Monday, 31 August 2015 09:17

“እንግዶች ደስ የሚሉት ‘እንደምን ዋላችሁ’…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዳ መቀበል ሲያምርብን! ኮሚኩ ነገር እኮ አሁን፣ አሁን እንግዳ እቤታችን ሲመጣ እኛ “ከቤት ውጡ…” የምንባል አይነት እየሆነ ነው፡፡
እሷ፡— ኦባማን ተቀበልክ?
እሱ፡— ማለት…
እሷ፡— ማለትማ ጋሽ ኦባማን ተቀበልክ             ወይ?   
እሱ፡— ምን አገባኝ?
እሷ፡— ቢያገባህም፣ ባያገባህም እንግዳ ተቀባይ አይደለን እንዴ!
ለነገሩማ “ሀበሾች እንግዳ ተቀባዮች ነን…” ይባል ነበር፡፡ አይደለም ቤት የሚመጣ እንግዳ ህዝባችን እኮ የአገር መሪዎች ሲመጡ በየመንገዱ ግራና ቀኝ ተኮልኩሎ እየዘፈነ ነበር የሚቀበለው፡፡ አሁን ይሄን አይነት ዘመን መጣና ቤታችን ቁጭ ብለን ‘በቴሌቪዥን ላይቭ መቀበል’ ጀምረናል፡፡ የ‘ሴኪዩሪቲ’ ነገር ዓለም አቀፍ ጉዳይ ስለሆነ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች አማራጭ የላቸውም፡፡ ችግሩ ለማስፈጸም የሚሰማሩ ግለሰቦች ባህሪያት ላይ ነው፡፡
በነገራችን ላይ እንግዶች ሲመጡና ትላልቅ ስብሰባዎች ሲደረጉ ከመንገድ እንድንወጣ ሲደረግ፣ “ጥግ ያዙ…” ምናምን ስንባል አንዳንድ ጊዜ መጉላላት ቢጤ እየገጠመን “እውነት ይቺ አገር የማናት?” እንደምንል ይጣፍልንማ! በተረጋጋና የሰውን መብት በማይነካ መንገድ ማድረግ እየተቻለ ‘የማባረር’ አይነት ሲሆን… አለ አይደል… እንግዳ በመጣ ቁጥር “ወይ አበሳ!” የማንልሳ! ባለድርሻ አካላት ያስቡበትማ፡፡
ስሙኝማ….የእንግድነት ነገር ካነሳን አይቀር ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ ‘እንግዳ ተቀባዮች’ ምናምን የሚባለው ነገር እንደ ‘ተንኮለኛው ከበደ’ ታሪክ አይነት ህጻናትን ለማዝናናት የተፈጠረ እየመሰለ ነው፡፡
የሆነ የአንድ አገር ተረት ምን ይላል… “እንግዶች ደስ የሚሉት እንደምን ዋላችሁ ብለው ሲገቡ ሳይሆን፣ ደህና ሁኑ ብለው ሲወጡ ነው፡፡”
ስሙኝማ…ቀደም ባለው ጊዜ የሆነ ዘመድ ቤት አንድ ሁለት፣ ሦስት ወር ቆይታችሁ ትሄዳላችሁ፡፡ እናማ…በሩን የሚከፍተው ሰው… “አንተ ምነው ይሄን ያህል ሰው አስጠላህ! ዘመድ ይጨነቃልም አትል! በሳምንት አንድ ቀን ብቅ ለማለት ጊዜ አጣህና ነው!” ምናምን ይባላል፡
ግብዣውማ …ምን አለፋችሁ… በ‘ጉርሻ ላይ ጉርሻ’ ነው፡፡ አንዱ ሳይላመጥ… “ስሞትልህ…አፈር ስበላ… ቆሜማ እምቢ አትለኝም፣ ይቺን ብቻ…” እየተባለ የእንትን ሰፈር የዕድር ዳኛን ሆድ የሚያካክል ጉርሻ ሆድን ሲጭኑ መዋል ነው፡፡
ዘንድሮ…ኑሮውም ከብዶ ይሁን፣ የሰው ልጅ ግንኙነት ኬሚስትሪውም ተበላሸቶ ይሁን… እንዲህ አይነት እንግዳ ተቀባይነት እየቀረ ነው፡፡ “እስቲ እነእንትናን ልጠይቅ፣ ካየኋቸው ስንት ጊዜ…” ተብሎ ተነስቶ መሄድ እየቀረ ነው፡፡
እናማ…ዓመት ከአምስት ወር ምናምን ቆይታችሁ የቅርብ ወዳጆቻችሁን ልትጠይቁ ትሄዳላችሁ፡፡
በር ታንኳኳላችሁ…በሩን የከፈተው ለረጅም ወራት ያላያችሁት ዘመድ በቆመበት ሆኖ ምን ቢል ጥሩ ነው…“አጅሬው ዛሬ ምን እግር ጣለህ!”
‘በውስጥ አማርኛ’… አለ አይደል… “ለምን መጣህ?” እንደማለት ነው፡፡ ወይም ሠራተኛዋ በር ከፍታላችሁ ድንገት ሲበሉ ከደረሳችሁ ሳህኑ ይንኳኳና…“ምነው ክፉ እንግዳ ይመስል በልተን ስንጨርስ መጣህ!” ትባላላችሁ፡፡ እንጀራው እኮ ገና አልተጋመሰም፡፡
“እንግዶች ደስ የሚሉት እንደምን ዋላችሁ ብለው ሲገቡ ሳይሆን፣ ደህና ሁኑ ብለው ሲወጡ ነው፡፡” ከማለት ይጠብቀንማ!
እናላችሁ…የዘንድሮ እንግዳ አቀባባላችን ተለውጧል፡፡ በበፊት ጊዜ… “አንቺ ቅቤውን እንዲህ የሞጀርሽው እንግዳ ሲመጣ ምን ሊቀርብ ነው!” ይባል ነበር፡፡ የምር እኮ… ሳህንና ሹካ ሳይቀር ‘ለእንግዳ’ እየተባለ ተለይቶ ይቀመጥ ነበር፡፡
ዘንድሮ ልጄ ምንቸት አብሽ፣ የበግ ቅቅል ቅብጥርስዮ ብሎ ግብዣ የለም፡፡ “አንቺ ማነሽ…ከማታ ቡና ቁርስ የተራረፈን ፈንዲሻ ነገር የለም!” … ምናምን አይነት ሆኗል፡፡
ዘመድ ወዳጅ ቤት ሄዶ መጠየቅም እንደ ትርፍ ጊዜ ማሳለፊያም ነበር፡.
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ነገር ካነሳን አይቀር ኳስ ጀመረልን አይደል! (ዲኤስቲቪ ያስገቡ ወዳጆቻችን ካሉ ብለን ስለላ ቢጤ ማካሄድ እንደጀመርን የሚመለከታችሁ ወዳጆቻችን ልብ በሉማ!)
እግረ መንገዴን…የምር ቅር ብሎኛል…ልክ ነዋ  ለምንድነው የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሲጀመር ርችት ምናምን ያልተተኮሰው! ልክ ነዋ…
እንኳንም ተጀመረልን…ልጄ፣ ትከሻችንን ሳይከብደን የምናወራው አንድ ነገር ቢኖር የእንግሊዝ ኳስ ነው፡፡
ኮሚክ እኮ ነው...የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እኛን እንደሚያሳስበን እንግሊዞቹን ያሳስብ እንደሆን የሚያውቅ ያብራራልንማ!…. ልክ ነዋ…አንዳንዴ ስለ ቬንገርና ሞሪንሆ ጠብ ስንሰማ…አለ አይደል… “የጸጥታው ምክር ቤት ጣልቃ የማይገባው ለምንድነው?” ምናመን ለማለት ምንም አይቀረንማ! አልቤንና ምንሽራቸውን መወልወል ከጀመሩ በኋላ እኛ የለንበትም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
የኳስ ነገር ካነሳን አይቀር…ሀሳብ አለን፡፡ እኛ አገር ኳስ ‘ላይቭ’ ሲተላለፍልን ኳስ በተነካች ቁጥር የተጫዋቾች ስም ከእነአባታቸው ለምን እንደሚጠራ ግራ ይገባል፡፡ ተመሳሳይ ስሞች ኖረው የሚያደናገር ካልሆነ በስተቀር መታወቂያ ላይ ያለ ስም እንዳለ ማንበብ ጊዜ ማባከን ነዋ! የአንድ ተጫዋች ሙሉ ስም ‘ተጠርቶ እስኪያበቃ’ ያቺ ኳስ በሰባት ተጫዋቾች ተነክታ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ “ሰጥአርጋቸው በእሱ ፍቃድ ኳሷን በቀኝ ክንፍ በኩል ለዘርአያቆብ ዕቁበሥላሴ አሳለፈ…” እስኪባል ድረስ እኮ ኳሷ እኮ ከአዲስ አበባ ስታዲየም ወጥታ ስታምፎርድ ብሪድጅ ልትደርስ ትችላለች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… የምር ግን ይሄ የማስተላለፍ ቋንቋ ይታሰብበትማ!
እግረ መንገዴን…ከዚህ በፊት ደጋግመን ያልናትን እንድገማትማ፡፡ በሬድዮ ይተላለፍ የነበረ ነው.. እና አስፋው ባዩ የሚባል ‘ግድግዳ’ ተከላካይ ነበር፡፡ እናማ የሆነ ጨዋታ በቀጥታ ሲተላለፍ… “አሁን አስፋው ባዩ ኳስ ይዞ እየገፋ ነው… እየገፋ ነው…” እያለ የጋዜጠኛው ድምጽ ምን አለፋችሁ እየናረ እየናረ ሄደና መጨረሻ ላይ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ለበረኛችን አቀበለው…” እናም ድምጽ ዘጠነኛው ደመና ላይ ከወጣ በኋላ “ለበረኛችን አቀበለው…” አይነት ማስተላለፍ….
እናላችሁ…ኑሮ ከፋና እንግዳ በመጣ ቁጥር “ያደረ ፈንዲሻ የለም?” ከማለት አልፈን፣ እንግዳችን ገና ቁጭ እንዳለ…“ ምን አሁንማ የሚላስ የሚቀመስ ነገር ባይጠፋ ነው…” ይባልና፣ ዕለቱ ‘የአትክልት ተራ ውሎ’ አይነት የሬድዮ ዘገባ የሚመስል ዝርዝር  ይቀርብላችኋል፡፡
ሽንኩርቱ ጣራ ነክቷል፣ ቲማቲም እንኳን እንዲህ ይወደድ! የቆስጣና ነጭ ሽንኩርት ነገርማ ተዪው…አይቀመስም ነው የምልሽ…” አይነት ዲስኩር ይደረጋል፡፡
እኔ የምለው… እናንተ “ለጤናችሁ እንዴት ናችሁ! ደህና ከረማችሁ ወይ?” ምናምን ለማለት ሄዳችሁ እንጂ… ይሄ ሁሉ የዋጋ ዝርዝር የሚቀርብላችሁ…ከዋናው ኦዲተር ተልካችሁ የሄዳችሁ ናችሁ!... ሰርቲፋይድ አካውንታንት ምናምን ናችሁ!…የዋጋ ግሽበት ምናምን መረጃ ሰብሳቢ ናችሁ! የምር ግን ነገሩ ሁሉ አልቻል አለና ተገደን እየዋሸን ነው፡፡
አንዷ ውሸትን እንዴት እንደተነተነችው እዩልኝማ፡፡
“ውሸት
ለወጣት ልጅ ጥፋት ነው፣
ለአፍቃሪ ጥበብ ነው፣
ለወንደላጤ ስኬት ነው፣
ለባል ሁለተኛ ባህሪው ነው፡፡”
አማሪካን ውስጥ አንዱ ጓደኛውን “ፖለቲከኛ ሲዋሽ በምን ይታወቃል?” ሲለው ምን ብሎ መለሰለት መሰላችሁ… “ፖለቲከኛ ከንፈሮቹ በተንቀሳቀሱ ቁጥር እየዋሸ ነው፡፡”
የውሸት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን እዩልኝማ…የሚዋሹ ሰዎች ምልክት ተብለው የተጻፉ ናቸው፡
ውሸት የሚናገሩ ሰዎች…
ብዙ ጊዜ ቶሎ ለመለያየት ይፈልጋሉ፤
ወደ መውጫ በር ደጋግመው ይመለከታሉ፤
ከእናንተ ራቅ ይላሉ፤
መልሶቻቸው አጫጭር ይሆናሉ፤
ምክንያት ፈጥረው ቶሎ መሄድ ይፈልጋሉ፡፡
“እንግዶች ደስ የሚሉት ‘እንደምን ዋላችሁ’ ብለው ሲገቡ ሳይሆን፣ ‘ደህና ሁኑ’ ብለው ሲወጡ ነው፡፡” ከማለት ይጠብቀንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2731 times