Saturday, 05 September 2015 08:45

የዝናብ እጥረት ያስከተለው ኤሊኖ ከምንጊዜውም የከፋ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

    ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራትን በተለዋዋጭ የአየር ሁኔታና የዝናብ እጥረት እንዲጠቁ ያደረገው የዘንድሮው የኤሊኖ ክስተት ከ50 አመት ወዲህ ከታዩ 4 ተመሳሳይ ክስተቶች የከፋ ነው ተብሏል፡፡ የአለማቀፉ የሜትሮሎጂ ድርጅት ትንበያን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ላይ የአየር መዛባት ተከስቷል፡፡ ኢሊኖ የውቅያኖስ መቀት መጨመርን ተከትሎ የሚፈጠር የአየር መዛባት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በተለይ የዘንድሮው የፓስፊክ ውቅያኖስ ሙቀት መጨመር በታሪክ ጠንካራውን የኤሊኖ ክስተት አለም እንድታስተናግድ አስገድዷል ብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ጠንካራ የአየር መዛባት ተከስቶ የነበረው እ.ኤ.አ ከ1997-98 መሆኑን ጠቅሶ “የዘንድሮው ክስተት ከዚያም የከፋ ነው፤ ከ1990ዎቹ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ አይነት ነው” ብሏል ቢቢሲ በዘገባው፡፡
ክስተቱ ባጋጠመባቸው ሃገራት በሚቀጥሉት ወራት ተመጣጣኝና በቂ የዝናብ ስርጭት ሊኖራቸው እንደሚችልም የትንበያ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በቀጣይ የሚኖረው የአየር ፀባይ፣ የኤስያ ሃገራትን በድርቅ ሊያስመታ በሰሜን አሜሪካ ከባድ ጐርፍ የሚያስከትል ዝናብ ሊከሰት ይችላል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ አካባቢም በጐርፍ የሚያጥለቀልቅ ዝናብ ሊፈጠር እንደሚችልና በአንፃሩ በደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል ድርቅ ሊያስከትል የሚችል የዝናብ እጥረት እንደሚኖር ከትንበያው መረዳት ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ እየተገባደደ ባለው የክረምት ወራት፣ ሰብል አብቃይና ቆላማ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ካለፉት አመታት አንፃር ድርቅን ያስከተለ ከፍተኛ የዝናብ እጥረት መፈጠሩ የሚታወስ ሲሆን በተለይ በአፋር የአደጋው መጠን የቤት እንስሳትን ለሞት እስከመዳረግ ደርሷል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ በአየር መዛባት ምክንያት ባጋጠመው የዝናብ እጥረትና መቆራረጥ 4.5 ሚሊዮን ዜጐች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ሰኔና ሐምሌ ዝናብ አጥተው የነበሩ አካባቢዎችም በነሐሴ የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደነበራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገልፆ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በሀረር፣ ድሬደዋ፣ ደብረብርሃን፣ ወሎና አፋር አካባቢዎች ላይ ሰሞኑን ዝናብ እየዘነበ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 4814 times