረግም ለአዘጋጁ ምን ይለዋል…“እዚሀ ከተማ ሁሉም ሰው ያውቀኛል፡፡”
ታዲያላችሁ…ኮንሰርቱ ላይ ሦስት ሰዎች ብቻ ይመጣሉ፡፡ አዘጋጁም ይናደድና…
“ምን አይነት ውሸታም ነህ!” ይለዋል፡፡
“ምን አደረግሁ?”
“ሰዉ ሁሉ ያውቀኛል አላልክም እንዴ!  ሦስት ሰው ብቻ ነው እኮ የመጣው…” ሲለው ታዋቂው ድምጻዊ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“የመጡት የማያውቁኝ ሦስት ሰዎች ናቸው፡፡ የሚያውቁኝማ ያውቁኛል…” ብሎ ቁጭ፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ነገራችን ሁሉ “እንኳን በዓል መጥቶ እንዲሁም ብላ፣ ብላ… ጠጣ፣ ጠጣ ይለኛል…” አይነት ነገር ሆኖ የለ…በልክ ቢሆን አሪፍ ነው፡፡
እኔ የምለው… ከእኔ ቢጤ ‘ባዶ ኪስ፣ ሙሉ ምላስ’ ወዳጆቼ ጋር ስንገናኝ ሁል ጊዜ ከአፋችን የማይጠፋው ዓረፍተ ነገር ምን መሰላችሁ… “ሰዉ ገንዘብ ከየት ነው የሚያመጣው?” የሚል ነው። ያስብላላ! ለቲማቲምና ሽንኩርት የሠላሳና አርባ ብር ተጨማሪ ወጪ ሲጠየቅ… “የዘይት ጉድጓድ አለኝ መሰለሽ!” ብሎ ከሚስቱ ጋር የኑክሌር ጦርነት ለመጀመር ምንም የማይቀረው አባወራ፣ ከረፋድ ጀምሮ ‘ሲገለብጠው’ ስታዩ “ሰዉ ገንዘብ ከየት ነው የሚያመጣው?” የማያስብላችሁሳ!
ሰውየው ምን አለ አሉ መሰላችሁ… “የኪስ ቦርሳዬ እንደ ሽንኩርት ነው፣ በከፈትኩት ቁጥር እንባዬ ይመጣል።”
እናማ…እንዲህ በሚባልበት ዘመን…አለ አይደል… የቤቱ መሶብ ባዶ ሆኖ በየክትፎ ቤቱ ‘ቦታ እስኪለቀቅ’ ሰልፍ የሚያዝበትን ዘመን ስታዩ፣ የሆነ ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ ይታያችኋል፡፡ በገንዘብ ቦርሳችን ስጥ ብሩን ብቻ ሳይሆን አርቆ ማስተዋልን የሚያስገባልን ተአምሩን ይላክልን፡፡
“የኪስ ቦርሳዬ እንደ ሽንኩርት ነው…” ከማለት ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2651 times