Saturday, 05 September 2015 10:32

እስያ በአለም የኢኮኖሚ እድገት መሪነቷ እንደምትቀጥል ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአለም ኢኮኖሚ እድገት ከተገመተው በታች ይሆናል ተብሏል
             አዝጋሚው የቻይና ኢኮኖሚ በአለማችን ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል
                           አህጉረ እስያ በአለም ኢኮኖሚ መሪነቷ ትቀጥላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ማስታወቃቸውን ዘ ሂንዱ ታይምስ ዘገበ፡፡
አለማቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ከዚህ በፊት ተገምቶ ከነበረው አነስ ባለ መጠን በመካከለኛ ደረጃ ላይ ሆኖ እንደሚቀጥል የገለጹት ክርስቲያን ላጋርድ፣ በአለማችን የኢኮኖሚ እድገት መሪነቱን የያዘችው እስያ፤ ምንም እንኳን የእድገት መጠኗ እየቀነሰ ቢሆንም በመሪነቷ ትቀጥላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢንዶኔዥያ ያመሩትና ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ ጋር በአለማቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ዙሪያ የመከሩት ላጋርድ፣ ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ አለማቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ ኢንዶኔዢያን በመሳሰሉ ያላደጉ አገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ገልጸዋል፡፡
የአምናው የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.4 በመቶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ አይ ኤምኤፍ ባለፈው ሃምሌ ወር ላይ የዘንድሮው የአለማችን የኢኮኖሚ ዕድገት 3.3 በመቶ ሊያድግ ይችላል ብሎ መገመቱንና ዕድገቱ ግን ያነሰ ሊሆን እንደሚችል ዳይሬክተሯ መናገራቸውን አስረድቷል፡፡ አምና 2.4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበችው አሜሪካ፤ ዘንድሮ በ2.5 በመቶ ታድጋለች ተብሎ መገመቱን የጠቀሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት 7.4 በመቶ ያደገችው ቻይና በበኩሏ፤ የዕድገቷ መጠን ቀንሶ 6.8 በመቶ ሊደርስ ይችላል ተብሎ እንደተገመተ ጠቁሟል፡፡
ያደጉ አገራት ኢኮኖሚ በተወሰነ መጠን ማገገም ይታይበታል ቢባልም፣ በማደግ ላይ ያሉ ኢኮኖሚዎች ግን ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ ይላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ክርስቲያን ላጋርድ ተናግረዋል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ ክርስቲያን ላጋርድ አዝጋሚው የቻይና ኢኮኖሚ በአለማቀፉ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ዘግቧል፡፡
“የቻይና ኢኮኖሚ እድገት በሌሎች የአለማችን አገራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ከዚህ በፊት ከተገመተው በላይና የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለሆነም ቻይና የጀመረቻቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማስቀጠል ይገባታል” ብለዋል ላጋርድ፡፡
በቻይና ኢኮኖሚ ላይ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ነዳጅና ማዕድናትን የመሳሰሉ ሸቀጦች ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉን የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህም ሸቀጦቹን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ብራዚልና ሩሲያን የመሳሰሉ አገራት ክፉኛ እየተጎዱ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

Read 3623 times