Monday, 31 August 2015 09:28

የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ይሳተፋሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 የአሜሪካ ሴቶች ከ95 አመታት በፊት የተጎናጸፉት መብት ነው
                   70 ሴቶች በዕጩ ተወዳዳሪነት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል
    የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች በመጪው ታህሳስ ወር በሚካሄደው የከተማ አስተዳደር ምርጫ በዕጩ ተወዳዳሪነትና በድምጽ ሰጪነት በመሳተፍ በአገሪቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ተሳትፎ እድል ተጠቃሚ እንደሆኑ  ሲኤንኤን ዘገበ፡፡በምርጫ ተወዳዳሪነትም ሆነ በመራጭነት የመሳተፍ መብት ተነፍጓቸው የኖሩት የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች፤በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በመራጭነት እየተመዘገቡ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ከነገ ጀምሮም በዕጩ ተወዳዳሪነት ይመዘገባሉ ብሏል፡፡የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ንጉስ አብደላ የአገሪቱ ሴቶች እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ በምርጫ ተወዳዳሪነትና በድምጽ ሰጪነት መሳተፍ እንደሚጀምሩ ከአራት አመታት በፊት ማስታወቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን ሴቶች ይሳተፉበታል በተባለው ቀጣይ የከተማ አስተዳደር ምርጫ የሚያሸንፉ ሴቶች የተገደበ ስልጣን እንደሚኖራቸው ገልጧል፡፡
በመጪው ምርጫ ሴቶች እንዲሳተፉ መፈቀዱ የአገሪቱን ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው መባሉን ዘገባው ገልጾ፣የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች አሁንም ድረስ ከፍተኛ በደልና ተጽዕኖ እንደሚደርስባቸው ጠቁሟል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ሴቶችን የምርጫ ተሳታፊ ለማድረግ መወሰኑ በሴቶች መብት ጥሰት ከፍተኛ ውግዘት ስታደርስበት ከኖረችው አሜሪካ ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲፈጥር በር ሊከፍትለት ይችላል ያለው ዘገባው፣ የአሜሪካ ሴቶች በምርጫ የመሳተፍ መብታቸው የተረጋገጠላቸው ከ95 አመታት በፊት እንደነበር አስታውሷል፡፡በመጪው ምርጫ 70 ያህል የሳኡዲ አረቢያ ሴቶች በዕጩ ተወዳዳሪነት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ሌሎች 80 ሴቶችም በምርጫ ዘመቻ ሃላፊነት ለመስራት መመዝገባቸውን የዘገበው ዴይሊ ሜይል በበኩሉ፣ ይሄም ሆኖ ግን የአገሪቱ ሴቶች አሁንም ድረስ መኪና መንዳት፣ የባንክ ሂሳብ መክፈት፣ ከባላቸው ውጪ ፓስፖርት ማግኘትና ወደፈለጉት አካባቢ መዘዋወር እንደማይፈቀድላቸውና ዘርፈ ብዙ የጾታ ጫና እንደሚደርስባቸው ጠቁሟል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጾታዊ እኩልነት መለኪያ መስፈርት መሰረት፤ ሳኡዲ አረቢያ ከአለማችን 140 አገራት 136ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ዘገባው አክሎ አስታውቋል፡፡

Read 2549 times