Monday, 31 August 2015 09:25

የአረብ ሊግ አገራት የጋራ የጦር ሃይል የማቋቋም ዕቅዳቸውን አራዘሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የጦር ሃይሉ መቀመጫ በአገራቱ መካከል አለመግባባት ፈጥሯል
    የአረብ ሊግ አባል አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች የጋራ የጦር ሃይል ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ስምምነት ከትናንት በስቲያ ለመፈረም ይዘውት የነበረውን ዕቅድ ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘማቸውን ኤቢሲ ኒውስ ዘገበ፡፡አባል አገራቱ ግጭት በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የሰላም ማስከበር ስራ የሚሰራ የጋራ የጦር ሃይል ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ስምምነት ባለፈው ሃሙስ ሊፈርሙ ቀጠሮ ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ ሊጉ በዋዜማው ባወጣው መግለጫ እቅዱ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አስታውቋል፡፡አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ግን፣ እንደ ሊቢያ ባሉ አገራት መንግስትን ለሚቃወሙ ሃይሎች ድጋፍ የሚሰጡ የአረብ አገራት ባሉበት ሁኔታ፣ የሚያቋቁሙት የጋራ የጦር ሃይል ጣልቃ ይግባ አይግባ የሚለው ጉዳይ በአገራቱ መካከል አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል ማለታቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ የጦር ሃይሉ መቀመጫ የሊጉ ዋና ጽህፈት ቤት በሚገኝባት ካይሮ ይሁን የሚለው ሃሳብ በአገራቱ መካከል አለመግባባት ፈጥሮ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ስምምነቱ የተራዘመው ሳኡዲ አረቢያ፣ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስና ኢራቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑንም ገልጧል፡፡አገራቱ የጦር ሃይሉን ለማቋቋም ፈቃደኛ መሆናቸውን ባለፈው መጋቢት ወር በይፋ ማስታወቃቸውንና በግንቦትም ስምምነቱን ማርቀቃቸውን ዘገባው አስታውሶ፣የተራዘመው ስምምነት የሚፈረምበትን ቀን አገራቱ ወስነው እንደሚያስታውቁ ጠቁሟል፡፡

Read 1628 times