Saturday, 05 September 2015 10:29

የግብጽ ምርጫ በ139 የአለም አገራት ጭምር ይከናወናል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ መንግስት ሞሃመድ ሙርሲን ከመንበረ መንግስቱ አስወግዶ ስልጣን ከያዘ በኋላ በአገሪቱ የመጀመሪያው በሚሆነውና ከሚጠበቀው ጊዜ ዘግይቷል በሚል ሲተች ቆይቶ በጥቅምት ወር ሊካሄድ ቀን በተቆረጠለት የግብጽ ፓርላማ ምርጫ፣ በውጭ አገራት የሚገኙ ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ መፈቀዱ ተዘገበ፡፡
ኦል አፍሪካን ዶት ኮም ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በርካታ ግብጻውያን በሚኖሩባቸው 139 የተለያዩ የአለማችን አገራት በሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ዜጎች ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማስቻል አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
በምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃምዲ ሳንድ ሎዛ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ በ139 አገራት ውስጥ በሚገኙ የግብጽ ኤምባሲዎች የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው ዜጎች ድምጽ እንዲሰጡ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ዘገባው ገልጧል፡፡
ማክሰኞ በተጀመረው የአገሪቱ የምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ 2 ሺህ 745 ያህል ዜጎች በተወዳዳሪነት መመዝገባቸውንና ምዝገባው ለ10 ቀናት ያህል እንደሚቆይ የግብጽ ከፍተኛ የምርጫ ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን፣  55 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውንም አሃራም የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የምርጫ ኮሚሽን፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ምርጫው በጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚካሄድና የድምጽ አሰጣጡም ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ማስታወቁን የጠቆመው የቴሌግራፍ ዘገባ፣ አገሪቱ ከሰኔ ወር 2012 አንስቶ ፓርላማ እንደሌላትና ምርጫ እንድታካሄድ የተወሰነው ቀደም ብሎ ቢሆንም በፕሬዚዳንቱ ቸልተኝነት መዘግየቱን አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፤ ከነባር የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ለመቀላቀልም ሆነ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በቀጣዩ ምርጫም ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማይወዳደሩ ጠቁሟል፡፡
ምርጫው ከተያዘለት ጊዜ እንዲራዘምና ባለፈው መጋቢት ወር እንዲካሄድ ቢወሰንም፣ የአገሪቱ ፍርድ ቤት አንዳንድ የምርጫ ህጎች ህገመንግስቱን የሚጥሱ ናቸው በማለት ምርጫው ዳግም እንዲራዘም መወሰኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1802 times