Friday, 11 September 2015 09:27

በጊዜ የመጣ እንግዳ፣ እንደረዳህ ይቆጠራል!

Written by 
Rate this item
(15 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት የአዕምሮ ህመምተኞች የእንቁጣጣሽ ምግብ ሊበሉ በገበታ ዙሪያ ሆነው ይጨዋወታሉ፡፡
አንደኛው - አንድ ዕንቁላል ነው ያለው ማን ይብላት?
ሁለተኛው - ሁለት ላይ ማካፈል ነዋ በቃ
አንደኛው - ማን ይከፍለዋል?
ሁለተኛው - ወይ እኔ ወይ አንተ ነና
አንደኛው - እኔ አልገባበትም
ሁለተኛው - ለምን?
አንደኛው - በትክክል ዕንቁላሏን ሁለት እኩል ቦታ ለመክፈል አልችልም
ሁለተኛው - እንግዲያው እኔው ራሴ እከፍለዋለሁ
አንደኛው - ብትሳሳት ግን መልሰህ ትገጥመዋለህ - ዕወቅ
ሁለተኛው - እንደሱ ከሆነማ እኔም አልገባበትም!
አንደኛው - ታዲያ ምን እናድርግ?
ሁለተኛው - ዕጣ እንጣል
አንደኛው - ዕጣውን ማን ይፅፋል?
ሁለተኛው - ወይ እኔ ወይ አንተ ነሃ!
አንደኛው - እኔ አልገባበትም
ሁለተኛው - ለምን?
አንደኛው - ምልከት ብታረግበትስ?
ሁለተኛው - በደምብ ጠጋ ብለህ እየኛ!
ይህን ሲባባሉ አንድ መንገደኛ ያይ ኖሮ፣
“እንግዲህ ዕጣ እስክትጣጣሉ ድረስ‘ኮ ዕንቁላሉ ቀዘቀዘ” አላቸው፡፡
አንደኛው ብድግ አለና፤
“ዕጣ እማንጣጣለው በአንድ ጉዳይ ብቻ ነው”
መንገደኛው፤
“በምን?”
አንደኛው፤
“ያንተን መንጋጭሌ በማውለቅ!”
አለና መንገደኛውን አገጩን በቡጢ አነገለው!
*  *   *
ያለጉዳያችን ጣልቃ ስንገባ የሚገጥመን ነገር አይታወቅም፡፡ ራስን ችሎ በራስ ተማምኖ መጓዝ መልካም ነው፡፡ በአዲስ ዓመት የማያጠራጥር በምግብ ራስን መቻልን ይስጠን፡፡
በአዲሱ ዓመት ለትንሽ ለትልቁ ዕጣ የማንጣጣልበት እንዲሆንልን እንፀልይ፡፡
አዲሱ ዓመት የተሻለ ሹምና መልካም አስተዳደርን የሚሰጠን እንዲሆንልን እንመኝ፡፡
አዲሱ ዓመት ተስፋችን የሚለመልምበት፣ ከድርቅ የምንርቅበት ያድርግልን፡፡
አዲሱ ዓመት ፍትህ ርትዕ የሚሰፍንበት፣ የተዛባ የሚቃናበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት ከአምና የምንማርበት፣ የዘራነውን የምንለቅምበት፣ የወለድነውን የምንስምበት፣ ትምህርታችንን ይግለጥልን የምንልበት ይሁንልን፡፡ ከመጠምጠም መማር የሚቀድምበት፡፡ የተማረ የሚከበርበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት የማንወሻሽበት፣ ግልፅነትን የምናዳብርበት፣ ተንኮልን የምናስወግድበት ያድርግልን!
አዲሱ ዓመት ደግመን ደጋግመን ራሳችንን የምንመረምርበት፣ አንድነታችንን የምናይበት፣ ባህላችንን የምናከብርበት፣ በማንነታችን የምንኮራበት ያድርግልን፡፡
አዲሱ ዓመት አዲስ ትውልድ የምንኮተኩትበት፣ አበባ የምናሰባስብበት፣ ፍሬ የምንለቅምበት ይሁንልን፡፡
አዲሱ ዓመት ምሬት ወደ ምርት የሚለወጥበት እንዲሆን ያድርግልን!
ከሁሉም በላይ አዲሱ ዓመት የጊዜን አጠቃቀም የምናውቅበት፣ አርፍደን የማንፀፀትበትና “በጊዜ የመጣ እንግዳ እንደረዳህ ይቆጠራል” የሚለውን ተረት በቅጡ የምናጤንበት እንዲሆንልን፣ ትጋቱን ይስጠን!


           መልካም አዲስ ዓመት!

Read 4395 times