Monday, 24 August 2015 09:46

ኮሜዲያኑ በቡሄ ጭፈራ 10ሺ ብር አሰባሰቡ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(9 votes)

ችግርንም ጫማንም እንጠርጋለን” ፕሮጀክት ይጀመራል

ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የኢትዮጵያ ኮሜዲያን ማህበር አባላት ግማሽ ያህሉ ኮተቤ በሚገኘው “ሙዳይ በጎ አድራጎ ማህበር” ግቢ ውስጥ ነበሩ፡፡ ኮሜዲያኑ የተሰናዱበት ምንም ዝግጅት አልነበራቸውም፡፡ ከነሐሴ 11-17 ቀን 2007 ዓ.ም የቡሄንና የአሸንዳን በዓል ምክንያት በማድረግ በበጎ አድራጎቱ ማህበር ግቢ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄድ በመስማታቸው ነበር ወደ ቦታው የመጡት።
በባህል ሳምንቱ የአሸንዳና ሆያ ሆዬ ጭፈራዎች እንደሚካሄዱ፤ የባህል ጥበቃ ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም መሰናዳቱን፤ የባህላዊ አለባበስ ትርዒት እንደሚቀርብ፤ የስዕል ኤግዚቢሽን እንደተሰናዳ፤ የችቦ፣ የዶሮና የእንቁላል ሽያጭ እንደሚኖር፤ በዝግጅቶቹ ላይም የተለያዩ አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች እንደሚገኙ ሰምተዋል፡፡
በዚህ ምክንያት በ “ሙዳይ በጎ አድራጎ ማህበር” ግቢ የተገኙት ኮሜዲያኑ፤ በዕለቱ በግቢው የተሰናዳውን ዝግጅት አይተውና ገለፃ ሰምተው ብቻ መመለስ ስላልፈለጉ “ምን እናድርግ?” የሚል ጥያቄ አንስተው፣ በኮተቤ ዙሪያ የቡሄ ጭፈራ በመጫወት የበጎ አድራጎት ማህበሩን ሥራ ለማስተዋወቅ ወሰኑ፡፡
ለዚሁ ዓላማ በረከት በቀለ (ፍልፍሉ)፣ ደምስ ፍቃዱ (ዋኖስ)፣ ስንታየሁ ክፍሌ (አሙቅልኝ)፣ ይበለጥ ግዛው (ወይራው)፣ አቢይ ሳህሌ (መሮ)፣ አሰፋ ተገኝ (ባሻ)፣ አይቸው ሽመልስ (የገሊላ ሰው)፣ መርድ አባተ፣ መስፍን ጋሻው፣ ሀብታሙ ካሣዬ፣ አለማየሁ ጌታቸው፣ ሀና አሰፋና ብሩክታዊት ፋንታሁን ለቡሄ ጭፈራ ተነሱ፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ሚኒባስ መኪና አቀረበ። የአካባቢው ወጣቶች፤ ኮሜዲያኑ ሄደው ቡሄ የሚጨፍሩባቸውን ግለሰብና ተቋማት መርጦ የመምራት ኃላፊነት ወሰዱ፡፡
ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሁለተኛ በር የጀመረው የኮሜዲያኑ የቡሄ ጭፈራ፣ወደ ኮተቤ መሳለሚያ አቅንቶ፣ ካራ በመድረስ በጤና ጣቢያዎች፣ ሆቴሎች፣ ቡና ቡቶች …. ለ3 ሰዓት ያህል ከተከናወነ በኋላ ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ግቢ ሲመለስ 10ሺ 345 ብር አሰባስቦ ነበር፡፡
ኮሜዲያኑ በቡሄ ጭፈራው ከሰበሰቡት ገንዘብ በላይ ለበጎ አድራጎት ማህበሩ ያደረጉት የማስተዋወቅ ሥራ ላቅ ያለ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ከቡሄው ጭፈራ በኋላ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ግቢ ችቦ የማብራት ሥነ ስርዓት ተከናውኗል፡፡ ኮሜዲያኑ እግረመንገዳቸውን የግቢውን ተማሪዎች ለማዝናናትም ሙከራ አድርገዋል፡፡
ለአጭር ሰዓት በቆየው የውይይት መድረክም ኮሜዲያኑ በቁጭት ያነሱት ነገር ነበር፡፡ ጊዜ ተወስዶ ቢታሰብበትና ተዘጋጅተውበት ቢሆን ኖሮ፤ ብዙ ባለሙያዎችን በማሳተፍና በማስተባበር ትልቅ ሥራ መስራት ይቻል እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ግቢ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ወጣቶች ያመነጩት ሀሳብ ለኮሜዲያኑ አቀረቡ፡፡ ጉዳዩ መርካቶ ውስጥ በተመረጡ ቦታዎች ጫማ በመጥረግ ማህበሩን በማስተዋወቅ ረጂዎችን የመመልመል ተግባር ለመፈፀም ነው ያሰቡት። ኮሜዲያኑ በእቅዱ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። “ችግርንም ጫማንም እንጠርጋለን” በሚል ቃል የሚካሄደው ፕሮግራም፤ ከጥቂት ሣምንታት በኋላ የሚጀመር ሲሆን ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ አባላት ያለበት ኮሚቴም ተዋቅሯል፡፡
ስለሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር አመሰራረትና እያከናወነ ስላለው ተግባራት የሚተርክ የ15 ደቂቃ ዶክመንተሪ ላይ እንደሚታየው፤ የበጐ አድራጐት ማህበሩን በስሟ የመሰረተችው ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ትባላለች፡፡ ማህበሩ ለሕፃናት፣ ሴቶችና እናቶች ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በመጀመሪያ የተከፈተው በትምሀርት ቤትነት ነበር፡፡ በ1993 ዓ.ም የተቋቋመው “ፍሬሽ ኤንድ ግሪን ትምህርት ቤት” በክፍያ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ፡፡ የሚያስተምር ሲሆን
ከፍለው መማር የማይችሉ ተማሪዎችን መርዳት የጀመረው በምሥረታው ማግስት ነበር። በነፃ የሚማሩት ልጆች ቁጥር እየበረከተ ሲመጣ ልጆቻቸውን ከፍለው የሚያስተምሩ ወላጆች ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ችግሩን ለመፍታትም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ለወ/ሮ ሙዳይ የቀረበላት ጥያቄ ከሁለት አንዱን ምረጪ የሚል ነበር፡፡ ቢዝነሱ ይሻልሻል ወይስ በዕርዳታው ተግባር መሰማራት? ተባለች፡፡
“ችግረኛ ልጆችን መበተን አላስቻለኝም” የምትለው ወ/ሮ ሙዳይ፣ ሰብአዊነት ወደሚጠይቀው ተግባር ተሰማራች፡፡ ሙዳይ የበጎ አድራጎት ማህበርን በመመሥረት ለህፃናት ትምህርት፣ ምግብና ማደሪያ፤ ለወላጆቻቸውና ለተለያዩ ችግረኛ ሴቶች ደግሞ ስራ ፈጥራ የአቅሟን ማድረግ ከጀመረች 13 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
160 ችግረኛ ልጆችን በመርዳት የጀመረው የበጎ አድራጎ ተግባር፤ አሁን በተለያዩ ደረጃ እየተረዱ ያሉት ሕፃናት ቁጥር 739 ደርሷል፡፡ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ይህንን የበጎ አድራጎት ተግባር የምታከናውነው በሁለት የገቢ ምንጭ ነው፡፡ የከብት እርባታ፣ የእንጉዳይና አትክልት ልማት ሥራዋ አንዱ የገቢ ምንጭ ሲሆን ለምትሰራው የበጎ አድራጎት ተግባር አቅማቸው በፈቀደ መጠን የተለያየ እርዳታ የሚያደርጉላት ሰዎች እገዛ ሌላው ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ከተረጂዎቹ ቁጥር ብዛትና ከስራው ስፋት አንፃር ችግሮቹ ሰፍተው ከአቅሟ በላይ እየሆነ መምጣቱን ትናገራለች፡፡
የበጎ አድራጎት ሥራው፤ በወር 60ሺህ ብር ገደማ ኪራይ በምትከፍልባቸው የግለሰብ ቤቶች ነው የምታከናውነው፡ በየዕለቱ አንድ ኩንታል ጤፍ ተፈጭቶ ቢጋገርም ለተረጂዎቹ የምግብ ፍላጎት በቂ ሆኖ ስላልተገኘ በቅርቡ እራት ማብላቱን ለመቀነስ መገደዷን ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ ገልፃለች፡፡ “ከእህል ነጋዴዎች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የተለያየ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች … በአመኔታ በዱቤ የወሰድኩባቸው ዕዳ መከማቸት የገጠመኝ ችግር አንዱ ማሳያ ነው” ትላለች፤ ወጣቷ የበጎ አድራጎ ማህበር መሥራች፡፡
በሙዳይ በጎ አድራጎት ማህበር ግቢ እየኖሩ እርዳታ ከሚያገኙት መሐል አንዱ ህፃን የሱነህ አስራት ይባላል። የሕፃኑ ወላጆች ልጃቸው ማየትም፣ መስማትም፣ መናገርም ሆነ መቆም እንደማይችል የተረዱት ከተወለደ ከ6 ወር በኋላ ነበር፡፡ የሱነህ ከወላጆቹ ተገቢውን እርዳታ ማግኘት አለመቻሉን የሰማችው ወ/ሮ ሙዳይ፤ ህፃኑን ወደ ማዕከሉ አምጥታ የተሻለ እርዳታ እንዲያገኝ አደረገች፡፡
አሁን የ6 ዓመት ልጅ የሆነው የሱነህ አስራት፤ ለብቻው ሞግዚት ተመድለት እንክብካቤ ይደረግለታል። ትንሽ ትንሽ መቆም ጀምሯል፡፡ የመስማት፣ የመናገርና የማየት ተስፋ እንዳለውም በሐኪሞች ተረጋግጧል። የችግሩ ዋነኛው ምክንያት ጭንቅላቱ ውስጥ ያለ እጢ መሆኑ ታውቋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ኦፕራሲዮን ከመሞከር ይልቅ በሂደት ለውጥ የሚያመጣ መድኃኒት እየተሰጠው መሆኑንና ከ4 ዓመት በኋላ ህፃን የሱነህ ዓይኖቹ ማየት እንደሚችሉና ችግሮቹ እንደሚቀረፉ በሐኪሞች ተነግሯቸው፤ በተስፋ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ለህፃኑ የተመደበችለት ሞግዚት ትገልፃለች።
የቡሄና የአሸንዳ በዓልን ምክንያት በማድረግ፤ የበጎ አድራጎት ማህበሩን ተግባራት ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ የታሰበውን ፕሮግራም ለመመልከት በቦታው የተገኙት የኮሜዲያን ማህበር አባላት ምንም ባልተዘጋጁበት ሁኔታ የፈጠሩት ገቢ የማሰባሰብ፣ ለአካባቢው ህብረተሰብ ግንዛቤ የማስጨበጥና የበጎ አድራጎት ማህበሩን አባላት የማዝናናት እንቅስቃሴ ድንቅ ነበር፡፡ “ችግርንም ጫማንም እንጠርጋለን” በሚል ሊካሄድ በታቀደው ፕሮጀክት የተሻለ ነገር እንሰራለን ብለዋል - ኮሜዲያኑ፡፡

Read 3474 times