Saturday, 05 September 2015 08:36

በኮሪያ ሆስፒታል ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    በሚዩንግ ሰንግ አጠቃላይ ሆስፒታል (ኮሪያ ሆስፒታል) የመድኀኒትና የህክምና መሳሪያዎች ክምችትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሰሞኑን ድንገተኛ ፍተሻ የተካሄደ ሲሆን ከፍተሻው ጋር በተገናኘ ሆስፒታሉ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቁን ምንጮቻችን ገለፁ፡፡
ከምንጮቻችን ባገኘነው መረጃ መሠረት፤ የፌደራል የምግብ፣ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ባለፈው አርብ ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኘውን የመድኃኒት ማከማቻ ክፍል ፣ የማደንዘዣ መድኃኒቶች ማስቀመጫ ክፍሎች፣ የህክምና መሳሪያዎችና ስቴራላይዝ ማድረጊያ ሥፍራዎችን አሽጎ ነበር፡፡ ባለፈው ሰኞ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች እሽጉን በመክፈት ምርመራቸውን ያከናወኑ ሲሆን በወቅቱ ስለተገኙ ነገሮች ፣ ስለ አሠራር ሒደቱ፣ እንዲሁምየ ሰራተኞችን የሙያ ብቃትና ፍቃድ የተመለከቱ መረጃዎች ሆስፒታሉ እንዲያቀርብ ደብዳቤ ተፅፎለታል፡፡በሆስፒታሉ በተደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የተገኙት መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች፤ በባለስልጣኑ እውቅናና ፈቃድ የሌላቸውና በባለስልጣኑ በኩል ተመርምረው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ፍቃድ ያልተሰጣቸው ናቸው ተብሏል፡፡
እነዚሁ መድኃኒቶችና ልዩ ልዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችም በባለስልጣኑ የምርመራ ሰራተኞች የተወሰዱ ሲሆን፤ ሆስፒታሉ ስለእነዚህ ነገሮች በቂ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡ ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት የፌደራል የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የሥራ ኃላፊዎችን ብንጠይቅም ጉዳዩ ገና በምርመራ ሂደት ላይ በመሆኑ መረጃ ለመስጠት እንደማይቻል ገልፀው የምርመራ ሂደቱን በተመለከተ ሪፖርት እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከዚህ ቀደምም በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ፣ በሰራተኞች አያያዝና በመድኃኒቶች አቅርቦት ዙሪያ የሚሰሙ ቅሬታና ችግሮችን የተመለከተ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

Read 2113 times