Monday, 24 August 2015 10:08

የህይወት አዙሪት

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(12 votes)

 ማናችንም ህይወት ወዴት እንደምትመራን አናውቅም፡፡
ማናችንም!
እሷ የደሀ ልጅ ነበረች፡፡ ትምህርት አልሆናትም። ስለዚህ ተሰደደች፡፡ የተሰደደችው የራስዋን ኑሮ ልታሸንፍና ቤተሰቦችዋንም ለመርዳት አስባ ነው፡፡ ተሰደደች ወደ ጅዳ!፡፡
ህይወትዋ ኩሽና ውስጥ ሆነ፡፡ ኑሮዋ የሚያብበው የሰው አፓርታማ ከነባኞ ቤቱ፣ ከነሽንት ቤቱ ስታፀዳ ሆነ። ዕጣ ፈንታ እንዲህ ነው! አንዱን ለተሽከርካሪ ወንበር፣ አንዱን ለሰው ጓዳ፣ አንዱን ለክብር፣ ሌላውን ለውርደት፤ አንዱን ለሳቅ፣ አንዱን ለለቅሶ፣ አንዱን ለደስታ፣ አንዱን ለሀዘን፣ አንዱን ለቁንጣን (ከጥጋብ አልፎ)፣ አንዱን ለጠኔ (ከረሀብም አልፎ)፣ አንዱን ለድህነት … ዕጣ ፈንታ እንዲህ ነው! …..
የመጀመሪያ ሰሞን ከብዷት ነበር፡፡ ብቸኝነቱም፤ ዕድሏም፣ እያማረርዋት እረፍት ነስተዋት ነበር፡፡ በኋላ ግን በመጠኑም ቢሆን ለመደች፡፡ የግድ ሲሆን የማይለመድ ነገር የለም አይደል!
ቀኑን ሙሉ ከፎቅ ፎቅ ስትሮጥ፣ አፓርታማውን ስታካልል ትውላለች፡፡ ሌሊቱን ስለ ቤተሰቦችዋና ስለ ወደፊት ህይወትዋ ስታልም ታድራለች። የመጀመሪያዎቹ ዓመታት እየነጎዱ ሄዱ፡፡ እንደ ቀልድ አስር ዓመት ሆናት። አንድ ቀን እንደ ልብዋ ስቃ ሳትጫወት፣ አንድ ቀን እንደ ፍላጎትዋ ለብሳ ሳትታይ፤ እንደ ሴትነትዋ ሳትጋጌጥና ሳትዋብ፡፡ ሳትዋብና ወንድ ሳትስብ፡፡
ከጊዜያት በኋላ ህይወትዋ ያሳስባት ጀመር፡፡ ወንድ ስማ አታውቅም! በወንድ ተስማ አታውቅም!
ሴትነትዋ ከወንድነት ጋር አልገጠመም፡፡ ተፈጥሮን የተቃወመችው ይመስላት ጀመር፡፡ ወንድ ያለ ሴት፣ ሴትም ያለ ወንድ መኖር እንደማይችል ሲነገር፣ ሲባል ሲወራ ሰምታለች፡፡ እሷ ግን ….
ልክ ነው፤ “አዳም ብቻውን ቢሆን መልካም አይደለም፤ አጋር ያስፈልገዋል” ብሎ አይደል እግዜርስ ከጎድን አጥንቱ ሄዋንን የፈጠረለት?! ስለዚህ …
በዚህ ሀሳብ መብሰልሰል ከጀመረች በኋላ ምንም ነገር ሳይለወጥ አምስት ዓመት እንዲሁ እንደዋዛ ጨመረች፡፡ በአረብ ሀገር ለአስራ አምስት ዓመታት ኖረች፡፡ ያሳሰባት ዕድሜዋ ገባ፡፡ ሰላሳዎቹን አጋመሰች፡፡ እንደ ሸረሪት ድር፣ ሀሳብና ጭንቀት አናትዋ ላይ ጎጆውን ሰራ፡፡
በእረፍት ቀንዋ ከሀገርዋ ልጆች ጋር ወደተከራዩት ቤት እየሄደች ታሳልፋለች፡፡ ወደዚያ ስትሄድ እንደቀድሞው በግድየለሽ አለባበስ ላለመሄድ ወሰነች፡፡ ቢያንስ በሰው ዓይን ውስጥ ለመግባት፣ ቢበዛ ወንድ ለመማረክና የግልዋ ለማድረግ መሽቀርቀር ጀመረች፤ ሴት ጓደኞችዋ እስኪገረሙባትና ተገርመው እስኪያሟት ድረስ!
“ምን ተገኘ ባካችሁ?”
“አዲስ ነገር አለ እንዴ?”
“ቤዛ ምን አገኘች እንዲህ የተለወጠችው?”
ወዘተ ወዘተ ተባለ፡፡ ….
በስልክዋ ላይ ካስጫነቻቸው ዘፈኖች አንዱ የኃይሌ ሩትስ ዘፈን ነው፡፡
“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ
እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ!”
ደግማ፣ ደጋግማ ትሰማዋለች፡፡ የራስዋ ጩኸት የሆነ ያህል ይሰማታል፡፡ ግጥሙን ራስዋ የፃፈችው ሁሉ ይመስላታል፡፡
“እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ
እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ!”
የአዲስ አበባ ልጆችና ጥቂት የክፍለ ሀገር ልጆች ሆነው ነው የእረፍት ቀናቸውን የሚያሳልፉበትን ቤት የተከራዩት፡፡ ታዲያ “ዘር ከልጓም …” እንዲሉ በኢትዮጵያዊነታቸው በጣም ነው የሚዋደዱት። የአንድ ሀገር ልጆች ሳይሆን የአንድ እናት ልጆች ነው የሚመስሉት፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን መዘማል መጣ፡፡
የመጣው ጓደኛቸው አዜብ ጋ ነበር፡፡ መዘማልና አዜብ የሐዋሳ ልጆች ናቸው፡፡
ቤዛ የአዲስ አበባ ልጅ ብትሆንም ከአዲስ አበባዎቹ ጋርም ሆነ ከክፍለ ሀገር ልጆች ጋር በደንብ ትግባባለች፡፡ መዘማል ቤዛን ሲያይ፤ “የማን ቆንጆ ናት ባካችሁ እቺ!!” አለ፤ ተደንቆ፡፡
እነ አዜብ አስተዋወቁዋቸው፡፡
“ቤዛ ትባላለች፤ የአዲስ አበባ ልጅ ናት፤ እዚህ ከመጣች አስራ አምስት ዓመት አልፏታል” ለሷም ነገርዋት፡፡
“መዘማል ይባላል፤ የሀዋሳ ልጅ ነው፡፡ እዚህ ከመጣ ሁለት ዓመቱ ነው፡፡” ቤዛና መዘማል ተዋወቁ፡፡
መዘማል በእረፍት ቀን መምጣቱንና ከቤዛ ጋር ጥግ ይዞ ማውራቱን አዘወተረ፡፡
ከብዙ ………. ብዙ ግንኙነት
ከብዙ ………. ብዙ ትውውቅ
ከብዙ ………. ብዙ ጭውውት
ከብዙ ……….. ብዙ ጊዜ በኋላ፤ መዘማልና ቤዛ ፍቅረኛሞች ሆኑ፡፡
ቤዛ “ያሰብኩት ተሳካ፤ ያለምኩት ደረሰ ብላ” አንጎራጎረች፡፡
ስለ ወደፊት ህይወታቸው ሲነጋገሩ፣ ቤዛ አገርዋ መግባት እንደምትፈልግ ገለፀችለት፡፡
“እዚያ ተኪዶስ ምን ይሰራል? ኢትዮጵያ እኮ ለኑሮ በጣም አስቸጋሪ አገር ሆናለች” አላት
“ታዲያ በግርድና ልቀር ነው፤ እስቲ ልሂድና አንድ ቀን እንኳን የሀገሬን ንፁህ አየር ልተንፍስ!” አለችው፡፡
“አይ አባባሌ እዚህ ቅሪ ለማለት ሳይሆን ትንሽ ጊዜ ሰርተን .. ገንዘብ ካጠረቃቀምን በኋላ ብንሄድ ብዬ ነው።” አላት
“ለማንኛውም አስብበት! አብረን ነው ወደ ሀገራችን የምንገባው፤ ገብተን ቶሎ መጋባት አለብን እሺ!?”
“አታስብ የሆነ ነገር ላይ የምናውለው ገንዘብ እኔ አላጣም … አንተ ከመጣህም ቅርብ ስለሆነ ምንም ላይኖርህ ይችላል፡፡ እኔ ግን ያጠራቀምኩት የሆነ ያህል ገንዘብ ስላለኝ፣ እሱን አንድ ነገር ላይ እናውለውና መተዳደሪያችን እናደርገዋለን፡፡”
ቀና ብላ ፊቱን አየችው፡፡ ምንም ዓይነት የስሜት ለውጥ ፊቱ ላይ አላየችም፡፡ እናም ቀጠለች፡፡ “እኔ የምልህ”
“አንቺ የምትይኝ?”
“የትራንስፖርት ዘርፍ እንዴት ነው? በኢትዮጵያ ማለቴ ነው …”
“ደህና ይመስለኛል …”
“ባንድ ልቤ የሆነ የጭነት መኪና ገዝተን አንተ ብትሾፍረው … እያልኩ አስባለሁ … በሌላ ልቤ ደግሞ ደህና ቦታ ላይ ሱቅ ነገር… ቡቲክ ምናምን ብንከፍት ብዬ አስባለሁ፡፡ የቱ የሚሻል ይመስልሃል?”
“ስለ ሱቁ ብዙ የማውቀው ነገር የለም፡፡ የመኪናው ሀሳብ ግን ጥሩ ይመስለኛል” አላት፡፡
“በቃ ከስድስት ወር በላይ መቆየት የለብንም … ወደ ሀገራችን ተመልሰን መኖር አለብን!”
* * *
ከስድስት ወር በኋላ …..
መዘማል ከእሷ ቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የስራውን ሁኔታ ካጠና በኋላ መኪናውን ገዝቶና ቤት ተከራይቶ እንዲጠብቃት ነግራው፣ ብሩን ሰጥታው ወደ ኢትዮጵያ ሸኘችው፡፡ ከወር በኋላ እሷም ጓዜን ማቄን ሳትል፣ ለቤት ማሟያ የሚሆናትን አንዳንድ ነገር ሸምታ ወደ ኢትዮጵያ ተሳፈረች፡፡
አዲስ አበባ ስትደርስ ግን መዘማል ቤት አልተከራየም። ቤዛ ወላጆችዋ ቤት አረፈች፡፡
ለምን ሳይከራይ ቆየኝ ብላ ማዘኗ አልቀረም፡፡ ግን እሱን ትታ ሌላኛው አጀንዳቸው ላይ አተኮረች፡፡ ስለ ስራው አጥንቶ ምን ላይ እንደደረሰ ጠየቀችው፡፡
“ጥሩ ስራ ነው” አላት “ቆንጆ አይሱዙም ገዝቻለሁ … መንጃ ፍቃዴን አሳድሼ ስራውን እጀምራለሁ፡፡” አላት፡፡
ቤዛ ደስ አላት፡፡ ወደ ሀገርዋ በመመለሷ ፈንጥዛለች። መዘማል ስለ ስራው አጥንቶ ያገኘው መረጃና መኪናውንም መግዛቱ አስደስቷታል፡፡ አሁን ዋና ዓላማዋ ልጅ መውለድ ነው፡፡ የአብራክዋን ክፋይ ስታሳድግ በዓይነ ህሊናዋ እየሳለች ሀሴት አደረገች፡፡
ዕድሜዋ ሰላሳ ሰባት ደርሷል፡፡ ከዘጠኝ ወር በኋላ የመጀመሪያ ልጅዋን ለመውለድ ወስናለች። ቢሆንላት አንድ አራት ልጆች የመውለድ ዕቅድ አላት፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮ ማዕቀብ ሳትጥልባት ልትቀድማት አሰበች፡፡ ቶሎ ቶሎ መውለድ አለብኝ ብላ ከራሷ ጋር ተማከረች፡፡
ነገሮች መስመር እየያዙላት ነው፡፡ አሁን የሚያሳስባት የጋብቻቸው ሁኔታ ነው፡፡ ሠርግ ይደገስ አይደገስ የሚለው ሀሳብ አወዛገባት፡፡ እንደ ማንኛዋም ዕድለኛ ሴት ቬሎ ብትለብስ ደስ ይላታል።
ሚዜው ፈዛዛ ነው
ሽቶው ውሃ ነው
የኛ ሙሽራ ዘመናይ
… ቢባልላት ትወዳለች፡፡ ግን ደግሞ ወጪው አስፈርቷታል፡፡ ታዲያ ምን ይሻላል? ቤዛ ብቻዋን ተጨነቀች፡፡
ከ17 ዓመት በኋላ ነበር ወደ አገሯ የተመለሰችው። የ17 ዓመት የቤተሰብ ናፍቆት ተሸክማ፡፡ ለቤተሰቦችዋ ብርቅ ሆናለች፡፡ የእናትና አባትነት፤ የእህትና ወንድምነት ፍቅር፡፡ የከረመ ናፍቆት ….
ዛሬ ግን ቤቱ ደስታ በደስታ ሆኗል፡፡ ያወራሉ …. ይጯጯሃሉ …፡፡ ምን ያክል ተበድላ እንደነበር የታያት አሁን ነው፡፡ የማይረሳ የለም፤ የቤተሰብ ፍቅር ረስታ ነበር፡፡ ቢናፍቋትም፤ ልታገኛቸው ብትፈልግም፤ እንዲህ ጣፋጭና ማራኪ ጊዜ እንደሚኖራቸው ተዘንግቷት ነበር፡፡ አሁን የፍቅር ጥልቀቱ ታያት፡፡ ይህን እውነት መገንዘብዋ ሆድ አስባሳት፤ አለቀሰች፡፡
ደስ ብሏት አለቀሰች! በቁጭት አለቀሰች! የደስታና ሀዘን፤ የሳቅና ለቅሶ ድንበር ጠፋባት፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ የመዘማልን ስልክ ስትሞክር እምቢ አላት፡፡ ናፍቀዋለች! ………... ግን እንዴት ታግኘው? … ብቸኛው የግንኙነታቸው ድልድይ ስልክ ነበር፡፡ ቤተሰቦቹ ጋ እንዳታስልክ ወይ ራስዋ እንዳትሄድ እነሱ ያሉት አዋሳ ነው፡፡ የዚህ ሀገር ጓደኞቹን ደሞ አታውቃቸውም፡፡ ቤዛ ግራ  ገባት! ….
“ምን ሆኖ ይሆን?” ብላ ተጨነቀች፡፡ “አዲስ አበባ ውስጥ ድንብርብር ሲል ሌቦች አግኝተውት ያለውን ተቀብለው ደብድበውት ይሆን?” ብላ ሰጋች፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ብትደውል ብትደውል ስልኩ እምቢ አላት፡፡
እንዳጋጣሚ አንድ ሌሊት እንቅልፍ እምቢ ብሏት ስትገላበጥ፣ እስቲ ለማንኛውም ብላ ስትሞክር ስልኩ ጠራላት፡፡ ከደስታዋ ብዛት ከአልጋዋ ላይ ዘላ መሬት ወረደች፡፡
“ሄሎ”
“ሄሎ መዘማልዬ …. ምን ሆነህ ነው? ምን ገጥሞህ ነው የኔ ማር… ስልክህን ዘግተህ እንዲህ የጠፋኸው?”
“ሞክረሽ ነበር?”
“ይሄን ሳምንት ያልደወልኩበት ቀን የለም፤ በየቀኑ ስሞክርልህ ነበር”
“ነው?”
“አዎ … እንዴት እንደናፈቅኸኝ ደግሞ!”
“ለመሆኑ … መቼ ለመሄድ ወሰንሽ?”
“ወዴት?”
“ወደ ጅዳ ነዋ!”
ፈፅሞ ያልጠበቀችው ዱብዕዳ ነበር፡፡ “እንዴ የምን ጅዳ ነው? ተነጋግረን አይደል እንዴ የመጣነው፤ በመኪናው እየሰራን ተጋብተን እዚሁ ልንኖር‘ኮ ነው ቃላችን!”
“እሱማ ልክ ነሽ …. ግን ….”
“ግን ምን?”
“የመኪናው ገቢ ለሁለት ሰው የሚበቃ አልመሰለኝም፤ ስለዚህ እሱን እኔ እዚሁ እንደሚሆን እንደሚሆን አደርገዋለሁ፡፡ አንቺም የራስሽን አማራጭ መውሰድ አለብሽ!”
“ምንድነው የራስሽን አማራጭ ማለት! ይሄ‘ኮ ተነጋግረንና ተመካክረን የጨረስነው ጉዳይ ነው፡፡”
“አዝናለሁ ቤዛ፤ መኪናው የኔና የኔ ብቻ ነው!” ብሎ ጆሮዋ ላይ ዘጋ፡፡
“ሄሎ …… ሄሎ…… ሄ……..ሎ”
ድጋሚ መልሳ ስትሞክር ስልኩ ዝግ ነው አላት፡፡ ቤዛ አለቀሰች፡፡ ደም እንባ አነባች፡፡
በወግ በማዕረግ አግብቼ እኖራለሁ ስትል፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የልጅ እናት እሆናለሁ ስትል፤ እንዲሁ ሜዳ ላይ መቅረትዋ ክፉኛ ስሜትዋን ጎዳት። ልብዋ ተሰበረ፡፡ በህይወት ተስፋ ቆረጠች፡፡
መዘማል ድምፁ ጠፋ፡፡ ተሰወረ፡፡ እንዳትከሰው ውል የላትም፡፡ ውሉስ ቢኖር እሱ የት ተገኝቶ?!
ብሩን የሰጠችው በእምነት ነው፡፡ እንኳን ገንዘብ ሁለመናዋን ሰጥታው የለ? የወደፊት ባሌ፣ የልጆቼ አባት ብላ … ነበር ያሰበችው፡፡
እሱ ግን መኪናውን በራሱ ስም ከገዛ በኋላ በጠራራ ፀሐይ ከዳት፡፡ … ብዙ አስባ … ብዙ አውጥታ አውርዳ … ሌላ ምርጫ እንደሌላት ተገነዘበች፡፡ ሁሉን ነገር ተዘርፋ መለመላዋን ቀርታለች፡፡ ገንዘቧን … ፍቅሯን … ያለመችውን ትዳርና ልጅ … ሥነ ልቦናዋን … የቀራት ምንም የለም፡፡
ቤዛ ጓዟን ሸክፋ ጨርሳለች፡፡ ዛሬ ማታ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ወደ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ትበራለች። የአገሯን አየር እየተነፈሰች፣ ከቤተሰቧ አጠገብ ለመኖር አልታደለችም፡፡ ዕጣፈንታ እንዲህ ናት!

Read 4513 times