Monday, 24 August 2015 10:15

“ኤሌክትሮኒክ ንግድ” በ30 ሰከንድ 1.2 ሚ. ዶላር ገቢ ያስገኛል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ፌስቡክ  በግማሽ ደቂቃ 5 ሺ 483 ዶላር ገቢ ያገኛል

   በድረ-ገጾች አማካይነት በአለማቀፍ ደረጃ የሚከናወነው “የኤሌክትሮኒክ ንግድ” በየግማሽ ደቂቃው በድምሩ የ1.2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እያስገኘ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን ዘ ሂንዱ ታይምስ ረቡዕ ዕለት ዘገበ፡፡
አሶቻም ዲሎይት የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ሰሞኑን ይፋ ያደረገውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ በሚገኘውና ትርፋማነቱ እየጨመረ በመጣው የኤሌክትሮኒክ ንግድ ከፍተኛ ገቢ እያገኙ ካሉት የአለማችን ታላላቅ ኩባንያዎች መካከል ቀዳሚነቱን የያዘው ታዋቂው የማህበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ ነው።
ፌስቡክ በኤሌክትሮኒክ ንግድ በየሰላሳ ሰከንዱ 5 ሺህ 483 ዶላር ገቢ ያገኛል ያለው ጥናቱ፤ ፒንተረስት እና ትዊተር የተባሉት የማህበራዊ ድረ ገጾችም በ4 ሺህ 504 እና በ4 ሺህ 308 ዶላር የግማሽ ደቂቃ ገቢ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃዎችን የያዙ የአለማችን የኤሌክትሮኒክ ንግድ ገቢ ቀዳሚ ኩባንያዎች ናቸው ብሏል፡፡
ማህበራዊ ድረገጾች መስፋፋታቸው በአለማቀፍ ደረጃ በኤሌክትሮኒክ ንግድ ገቢና ትርፍ ረገድ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል ያለው ዘገባው፤ ማህበራዊ ድረ ገጾቹ የኩባንያዎችን ምርቶችና አገልግሎቶች በተመለከተ ፈጣን መረጃዎችን በማሰራጨትና ንግዱን በስፋት በማቀላጠፍ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ዘገባው ገልጿል፡፡
ኤሌክትሮኒክ የክፍያ ስርአቶች በስፋት መዘርጋታቸውም ንግድ በአለማቀፍ ደረጃ የተቀላጠፈ እንዲሆንና ገዢና ሻጮችን ለአደጋ ከሚያጋልጠው የካሽ ግብይት ወደ ኤሌክትሮኒክ ክፍያ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደረገ ሲሆን የኤሌክትሮኒክ ንግድ እንዲስፋፋም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል ተብሏል፡፡

Read 1802 times