Monday, 24 August 2015 09:55

በድድ ህመም የሚገለፁ በሽታዎች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

የድድ ህመም ከጥርስ ንፅህና ጋር ተያይዞ ከሚከሰተው በተጨማሪ የተለያዩ ከባድ የጤና ችግሮች ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ በድድ ህመም ከሚገለፁ የጤና ችግሮች ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
የድድ ህመምና የስኳር በሽታ
የድድ ህመም የስኳር በሽታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቋሚ ምልክት ሊሆን ይችላል። የስኳር በሽታ የሰውነትን ኢንፌክሽን የመከላከል አቅም ያደክማል፡፡ ይህ ደግሞ የደም የስኳር መጠን እንዲጨምር በማድረግ ችግሩ በድድ ህመምነት ይገለፃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የድድ ህመም የደም ስኳር መጠንን ያዛባዋል፡፡ ትክክለኛ የልኬት መጠኑን ለማወቅ እንዳይቻልም ያደርጋል፡፡
የድድ ህመምና ደም ማነስ
የደም ማነስ ህመም ካለብዎ ህመምዎ በድድዎ መወየብ ይገለፃል፡፡ የደም ማነስ አለብዎ ማለት ሰውነትዎ በቂ ቀይ የደም ሴል የለውም፣ አሊያም ቀይ የደም ሴሎችዎ በቂ ሆሞግሎቢን አልያዙም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰውነትዎ ለኦክስጅን እጥረት እንዲጋለጥ በማድረግ በአፍዎና በድድዎ ላይ ቁስለትና መወየብ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል፡፡
የመገጣጠሚያ አካላት በሽታና የድድ ህመም
ሩማቶይድ አርተሪስ ተብሎ የሚጠራው የመገጣጠሚያ አካላት በሽታ በአብዛኛው በድድ ህመም ሊገለፅ ይችላል፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች በድድ በሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ህመሙ ከሌለባቸው ጋር ሲነፃፀር በስምንት እጥፍ የበለጠ ነው፡፡
ኤችአይቪ ኤድስና የድድ ህመም
የኤች አይቪ ቫይረስ በደምዎ ውስጥ ካለ የአፍና የድድዎ አካባቢ በሽፍታና በቁስለት መጠቃቱ አይቀሬ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚዎች በሽታው የሰውነታቸውን በሽታ የመከላከል አቅም ስለሚያዳክመው በአፋቸው አካባቢ የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች የድድ ቁስለትን ሊያስከትልባቸው ይችላሉ።
የልብ በሽታና የድድ ህመም
በአፋችን አካባቢ የሚገቡ ባክቴሪያዎች በደም ስሮቻችን አማካኝነት በደም ቅዳዎቻችን ላይ በሚገኙ ፋቲ አሲዶች ላይ በመጣበቅ እብጠትን ይፈጥራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በልብ ህመም ለመያዝ ምክንያት ይሆናል። አንዳንድ ጥናቶች፤ የድድ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ህመሙ ከሌለባቸው በበለጠ ለልብ በሽታ የተጋለጡ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡
ውርጃና የድድ ህመም
እርግዝናን ተከትለው የሚመጡ የሆርሞን ለውጦች ለተለያዩ ችግሮች መከሰት መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። ነፍሰጡር ሴቶች የድድ ህመም ካጋጠማቸው ፅንሱ ያለጊዜው ሊወለድ ወይም ውርጃ ሊያጋጥማቸው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ችግሩ የሚከሰተው በኢንፌክሽን አማካኝነት እንደሆነም ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ጭንቀት እና የድድ ህመም
ጭንቀትና ድብርት በተደጋጋሚ ከገጠምዎ ጤናዎ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው፡፡ ይህ ችግርዎ ደግሞ በድድ ህመምዎ ሊገለፅ ይችላል፡፡ ሰዎች በከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት ውስጥ ሲሆኑ ኮርቲስል የተባለው ሆኖሞናቸው መጠኑ ይጨምራል፡፡ ይህ ሆርሞን በድድና በአጠቃላይ የሰውነት ክፍላችን ላይ ችግር ፈጣሪ ሆርሞን ነው፡፡ ከጭንቀትና ድብርት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች አልኮል መጠጣት ሲጋራ ማጨስ ችግሩ እንዲባባስ ያደርገዋል፡፡
የአሜሪካ የጤና ተመራማሪዎች በያዝነው የፈረንጆ ዓመት ይፋ ያደረጉትጥናት እንደሚያመለክተው፤ ቀላ ያለና ያበጠ ወይም የሚደማ ድድ ከልብ እስከ ስኳር ህመም ድረስ ላሉና እጅግ አደገኛ ለሆኑ የጤና ችግሮች መኖር ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጤናማ ድዶች ፒንክ ቀለም ያላቸውና ጠንከር ያሉ መሆናቸውን የጠቆመው ጥናቱ፤ ችግር ያለባቸው ድዶች በወቅቱ ህክምና ካላገኙ ሌሎች በሽታዎችን የማስከተልና ለሞት ሊዳርጉም እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

Read 9704 times