Saturday, 05 September 2015 08:46

በርበሬ በህገወጥ መንገድ ከአገር እየወጣ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(12 votes)

ለበዓሉ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወሰዳል ተባለ
ኤልፎራ ከ30ሺ በላይ ዶሮና ከ1 ሚሊዮን በላይ እንቁላል ለገበያ አቅርቧል
       በርበሬ በህገወጥ መንገድ ከአገር እየወጣ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ይህም ለበርበሬ ዋጋ መናር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገለፀ፡፡ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ዘለቀ ከአዲስ አመት በዓል ግብይት ጋር በተያያዘ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ  እንደተናገሩት፤ የበርበሬ ምርት ዋጋ መናርን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት፣ ምርቱ በደቡብና በሰሜን የበርበሬ አምራች በሆኑ አካባቢዎች በሚገኙ ደላሎች አማካኝነት በህገወጥ መንገድ በድንበር ሾልኮ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ በህጋዊ መንገድ እሴት እየተጨመረበት ወደ ውጭ አገር ተልኮ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኘው የበርበሬ ምርት በተጨማሪ በህገወጥ መንገድ በደላሎችና በህገወጥ ነጋዴዎች ከአገር እንዲወጣ በመደረግ ላይ ያለው የበርበሬ ምርትም የዋጋ መናሩን  ብለዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡
የበርበሬ ምርትን አስመልክቶ ጥናት መደረጉን የጠቆሙት አቶ መርከቡ፤ ባለፉት 3 ዓመታት ምርቱ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው ዘንድሮ የተመረተው 1.7 ሚሊዮን ኩንታል በርበሬ ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር በ834ሺ ኩንታል ያነሰ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የምርቱ ማነስም ለዋጋ ንረቱ መባባስ ምክንያት እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በህገወጥ መንገድ ከአገር እየወጣ ነው የተባለውን የበርበሬ ምርት ለመቆጣጠር የሚያስችል የንግድ ሚኒስቴርና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሠራተኞች የተካተቱበት ፀረ ኮንትሮባንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ የበርበሬ አምራች በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
መጪውን የአዲስ አመት በዓል ምክንያት በማድረግ ህብረተሰቡ በሚፈልጋቸው ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የማያዳግም ጥብቅ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት አቶ መርከቡ፤ እርምጃው ሱቆችን ማሸግና ንግድ ፈቃድን እስከመሰረዝ እንደሚደርስ አስታውቀዋል - እንደ ቀድሞው ለማወያየትና ለይቅርታ ጊዜ እንደማይሰጥ በመጠቆም፡፡ መንግስት ገበያውን ለማረጋጋትና ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ሸቀጦች በስፋት ለማቅረብ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን አቅም ያላቸው ነጋዴዎችም ገበያውን ለማረጋጋት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ተነግሯል፡፡
 ኤልፎራ ለበዓሉ ገበያ ከ30ሺ በላይ ዶሮዎችንና ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንቁላሎችን እንዳቀረበ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ትክክለኛውን የገበያ ሥርዓት ለማደናቀፍ በሚሞክሩ ነጋዴዎች ላይ ለሚወሰደው እርምጃ፣ ህብረተሰቡ ሊተባበርና ህገወጦችን በመጠቆም፣ ከመንግስት ጐን ሊቆም እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡   

Read 4645 times