Print this page
Saturday, 05 September 2015 09:53

ኢትዮጵያ ሲሼልስን በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅባታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ2017 እ.ኤ.አ ላይ ጋቦን ለምታስተናግደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉት የምድብ ማጣሪያዎች በ2ኛ ዙር ግጥሚያዎች ዛሬ እና ነገ ይቀጥላሉ፡፡  በምድብ 10 ከአልጀሪያ፣ ሌሶቶና ሲሼልስ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲሆን በ2ኛ ዙር የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያውን ዛሬ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ከቻለ የማለፍ ዕድሉን ያሰፋለታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2ኛ ዙር የማጣሪያ ግጥሚያውን ዛሬ ከሜዳው ውጭ በቪክቶሪያ ከተማ በሚገኘው በስታድ ሊንቴ ስታድዬም ከሲሸልስ አቻው ጋር የሚያደርግ ሲሆን ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት የሚመሩና ኮሞሮሳዊው አሊ አዴላይድ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ከዚሁ ወሳኝ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ሳምንት ቀደም ብሎ የአቋም ፈተሻ ግጥሚያ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ከሜዳው ውጭ አድርጐ 3ለ1 መሸነፉ አይዘነጋም፡፡ ዛሬ ከሲሼልስ ጋር በሚያደርገው የነጥብ ጨዋታ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ የማጣሪያውን ጉዞ ያደላድልለታል፡፡ በምድብ 10 ሌላ ጨዋታ ነገ አልጀሪያ ከሜዳው ውጭ በማሱሩ ከተማ ለሚገኘው ሲተሰቶ ስታድዬም ከሌሶቶ ጋር ትገናኛለች፡፡ በምድብ 10 ላይ አልጀሪያ በመጀመሪያ ጨዋታዋ ሲሼልስን በሜዳዋ 4ለ0 ካሸነፈች በኋላ በሦስት ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ ትመራለች፡፡ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዋ በሜዳዋ ሌስቶን 2ለ1 አሸንፋ በ3 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ሌሶቶ ያለምንም ነጥብ በ1 የግብ ዕዳ ሦስተኛ ደረጃ እንዲሁም ሲሼልስ ያለምንም ነጥብ በ4 የግብ ዕዳ መጨረሻ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
በታዋቂው የእግር ኳስ ዘጋቢ ድረገፅ ጐል ንባቢዎች ለምድብ 10 የ2ኛ ዙር የማጣሪያ ግጥሚያዎች የተለያዩ የውጤት ግምቶችን ተሰንዝረዋል፡፡ በአልጀሪያ እና ሌሶቶ ጨዋታ 76% የድረገፁ አንባቢዎች የአሸናፊነቱን ግምት ለአልጀሪያ ሲሰጡ፤ ለኢትዮጵያ እና ለሴሼልስ ጨዋታ ደግሞ 67% የማሸነፍ ዕድሉ ለኢትዮጵያ የተተነበየ ሆኗል፡፡ የምድብ 10 የ3ኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታዎች ከ7 ወራት በኋላ የሚቀጥሉ ሲሆን ሲሼልስ በሜዳዋ ሌሶቶን ስታስተናግድ ኢትዮጵያ በድጋሚ ከሜዳ ውጭ በመጓዝ አልጀሪያን ትገጥማለች፡፡

Read 3489 times