Monday, 31 August 2015 09:30

...የምበላው ቢሰጡኝ ብዬ ከቤታቸው ብሔድ...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2014 በአለም የጤና ድርጅት የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በአለማችን ዙሪያ የሚገኙ ቁጥራቸው ከ35% በላይ የሚሆኑ ሴቶች በህይወት ዘመናቸው አንዴ ለፆታዊ ጥቃት ወይም ተመሳሳይ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ ለዚህ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ከሚገኙባቸው የአለም ሀገራት መካከልም ኢትየጰጵያ አንዷ ነች፡፡ በኢትዮጵያ 71%  የሚሆኑ ሴቶች የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎች ናቸው፡፡
በአውሮፓውያኑ 2010 በሀገራችን በተደረገ ጥናት በገጠሩ የሀገራችን ክፍል 19%  በከተማው ደግሞ 12% የሚሆኑ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ ሴቶቹ ተገዶ የመደፈር ሰለባ የሚሆኑትም በተለያዩ ደረጃ ላይ በሚገኙ ሰዎች ሲሆን በተከታይነት ተመዘገቡ ምክንያቶችም በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ዝቅተኛ የእውቀት ደረጃ (የንቃተ ህሊና ማነስ)
በቀደመ የልጅነት ህይወት ተከስቶ የነበረ ተመሳሳይ ችግር (በልጅነት ግዜ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ መሆን)
ተመሳሳይ ድርጊቶች በቤተሰብ አባላት ወይም የቅርብ ሰው ሲፈፅም በተደጋጋሚ መመልከት
የተለያዩ የአእምሮ ህመሞች
የአልኮል መጠጥ ወይም የሌሎች አደንዛዥ እፆች ሱሰኛ መሆን
ለሴቶች የሚኖር ዝቅተኛ አመለካከት የሚሉ ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለተለያዩ ጥቅሞች በመገዛት (...እንደገንዘብ ...ወዳጅነት ለመሳሰሉ...) አንድ ሰው የፆታዊ ጥቃት እንዲያደርስ ...ድርጊቶችን እንዲፈፅም ሊገፋፉ ወይም ቅድመ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በጎንደር ሆስፒታል በከፈተው ሞዴል ክሊኒክ በመገኘት የተለያዩ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴት ልጆችንና የህክምና እንዲሁም የህግ ባለሙያዎችን ሀሳብ እነሆ ታነቡ ዘንድ አቅርበነዋል፡፡ ...የአእምሮ ዝግመት ያለባት ልጅ ነች፡፡ እናትዋ ሞታለች፡፡ በሕይወት ያለው አባትዋ ብቻ ሲሆን እሱም ሌላ ሚስት አግብቶ የተመቻቸ ኑሮውን የሚመራ ነው፡፡ እርስዋ እንደምትገልጸው የምትኖረው ከቤተሰቦቿ ዘንድ ሳይሆን በመንደርተኛው መካከል በሚደረግላት ድጋፍ ነው፡፡ ሰውነትዋ እጅግ ተጎድቷል፡፡ ንጽህና የሌለው ሕይወት ነው ሕይወትዋ፡፡ ልብስዋ ሰውነትዋ በሙሉ በጣም ቆሽሾአል፡፡ ጎዳና ላይ ውላ የምታድር ነው የምትመስለው፡፡ በጎንደር ሆስፒታል ከሚገኘው ሞዴል ክሊኒክ ለምን እንደመጣች ስትጠየቅ... “...እንጀራ እናቴ አስደፍራኝ ነው እዚህ የመጣሁት፡፡ እኔ ለሆዴ የምበላው ቢሰጡኝ ብዬ     ከቤታቸው ብሔድ ከእሷ ጋር ተቀምጦ የነበረ ሰው እንዲደፍረኝ እስዋ 30 /ሰላሳ/ ብር     ተቀበለች፡፡ የፈለግሁትን እንጀራም ሳላገኝ ...በቃ... ተደፈርኩኝ..... ነበር ያለችው፡፡
ይህች ልጅ ወደ ሆስፒታሉ የመጣችው ከፖሊስ ጋር ነበር፡፡ ባለሙያዋ ይህችን ልጅ እንዴት እንዳገኘቻትና ወደ ሆስፒታል እንዳመጣቻት ገልጻለች፡፡
***
ጥ/    ሳይጂን የኔአገኝ ጥጋቤ... ይህች የአእምሮ ዝግመት ያለባት ልጅ የመደፈር አደጋ     እንደደረሰባት ለፖሊስ እሪፖርት የደረሰው በምን ሁኔታ ነው?
መ/    የመደፈር አደጋ እንደደረሰባት ለፖሊስ እሪፖርት ያደረጉት የጤና ኤክስቴንሽኖች     ናቸው፡፡ እኛም መረጃው እንደደረሰን ወደ ደባርቅ ሆስፒታል ወስደን ስናሳክማት ሆስፒታሉ ደግሞ ወደዚህ ስላስተላለፋት አሁን ጎንደር ሆስፒታል ሕክምና በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ጥ/    ይህች ልጅ በትክክል የደረሰባትን ጉዳት አውቃ ለሚመለከተው አመለከተች?
መ/    አዎን፡፡ የጤና ኤክስቴንሽኖቹ ከቀበሌ ጋር ስለሚሰሩ እዛ ሄዳ ስትናገር አግኝተዋት ነው     ወደእኛ (ፖሊስ) ያስተላለፉዋት፡፡  
ጥ/    የህክምናው ውጤት ምን ሆነ?
መ/    በደባርቅ ሆስፒታል ምንም ያህል ሕክምና አልተደረገላትም፡፡ ምክንያቱም ቶሎ ወደ ከፍተኛ እና ጉዳዩን በትክክል መመርመር ወደሚቻልበት ወደ ጎንደር ሆስፒታል ነው ያስተላለፉአት፡፡ በእርግጥ እንደ ሽንት ምርመራ እና ኤችአይቪ የመሳሰለውን     አይተው ነው ያስተላለፉአት፡፡
ጥ/    ይህች ልጅ ተገድዳ ተደፍራለች የሚያሰኝ መረጃ ተገኝቶአል?
መ/    ተገዳ ተደፍራለች የሚያሰኘው ነገር ገና በምርመራ የሚገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን     እስከአሁንም በተደረገ የማጣራት ስራ የልጅትዋ እንጀራ እናት ለምርመራ በፖሊስ     ቁጥጥር ስር የምትገኝ ሲሆን በሰጠችውም ቃል ልጅትዋ ወድዳ እና ተስማምታ ያደረገችው እንጂ እስዋ ሁኔታውን አንዳላመቻቸች ተናግራለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላሳ ብር ለምን ተቀበልሽ ስትባል ...አ.አ.ይ እኔ ሰላሳ ብር አልተቀበልኩም አምስት ብር ነው ወርውሮልኝ የሄደው ብላለች፡፡ ሰውየው ማነው ስትባል ደግሞ እንደማታውቀው ትናገራለች፡፡ ታዲያ ማን ነው አምስት ብር የወረወረብሽ ስትባል ደግሞ ምንም መልስ የላትም፡፡ የሴትየዋ እምነት ልጅትዋ የአእምሮ ዝግመት ያለባት     ስለሆነች አታውቅም፣ ሕጻን ስለሆነች የእስዋ ምስክርነት ከቁብ አይቆጠርም፣ እራስዋ ወድዳ ነው ያደረገችው ከተባለም ወንጀል አይሆንም የሚል እሳቤ ያላት ናት፡፡ ነገር ግን ይሄ ሁሉ ዋጋ እንደሌለውና የልጅትዋን መብት የረገጠ በመሆኑ ፍትህ እንደሚያስፈልግ ሕጉ ያምናል፡፡  ስለዚህም በአሁኑ ወቅት የልጅትዋም አባት እንዲቀርብ እየተደረገ ሲሆን የተፈጠረውን ችግር     በትክክል ለማወቅ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብለን እንጠብቃለን፡፡  
ጥ/    ተገዶ በመደፈር ዙሪያ ለፖሊስ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ምን ይመስላሉ?
መ/    በእኛ አካባቢ እንደዚህ ያሉ ገጠመኞች ይስተዋላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ልክ     እንደተከሰተ ወዲያውኑ ወደ ህግ በመምጣት ወንጀለኛውን እንዲያዝ እና የሚደረገው ምርመራም ውጤታማ ሆኖ ወደ ፍትህ የሚመራበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ችግሩን አፍነው በምስጢር ይዘው ይቆዩና እንዲያውም ወደ መደራደር ይሄዳሉ፡፡ ይህ የደፋሪውንም ይሁን የተደፋሪውን የቤተሰብ ክብር የሚነካ ስለሆነ በምስጢር ተይዞ እንዲያገባት ሽማግሌ እንዲልክ ይጠየቃል፡፡ ወይንም ደግሞ በልጅቷ ጉዳት ካሳ የመቀበል አይነት ድርድር ያደርጋሉ፡፡ ይህ አልሳካ ሲላቸው ከአስራ አምስት ቀን ወይንም ከወር ከሁለት ወር በሁዋላ ያመለክታሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ምንም መረጃ     ስለማይገኝ ተደፍራለች ለማለት ስለሚያስቸግር መና ሆኖ ይቀራል፡፡ አንዳድ ጊዜም ቤተሰብ የተደፈረችው ልጅ እራስዋ ፈልጋ እንዳደረገችው በመቁጠር ሌላ ቤተሰባዊ ቅጣት የሚያደርሱም አልፎ አልፎ ያጋጥማሉ፡፡
ጥ/    ደፋሪዎቹ ነገሩ በፍጥነት ወደ ሕግ እንዳይቀርብ ለማድረግ የሚጫወቱት ሚና አለ?
መ/    አዎን፡፡ ደፋሪዎቹ ደግሞ በበኩላቸው ከሴቶቹ ጋር የመስማማት አዝማሚያ ያሳያሉ፡፡ እኔ     አገባሻለሁ፡፡ ለማንም እንዳትናገሪ፡፡ በዚህ ሰሞን ሽማግሌ እልካለሁ፡፡ እያሉ አውቀው     ጊዜውን ከፈጁ በሁዋላ ለመረጃ እማያመች ደረጃ መድረሳቸውን ሲያረጋግጡ ...በቃ     አላውቅም... የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡ ጊዜው በረዘመ ቁጥር ሐኪም መረጃ ለመስጠት     ይቸገራል፡፡ ለፖሊስም ብዙ አመላካች ማስረጃዎችን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡     ቀጥተኛ ማስረጃ አይገኝም፡፡ ወንጀለኛውም ይክዳል፡፡ የተደፈሩትም ቢሆኑ አንዳንዴ በትክክል ማስረጃውን ሙሉ በሙሉ ለማቅረብ ይቸገራሉ፡፡
ጥ/    ፖሊስ ለህብረተሰቡ ችግሩን የሚያስገነዝብበትና መሆን ያለበትን አካሄድ ለማሳወቅ     የሚጠቀምበት መድረክ አለ?
መ/    እኛ በአካባቢያችን በየቀበሌው የፖሊስ ኦፊሰር ተመድቦ ወደ ህብረተሰቡ ዘልቀን በመግባት     የምናስተምርበት ፕሮግራም አለን፡፡ አስገድዶ መድፈር ወንጀል መሆኑን ...ልጃገረድ     ትሁንም አትሁንም በግዴታ የደፈረ ሰው እስከ አስራ አምስት እና አስራ ስድስት አመት ድረስ በሚደርስ ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑን በየሳምንቱ በየወሩ እናስተምራለን፡፡ ተያይዞም ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ችግር ከደረሰ ወዲያው ሳይውል ሳያድር ለህግ እንዲያመለክት እና ወንጀለኛውን እንዲቀጣ እንዲያስችልም ምክር እንሰጣለን፡፡  
***
“…ተበዳይዋ ላይ ከደረሰው ጉዳት ይልቅ ቤተሰብ ለራሱ ክብርና ዝና ሲል አልሸነፍም ወይንም ተዋረድኩኝ ከሚል ስሜት በግልጽ ወደ ህግ ወይንም ሕክምናው አለመሄዳቸው በልጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ተደራራቢ ያደርገዋል፡፡ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባት ልጅ ቤት ውስጥ የምትታፈን ከሆነ ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት እንደተፈጸመባት ይቆጠራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ስነልቡናዋ የሚጎዳ ሲሆን ለምን ሆነ በሚል ዱላ ከተከሰተ አካላዊ ጥቃት ይሆናል፡፡ ስለዚህም ተደራራቢ ጥቃቶች በቤት፣ በጎረቤት እንዲሁም በትምህርት ቤት ሊደርስ ስለሚችል ከዚህ ጋር ተያይዞ በወደፊት የልጅቷ ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ጫና መገመት አያዳግትም፡፡ ስለዚህም ይህንን ተገንዝቦ አንዲት ልጅ ጥቃት ሲደርስባት ወደ ህግ እንዲሁም ወደ ሕክምናው በመውሰድ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ለወደፊቱ ማንነቷ መጨነቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ስለ እራስ ክብር ሳይሆን ስለልጅቷ የወደፊት ሕይወት ወላጅ ቤተሰብ ወይንም ሌላ የሚመለከተው ሁሉ ማድረግ ያለበትን እንዲያደርግ  ይጠበቃል፡፡
አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ
ይቀጥላል

Read 2872 times