Saturday, 05 September 2015 09:49

ማሬ ዲባባ ማራቶንን ትመራለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 * ዘንድሮ ብቻ ገቢዋ ከ1 ሚሊዮን ዶላር አልፏል

    በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የተሳትፎ ታሪክ በማራቶን የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደችው ማሬ ዲባባ፤ ማራቶንን በየዘርፉ በመሪነት ተቆጣጥራለች፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ በሰፈረው አሃዛዊ መረጃ መሠረት በሴቶች ማራቶን ማሬ ዲባባ በ1351 ነጥብ አንደኛ ናት፡፡ ባለፈው ሰሞን በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ከሆነች በኋላ ደግሞ በ2015 የዓለም ታላላቅ ማራቶኖች (World Marathon Major Series) ሊግ በነጥብ 1ኛ ሆና እየመራች ሲሆን፤ የውድድር ዘመኑን በአሸናፊነት ልትጨርስ ትችላለች፡፡
በሌላ በኩል በቤጂንጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ሻምፒዮን ስትሆን በሽልማት ካገኘችው 60ሺ ዶላር በተጨማሪ ከቡድን ሽልማትና ከስፖንሰር ጥቅሟ ጋር ገቢዋ በዕጥፍ  የጨመረላት ማሬ ዲባባ ከማራቶን ሊግ አሸናፊነቷ ጋር የዘንድሮ ገቢዋ ብቻ ከ1 ሚሊዮን ዶላር ሊያልፍ ችሏል፡፡ በዓለም አቀፉ የጐዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር (ARRS) ማሬ ዲባባ ከ2008 እ.ኤ.አ በጐዳና ላይ ሩጫዎች ከ15 በላይ ድሎች በማስመዝገብ 534,465 ዶላር በሽልማት ገንዘብ መሰብሰቧ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በውድድር ዘመኑ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ 6 ታላላቅ የማራቶን ውድድሮችን ተንተርሶ በሚሰጥ ነጥብ የማራቶን ሊግ አሸናፊ የሚወሰን ሲሆን፤ በየፆታ መደቡ በነጥብ መርተው የሚጨርሱ አትሌቶች እያንዳንዳቸው 500ሺ ዶላር ይሸለማሉ፡፡  
ማሬ ዲባባ ቤጂንግ ላይ የዓለም ሻምፒዮና ከሆነች በኋላ የማራቶን ሊጉን በ42 ነጥብ አንደኛ ሆና እየመራች ሲሆን፤ በቅርብ ርቀት የምትፎካከራት የኬንያዋ ሄለን ኬፕሮን በ32 ነጥብ ነው፡፡
ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ብርሃኔ ዲባባ እና ትዕግስት ቱፋ እንዲሁም ሌላዋ ኬንያዊት ካሮሊን ሮቲች በ25 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ተጋርተው ይከታተላሉ፡፡ በተያያዘ በወንዶች ምድብ በ25 ነጥብ የማራቶን ሊጉን መሪነት የተቆጣጠረው ቤጂንግ ላይ የብር ሜዳሊያ ያገኘው የማነ ፀጋዬ ነው፡፡ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከኬንያ፣ ግርማይ ገ/ስላሴ ከኤርትራ እንደሻው ንጉሤ እና ሌሊሣ ዴሲሳ ከኢትዮጵያ በእኩል 25 ነጥብ ይከተላሉ፡፡
የማራቶን ሊግ አሸናፊዎች የሚወሰኑት በ6 የዓለማችን ታላላቅ ማራቶኖች ባስመዘገቡት ውጤት በሚሰጠው ነጥብ ይሆናል፡፡ ማሬ ዲባባ በ2014 የቦስተን ማራቶን 3ኛ እንዲሁም በቺካጐ ማራቶን 1ኛ ደረጃ ከማግኘቷም በላይ፤ በ2015 በቦስተን ማራቶን 2ኛ እንዲሁም በዓለም ሻምፒዮና 1ኛ ከሆነች በኋላ ያስመዘገበችው ነጥብ 42 አድርሳለች፡፡  በወርልድ ማራቶን ሜጀር ሲሪዬስ ታሪክ ኢትዮጵያ ለ3 ጊዜያት የማራቶን ሊጉን አሸናፊዎች አስመዝግባለች፡፡
በ2007 እና በ2008 እ.ኤ.አ አከታትላ ያሸነፈችው ጌጤ ዋሚ ስትሆን በ2003 እ.ኤ.አ ደግሞ ፀጋዬ ከበደ ሊጉን በነጥብ መሪ ሆነው በማጠናቀቅ በነፍስ ወከፍ 500ሺ ዶላር አግኝተዋል፡፡


Read 1380 times