Saturday, 05 September 2015 08:50

“ሌላ አገር ያለን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ስሙኝማ…አንድ ጊዜ አንድ ዳያስፖራ አገሩን ሁሉ ከበር መልስ ጋብዞ ጉድ ሊያሰኝ ይመጣል፡፡ ስንት መሰላችሁ የያዘው…ሁለት ሺህ ዶላር! እናላችሁ…የሆኑ አብሮ አደጎቹን ይዞ ማታ ይወጣል፡ ታዲያላችሁ…በየቦታው ሲገባ ለካ አገሪቱ የ‘ሎካል ዳያስፖራ’ አገር ሆናለች፡፡
እሱ በሁለት ብር ምናምን የመታተን ገንዘብ እየቆነጠረ ሲያወጣ ‘ሎካል ዳያስፖራዎች’…አለ አይደል…ከአንድ ኪስ ዶላር፣ ከሌላው ፓውንድ፣ ከሌላው ዩሮ ምናምን ሲመዙ ሲያይ፣ ምን አለፋችሁ… በቀን ሁለት ሰዓት ጂም የሚሠራው ሰው ልብ ድካም ሊይዘው ምንም አልቀረውም!  
እናላችሁ…ወር ሊቆይ የመጣው ሰው በሳምንቱ ተመለሰ እላችኋለሁ፡፡
ስሙኝማ… እንደ ሰሞኑ ከሆነ… አለ አይደል… “ምነው ሞንጎሊያም፣ ሀይቲም ብቻ የሆነ አገርም ሆነ ሚጢጢ ደሴት ሄጄ መንገድም ጠርጌ፣ ጠረዼዛም ወልውዬ፣ ኡበርም ነድቼ ዲያስፖራ በተባልኩ!” ያሰኛል፡፡
ልክ ነዋ…እኛ እዚህ እንደ ኮብልስቶን ከግራና ቀኝ እንላጋለን ‘ዳያስፖራ’ ደንቀፍ እንኳን ሳያደርገው… “እኔን ይድፋኝ!” አይነት ነገር እየተባለ አይደል!
በነገራችን ላይ አይደለም ኢንቬስት ሊያደርጉ በዓመት ሁለቴ ለቤተሰብ የሚልኳትን መቶ ዶላር እንኳን ወደ ሀምሳ የቀነሱ ያየን አንጠፋም፡፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንዳንድ ኮሚክ ነገሮች አሉ፡፡ እነእንትና ደግሞ ኮምፕ እንዳያስመስልብን ያላችሁት ነገር
እኔ የምለው… መቼ ይሆን ለእኛ የ“እንኳን ደህና መጣችሁ…” ሳይሆን፣ “ስንቱን ነገር ችላችሁ እንኳን አገር ውስጥ ቆያችሁ…” ተብሎ ልዩ የእራት ግብዣ የሚደረግልን! ልክ ነዋ…
በቀደም ሸገር በተደረገ ውይይት ላይ አንድ አስተያየት ሰጪ የሆነ ፕሮጀክት ለመተግበር የደረሰባቸውን መንገላታት ሲገልጹ አንድ ያሏት ነገር አለች፡፡ ምን አሉ መሰላችሁ…
“ሌላ አገር ያለን ነው የሚመስለኝ…” አሪፍ አባባል አይደል፡፡
“ሌላ አገር ያለን ነው የሚመስለኝ…” ከማለት ይሰውረንማ!  
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እኛ ‘ቤት ጠባቂዎቹ’ ምንም ነገር ላይ ‘ፕሪቪሌጅ’ ምናምን የማይሰጠንሳ! እንደውም ‘ፕሪቪሌጅ’ ማግኘቱ ይቅርብንና ወረቀቱ ላይ በተቀመጠው እንኳን የማስተናግድሳ!
አንዳንዴ ትንሽ ይሄ የግለኝነት ነገር እናያለን፡
“መኖሪያ ቤት ይሰጠን…”
“ቤት የምንሠራበት ቦታ ይሰጠን…”
“ልዩ አስተያያት ይደረግልን…”
ምናምን አይነት ‘እኔ፣ እኔና እኔ ብቻ!’ አይነት ቃና ያላቸው አስተያየቶች ስንሰማ…አለ አይደል…የሆነ የማይመች ነገር አለው፡፡
ልክ ነዋ…ለስንትና ስንት ዓመት መኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው የሚጠብቁ ስንት መቶ ሺህ ምስኪኖች ባሉባት አገር፣ ለስንትና ስንት ዓመት የድርጅት መገንቢያ ምቹ ቦታ በአቅማቸው እንዲሰጣቸው የሚጠብቁ የአገር ውስጥ ባለገንዘቦች እያሉ… “ልዩ አስተያየት ይደረግልን…” “ቅድሚያ ይሰጠን…” ምናምን አይነት አባባሎች አሪፍ አይደሉም፡፡  
አገር ማለት እኛ አይደለን! ልክ ነዋ…“ፕሪቪሌጅ ይሰጠን፣” “ማበረታቻ ይመቻችልን…” ምናምን ማለቱ ቀርቶ ፈረንካው ያላቸው… አለ አይደል… ፈራንካቸውን ሆጭ አድርገው ፋብሪካውን፣ አንዱስትሪውን፣ ትላልቅ እርሻውን…ምናምን መሥራት አሪፍ ነው፡፡
የምር…ለኢንተርኔት ካፌው፣ ለምግብ ቤቱ፣ ለሞባይል መሸጫው ምናምን ለመክፈት እኮ የእኛ ባለፈረንካዎች ይበቃሉ፡፡
ለክፉም ለደጉም… አንዱን ዳያስፖራ እናናግረውማ፡፡
እኛ፡— እሺ ዳያስፖራ ወዳጄ…በሽ አደረግናችሁ አይደል!
ዳያስፖራ፡— ወዳችሁ ነው፡፡ በሽ ባታደርጉን ወደመጣንበት ተመልስን ለሽ ነዋ የምንለው፡፡ ያኔ ማን መጥቶ ኢንቬስት እንደሚያደርግ እናያለን፡፡
እኛ፡— እሱ ላይ እንኳን ስቀህ አታስቀን፡፡ ይልቅ… ‘ለምን ይዋሻል!’ የምትባል አነጋገር ሰምተህ ታውቃለህ?
ዳያስፖራ፡— እ…ሌት ሚ ሲ… ዲሲ ሬስቱራንት ውስጥ የሰማሁ መሰለኝ፡፡
እኛ፡— ለምን ይዋሻል ከመባባላችን በፊት… ጥያቄ እንጠይቅህ…
ዳያስፖራ፡— ፕሊስ…
እኛ፡— ለምሳሌ አንተ አሜሪካ ከሄድክ ስንት ጊዜህ ነው?
ዳያስፖራ፡— አሥራ ምናምን ዓመት…
እኛ፡— እና አሁን ምንድነው የምትሠራው?
ዳያስፖራ፡— የምሠራው ምን ያደርግላችኋል…
እኛ፡— ኢንቬትስ ልታደርግ አይደል እንዴ የመጣኸው!
ዳያስፖራ፡— ዌ…ል…
እኛ፡— እሺ፣ ስንት ዶላር አጠራቅመሀል…ምነው ተኮሳተርክ?
ዳያስፖራ፡— ስንት ዶላር አጠራቅመሀል ነው ያላችሁኝ…
እኛ፡— አዎ፣ ስንት አጠራቅመሀል?
ዳያስፖራ፡— ምን ነበር ሲሉ የሰማሁት…ቆይ፣ ሌት ሚ ቲንክ…አዎ፣ ሙድ እየያዛችሁብኝ ነው እንዴ!
እኛ፡— ምን በወጣህ…
ዳያስፖራ፡— አይ ማጠራቀም…የእኔ ጌታ የቤቱ፣ የመኪናው፣ የሶፋው፣ የፍሪጁ ምናምን ብድር አናቴ ላይ እያናጠረ ስንት አጠራቀምክ ትሉኛላችሁ!
እኛ፡— ታዲያ ምንህን ነው ኢንቬስት የምታደርገው?
ዳያስፖራ፡— ማን ኢንቬስት አደርጋለሁ አላችሁ!
እኛ፡— አሀ… በቀደም እዛ አዳራሽ መዳፍህ የዝንጀሮ እንትን እስኪመስል ስታጨበጭብ በቲቪ አላየንህም…
ዳያስፖራ፡— ‘ኮምፕሌክስ’ ነው እንዴ..
እኛ፡— ተው እባክህ…አሁን እኮ ስንትና ስንት ሎካል ዳያስፖራዎች አሉ መሰለህ…ይልቅ እናንተ ፈረንካ ባይኖራችሁ እንኳን በአንዳንድ ነገር ዕድለኞች ናችሁ…
ዳያስፖራ፡— እንዴት ማለት…
እኛ፡— እንዴት ማለትማ… ማንም አይጨቀጭቃችሁ፣ ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ልክ ልካችሁን አይነግሯችሁ፣ አዲስ ሸሚዝ በለወጣችሁ ቁጥር ገንዘብ ከየት አምጥቶ ነው አይሏችሁ፣ ከእነእከሌ ጋር መዋል አብዝቷል ተብላችሁ አትፈረጁ…በሆነ ባልሆነው ወዮላችሁ አትባሉ… ይሄ ሁሉ ግን እርስ በእርስ ያላችሁን ግንኙነት አይመለከትም፡፡
ዳያስፖራ፡— ጀስት ኤ ሚኒት… ትኩረት ሲሰጠን ምን ያበሳጫችኋል..
እኛ፡— እንደውም፡ ከተበሳጨንም የሚያበሳጨን እናንተ ትኩረት ማግኘታችሁ ሳይሆን እኛ ችላ መባላችን ነው….እንደ እናንተ እንክብካቤ ለማግኘት የግድ ውጪ አገር መሄድ አለብን እንዴ! ስማማ…እኛ ገንዘቡ እንዳለ ሆኖ በጣም የሚያስፈልገን ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
ዳያስፖራ፡— ምንድነው?
እኛ፡— ዕውቀት! ይሰማሃል…ያስቸገረን የዕውቀት እጥረት! የተማሩ የበቁ፣ የነቁ ዳያስፖራ ሀበሾች ዕውቀታቸውን ይዘው ቢመጡልን አሪፍ ነው፡፡
የምር ግን…አለ አይደል…አቅም ያላቸው ወገኖቻችን ከየትም ቢመጡ ከየትም አሪፍ ነው፡፡ ገንዘብ ያስፈልገናል፣ ዕውቀት ያስፈልገናል…ብዙ የሚያስፈልጉን ነገሮች አሉ፡፡ ግን ደግሞ…‘እንደ ስለት ልጅ ተንከባከቡን’ አይነት አሪፍ አይደለም፡፡ እዚህ ያለ ዜጋ አልፈታለት ያሉ አንድ ሺህ አንድ ችግሮች አሉበት፡፡ እናማ…ምን መሰላችሁ…ከልጅ ልጅ መለየት ሳይሆን የሁሉም ችግሮች አንድ ላይ የሚፈቱበት ነገር ቢኖር አሪፍ ነው፡፡
እናማ አቅም ያላቸው… “እንደ ዕንቁላል ሳሱልን…” ምናምን አይነት ነገር ቀንሰው ፈረንካቸውን ሥራ በሚፈጥሩና ምርት በሚያስገኙ ነገሮች ላይ ቢያውሉ አሪፍ ነው፡፡
እግረ መንገዳችንን… አሰሱን ገሰሱን ይዘው የሚመጡ ዳያስፖራ ወገኖቻችን እንዳሉም ማስታወሱ አሪፍ ነው፡፡  በቀደም በአዳራሹ ከሞላው አንድ መቶኛው እንኳን ኢንቬስት ቢያደርግ ስንትና ስንት ሰው የሥራ ዕድል ያገኝ ነበር፡፡
ብቻ እስከ ተከታዩ ዓመት የዳያስፖራ በዓል አዳራሹን ሞልቶት ከነበረው ህዝብ ስንቱ “ይኸው ኢንቬስት ለማድረግ ካጠራቀምኩት ጥሪት ቀንሼ አምጥቻለሁ…” እንደሚልና ስንቱ ደግሞ “ለምንድነው ለመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እስካሁን ያልተሰጠን…” እንደሚል ለማየት ያብቃንማ!
“ሌላ አገር ያለን ነው የሚመስለኝ…” ከማለት ይሰውረንማ!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2912 times