Saturday, 05 September 2015 10:30

የሙጋቤ ሚስት በጎዳና ላይ ነጋዴዎች ሊከሰሱ ነው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሚስት ግሬስ ሙጋቤ፤ ከሃራሬ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች የተዘረፉ ልባሽ ጨርቆችንና አልባሳትን ያለአግባብ ለፖለቲካ ደጋፊዎቻቸው በማከፋፈላቸው ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሆነ ተዘገበ፡፡
የሃራሬ ከተማ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች ፖሊስ የወረሰባቸውን ልባሽ ጨርቆችና አልባሳት ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው አከፋፍለዋል በሚል ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ የዚምባቡዌ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ድርጅት በሴትየዋ ላይ ክስ እንደሚመሰርት ማስታወቁን ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ህገወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ መከልከሉን ያስታወሰው ዘገባው፣ የሃራሬ ከተማ ፖሊስም በቅርቡ ባደረገው አሰሳ፣ በሺህዎች ከሚቆጠሩ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በርካታ ቶን የሚመዝኑ ልባሽ ጨርቆችና ሌሎች ቁሳቁሶችን መንጠቁን ገልጧል፡፡
ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፣ ባለፈው ሳምንት በሰሜናዊ ዚምባቡዌ በተከናወነ የፖለቲካ ቅስቀሳ ላይ፣ ፖሊስ ከነጋዴዎቹ የነጠቃቸውን 150 ቦንዳ ልባሽ ጨርቆችና አልባሳት ዛኑፒኤፍ ለተባለው ፓርቲያቸው ደጋፊዎች በነጻ ሲያከፋፍሉ መታየታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ ድርጊቱን ያወገዘው የዚምባቡዌ መደበኛ ያልሆኑ ዘርፎች ድርጅትም ክስ ለመመስረት እየተዘጋጀ መሆኑን ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ፤ የግል ንብረታቸው ያልሆነን ልባሽ ጨርቅና አልባሳት ለደጋፊዎቻቸው ማከፋፈላቸው ህገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ ይሄን ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ በአፋጣኝ ክስ እንመሰርታለን ብለዋል፣ የድርጅቱ ዳይሬክተር ፕሮሚዝ ክዋናንዚ፡፡
ግሬስ ሙጋቤ ከነጮች የተወረሱ ሰፋፊ መሬቶችን የግል ይዞታቸው በማድረግ በአገሪቱ አቻ እንደማይገኝላቸው የጠቆመው ዘገባው፣ ልባሽ ጨርቆቹን ሲያከፋፍሉ በደስታ ተውጠው ገዝተው እንዳመጡላቸው ለደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ እንደነበርም አመልክቷል፡፡
በርካታ የአገሪቱ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች በፖሊስ እየታደኑ እየተደበደቡና ንብረቶቻቸው እየተወረሰባቸው መሆኑንና  በ17 ያህል ነጋዴዎች ላይ ክስ መመስረቱንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 2513 times