Monday, 24 August 2015 09:57

የግል የጤና ተቋማት በአዲሱ የጥራት መለኪያ ላይ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ ገለፁ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

 የግልና የመንግሥት የጤና ተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር ለመወሰን እንዲያስችል የወጣው አዲሱ የጥራትና ብቃት መለኪያ (ስታንዳርድ) አንዳንድ ችግሮች እንዳሉበት እና የተቋማቱ መለኪያው ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም አኳኋን ሊስተካከል እንደሚገባው አስታወቁ፡፡
ተቋማቱ ሰሞኑን በፍሬንድሺፕ ሆቴል ባደረጉት ስብሰባ ላይ እንደገለፁት፤ የስታንዳርዱ መውጣት ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና የታካሚውን ደኅንነት ለመጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ቢታወቅም ስታንዳርዱ ግን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ፣ ከመሬት አቅርቦት፣ ከባለሙያዎች ቁጥር አንፃር ያልተቃኘና አሁን አገሪቱ ባለችበት ደረጃ ሊሟላ የማይችል ነው ብለዋል፡፡  
አዲሱ ስታንዳርድ ማሻሻያ ሳይደረግበት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በርካታ የጤና ተቋማትን ከአገልግሎት ውጭ እንደሚያደርጋቸው የገለፁት የተቋማቱ ኃላፊዎች ይህም ለጤና ተቋማቱም ሆነ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ገልፀዋል፡፡  የኢትዮጵያ ሕክምና ማህበር፣ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሀኪሞች ማህበር፣ የአዲስ አበባ የግል ጤና ተቋማት አሰሪዎች ማህበር፣ የግል ሆስፒታሎች ማህበርና የአዲስ አበባ የግል ክሊኒክ ባለቤቶችና አሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ስታንዳርዱ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ችግሮች እንዳሉበትና ሊስተካከል እንደሚገባው በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ ስታንዳርዱ የታካሚውን ደኅንነትና የሕክምና ጥራቱን በማይነካ መልኩ ሊሻሻል የሚችልበት በቂ ክፍተት እንዳለው አስረድተዋል፡፡ ይህንንም በተለያዩ መድረኮች ሲያቀርቡ እንደነበር ገልፀው፤ ስታንዳርዱን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ህብረተሰቡን ሊጠቅም በሚችል፣ የህክምናውን ጥራትና የታካሚዎችን ደህንነት በማይነካ መልኩ ማሻሻል ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችንና መሳሪያዎችን በማምጣት፣ ጥራት ያለው ህክምናና ደንበኛ ተኮር አገልግሎቶችን በመስጠት የግሉ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቶቹ፤ በከተሞች ከሚኖረው 59% እና ከገጠሩ ነዋሪ 34% የሚሆነው ህዝብ የጤና አገልግሎቶችን የሚያገኝባቸውን ከ11ሺ በላይ የግል የጤና ተቋማት ድጋፍና ማበረታቻ በማድረግ ራሳቸውን አሻሽለው ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው፣ የታካሚውን ደህንነት የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ማገዝ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በስታንዳርዱ ላይ ይታያሉ በሚሏቸው ችግሮች ላይ በጋራ ተወያይተው የማሻሻያ ሐሳቦችን ለመንግሥት ለማቅረብ ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም የማህበሩ ፕሬዚዳንቶች አክለው ገልፀዋል፡፡

Read 4302 times