Friday, 11 September 2015 09:44

በ2008 በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

  የቅርብ ተቀናቃኝ የነበረችው ኬንያ በዕጥፍ ብልጫ እያሳየች ነው…
   በዓለም ሻምፒዮናው የኬንያ ገቢ 7.2 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን የኢትዮጵያ ድርሻ ከ500 ሺ ዶላር በታች ነው፡፡
  በ31ኛው ኦሎምፒያድ ኬንያ 7 ወርቅ፣ 5 ብርና 5 ነሐስ፤ ኢትዮጵያ 3 ወርቅ፣ 3 ብርና 2 ነሐስ ያገኛሉ፡፡ ኢንፎስትራዳ

   የቻይናዋ ዋና ከተማ ቤጂንግ ባስተናገደችው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ተሳክቶለታል ለማለት ያዳግታል፡፡ ሁሌም የውጤት መለኪያ የቅርብ ተቀናቃኝ የነበረችው ኬንያ ነች፡፡ ባለፉት 2ሻምፒዮናዎች እና የለንደን ኦሎምፒክ ኬንያን መፎካከር ለኢትዮጵያ ያዳገተ መስሏል፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ባስመዘገበው ውጤት መርካት አይቻልም፡፡ በተለይ በወንድ አትሌቶች ያጋጠመው ሁኔታ ያስደነግጣል፡፡ በረጅም ርቀት አትሌቲክስ የኢትዮጵያ መሪነት ሙሉ ለሙሉ እየተነጠቀ ነው፡፡ ኬንያውያን ይቅርና ሞፋራህ ብቻውን ኢትዮጵያን ከኋላ ማስከተል ቀጥሏል፡፡ የውጤት ማሽቆልቆል ከምን የመጣ ነው? በተፎካካሪነት መድከምስ ለምን ይታያል? በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብዙ ክፍተቶች መኖራቸውን እየካዱ መቀጠል አያስፈልግም፡፡ በታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በከፍተኛ ደረጃ ተዘጋጅቶ መሳተፍ ይኖርበታል፡፡ ባለአቅምና ልምድ ተጠቅሞ የመዘጋጀትና የመሳተፍ ትኩረት ከሁሉም ባለድርሻ አካላትም ያስፈልጋል፡፡ በብራዚል ከተማ፤ ሪዮ ዲጄኔሮ 31ኛው ኦሎምፒያድ ሊካሄድ ከዓመት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ በታላቁ ኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያን አትሌቲክ የሚያነቃቁ ውጤቶች ለማስመዝገብ ከወዲሁ መነሳሳት አለብን፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለ ድርሻ አካላት ብዙ ናቸው፡፡ ስፖርቱ የአትሌቲክስ የፌዴሬሽኑ ብቻ አይደለም፡፡ መገናኛ ብዙሃናት፤ የስፖርት ምሁራን፣ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ታላላቅ አትሌቶች፣ ክለቦች፣ አካዳሚዎች… ወዘተ መረባረብ አለባቸው፡፡ በፌዴሬሽኑ የአስተዳደር፣ የእድገት እና የስልጠና መዋቅር አገር አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡
በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ሜዳሊያ ስብስብ ከበፊቱ ያልተሻለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ በወቅታዊ የስልጠና መዋቅር እየተሠራ አይደለም፡፡ በሌሎች አገራት ካለው የዕድገት ደረጃ አንፃር በጥናት የታገዘ ዝግጅት እንዳልተደረገም በገሃድ መታዘብ ተችሏል፡፡ በአትሌቶች ዝግጅት ላይ የአየር ሁኔታና ተስማሚነትን በአሣማኝ ሁኔታ የተካሄደ አልነበረም፡፡ በአመጋገብ በስነልቦና ጠንካራ ስራዎች እንዳልተሠሩም ይገለፃል፡፡ ወቅቱን የጠበቁ የአሰራር ስርዓቶች አለመዘርጋታቸውም ይስተዋላል፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ ሌሎች ብዙ ችግሮችን መመልከት ይቻላል፡፡ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልግ ነው፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው ድክመት ቢያንስ በመጭው ኦሎምፒክ እንዳይደገም ብዙ መሠራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ የቅርብ ተቀናቃኝ የነበረችው እና አሁን በዕጥፍ ብልጫ ማሳየት የጀመረችውን ኬንያ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው በድምሩ 16 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፣ 5የብር፣ 5 የነሐስ) በማስመዝገብ ኬንያ ከዓለም 1ኛ ሆና ጨርሳለች፡፡ በከፍተኛ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድር አፍሪካዊ አገር የሜዳልያ ሰንጠረዥን በመሪነት ሲያጠናቅቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡  ጃማይካ በ12 (7 የወርቅ፣ 2 የብርና 3 የነሐስ) ሜዳልያዎች፤ አሜሪካ በ18 (6 የወርቅ፣ 6 የብርና 6 የነሐስ) ሜዳልያዎች ታላቋ ብሪታንያ በ7 (4 የወርቅ፣ 1 የብርና 2 የነሐስ) ሜዳልያዎች እስከ 4 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ3 የወርቅ 3 የብርና 2 የነሐስ በአጠቃላይ በ8 ሜዳልያዎች 5ኛ ደረጃ ነበራት፡፡ የሜዳልያው ውጤት ኬንያ ያላትን ዕጥፍ ብልጫ የሚያመላክት ነው፡፡ ባለፉት 15 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ኬንያ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳልያ ብዛት 50 ሲደርስ የኢትዮጵያ 25 ነው፡፡
በሻምፒዮናው የአፍሪካ አገራት ከሰበሰቡት 31 ሜዳልያዎች ከፍተኛውን ድርሻ ኬንያና ኢትዮጵያ ይወስዳሉ፡፡ ከሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሌላ የወርቅ ሜዳልያ ድል ያስመዘገቡት ኤርትራ እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡  የደቡብ አፍሪካ የወርቅ ሜዳልያ በ400 ሜትር ወንዶች የተገኘው ነው፡፡ በተጨማሪ በ200 ሜትር ወንዶች የነሐስ ሜዳልያም ተመዝግቧል፡፡ ስለሆነም ደቡብ አፍሪካ ከአህጉሩ በውጤታማነት በ3ኛ ደረጃ ትጠቅሳለች፡፡ የሻምፒዮናው አስደናቂ ውጤት የተባለው ደግሞ በማራቶን ለኤርትራ የተገኘው የወርቅ ሜዳልያ ነው፡፡ ከ4ቱ አገራት ውጭ የሜዳልያ ውጤት ያስመዘገቡት ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ግብጽ በጦር ውርወራ የብር ሜዳልያ፣ ቱኒዚያ በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ፣ ሞሮኮ በ1500 የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም ኡጋንዳ በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝተዋል፡፡  አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመረጃ ምንጮች ከኬንያና ከኢትዮጵያ ባሻገር የሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራት የነበራቸውን ተሳትፎ ደካማ ብለውታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው ከአፍሪካ አህጉር ከ27  በላይ አገራት የተወከሉት በ1 አትሌት ብቻ ነበር፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ በስተቀር ከሌለው የአፍሪካ ክፍል በወንድ አትሌቶች ከፍተኛ የተሳትፎ ብቻ መቀነስ ተስተውሏል፡፡ አጭር ርቀት እና በሌሎች የሜዳ ላይ ስፖርቶች የሚታወቁት የሰሜንና  የምዕራብ አፍሪካ አገራትም አልሆነላቸውም፡፡ በተለይ ናይጀሪያ ጠንካራ ተሳትፎ አልነበራትም፡፡   
ኬንያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በሜዳልያ ስብስብ በአንደኛነት ጨርሳ ደረጃ አዲስ ታሪክ ማስመዝገቧ ድንገተኛ ክስተት አይደለም፡፡ የአገሪቱን አትሌቲክስ በበላይነት የሚመራው ተቋም የሚከተለው አቅጣጫ እንዳመጣው ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሰሞኑን እንኳን በዓለም ሻምፒዮናው የተገኘውን ውጤት በኦሎምፒክም ለመቀጠል የተጀመሩ ስራዎች ማስረጃ ይሆናሉ፡፡ “አትሌቲክስ ኬንያ” የተባለው የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአገሪቱ ዋና ዋና የክልል ከተሞች የተደራጁ የስልጠና ቦታዎችንና  ቢሮዎችን ለመክፈት ወስኗል፡፡ በጦር ውርወራ እና በ400 ሜትር መሰናክል በተገኙ ድሎች በመነቃቃትም በአጭር ርቀትና በሜዳ ላይ ስፖርቶች ለመስራት ሃሳብ ቀርቧል፡፡ ፌዴሬሽኑም ለአትሌቶች የሚመጥን ዘመናዊ የስልጠና መዋቅር፤ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ እንዲሁም ዘመናዊ የስፖርት መሣሪያዎችና ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን ባካተቱ ግብረ ኃይል መስራት እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ኬንያ በዓለም ሻምፒዮና ያገኘችው ስኬት ከመላው ዓለም አድናቆት አትርፎላታል፡፡ ከኢትዮጵያ ተቀናቃኝነት በላቀ ደረጃ እያመለጠች መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የኬንያ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው ከ7.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አጋብሰዋል፡፡ በአንፃሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ድርሻ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ በኬንያ የዓለም ሻምፒዮና ስኬት በቂ ምርምርና ጥረት ማድረግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስራ ነው፡፡ በተለያዩ ዘገባዎች ከቀረቡ ትንተናዎች ለመረዳት የሚቻለው ግን የአገሪቱ አትሌቲክስ በከፍተኛ የውጤት እና የዕድገት ደረጃ ላይ መሆኑን ነው፡፡ የኬንያ አትሌቶች ውጤታማነት በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ከመኖራቸው ሁኔታ ጋር ተያይዞ በስፋት መነሳቱ የተለመደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን በኬንያ አትሌቲክስ ዘመናዊና ምቹ የአሠራር መዋቅር መዘርጋቱን የሚገልፁ መረጃዎች አሉ፡፡ በኬንያ አትሌቲክስ ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች በመላው አገሪቱ ተስፋፍተዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ድጋፍ ሰጪ ስፖንሰሮች መብዛታቸውም የአካዳሚዎችና የማሠልጠኛዎችን አቅም አሳድጓል፡፡  እንዲሁም የኬንያ መንግስት በወጣቶች ላይ ያተኮረ የአትሌቲክስ የእድገት አቅጣጫዎች ላይ በትኩረት መሥራቱም ይጠቀሳል፡፡ ለኬንያ አትሌቶች የተዘረጋው ጥሩ የስልጠና መዋቅር ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የሚነሳ ነው፡፡ ከዚያም በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በክለብ ደረጃ የስልጠና ሂደቱ ይቀጥላል፡፡  ፕሮፌሽናል አትሌቶችን በየጊዜው እንዲወጡ አስችሏል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ተተኪዎችን ለማፍራት አቅሙ የዳበረውም በዚያ ምክንያት ነው፡፡ በተጨማሪም የሜዳልያ ስብሰባቸውን ለማብዛት በሌሎች የውድድር መደቦችም ላይ አተኩረውም ሰርተዋል፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አሠልጣኞችና ማናጀሮችም ከሀገር ውስጥም ከውጭም በስፋት እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ የስፖርት ምሁራን እና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በየጊዜው በመጽሐፍ፣ በቪዲዮ ምስልና በጥልቅ ዘገባዎች በኬንያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ምርምር በማድረጋቸውም ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የስፖርት ዳታዎችን  የሚያሰባስብና የሚያሰላ ግዙፍ ተቋም ኢንፎስትራዳ በኦሎምፒክ የሜዳሊያ ስኬት ቅድመ ትንበያ ተሰርቷል፡፡ በ2016 እ.ኤ.አ ሪዮዲጄኔሮ በምታስተናግደው 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ነው፡፡ የሜዳልያ ትንበያውን ኢንፎስትራዳ በየጊዜው እየከለሰ ሲያሰራጭ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ተቋም 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በተገባደደ  ማግስት የሜዳልያ ትንበያውን በመከለስ አስታውቋል፡፡ በኢንፎስትራዳ የሜዳልያ ትንበያ መነሻነት የተሠሩ ትንታኔዎች እንደሚያመለክቱት በሪዮ ኦሎምፒክ አውስትራሊያ የወርቅ ሜዳልያዋ በእጥፍ እንደሚጨምር፤ አዘጋጇ ብራዚል 4 የወርቅ ሜዳልያዎችን እንደምታጣ፤ ፈረንሳይ ደረጃዋ ቢቀንስም ካለፈው ኦሎምፒክ በተሻለ ተጨማሪ የወርቅ ሜዳልያዎች እንደምታገኝ፤ ጀርመን ከፈረንሳይ የተሻለ ውጤት እንደምታስመዘግብ፤ ታላቋ ብሪታንያ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች እንደምትነጠቅ፤ ቻይና ውጤቷ እንደሚያሽቆለቁልና፤ ራሺያ በከፍተኛ ተፎካካሪነት እንደሚሳተፉ በዝርዝር ተተንትኗል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ላይ ለንደን ባስተናገደችው 30ኛው ኦሎምፒያድ በድምሩ 104 ሜዳሊያዎች ያገኘችው አሜሪካ በኢንፎስትራዳ ትንበያ 10 የወርቅ ሜዳልያ ተቀንሶባታል፡፡ በሪዮዲጄኔሮ በምታገኘው አጠቃላይ የሜዳልያ ብዛት ከዓለም መሪነቱን ባትነጠቅም ታገኛለች የተባለው 95 የወርቅ ሜዳልያዎችን ነው፡፡ በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳልያ ሰንጠረዡን በአንደኝነት የጨረሰችው ኬንያ 31ኛው ኦሎምፒያድ ላይ 17 ሜዳልያዎች (7 ወርቅ፣ 5 ብርና 5 ነሐስ) እንደምታገኝ ተገምቷል፤ ለኢትዮጵያ የተተነበየው ደግሞ 3 የወርቅ 3 የብርና 2 የነሐስ በአጠቃላይ 8 ሜዳልያዎች ነው፡፡ በሜዳልያ ስብስባቸው ኬንያ ከዓለም 13ኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ 27ኛ ደረጃ እንደሚኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡  
ኢንፎስትራዳ 31ኛው ኦሎምፒያድ ከመጀመሩ 1 ዓመት ቀደም ብሎ ይፋ ያደረገው የሜዳሊያ ትንበያ ነው አሜሪካ 1ኛ ደረጃ የያዘችው በ95  (41 የወርቅ፣ 20 የብር፣34 የነሐስ) ሜዳልያዎች ነው፡፡ ቻይና በ79 (33 የወርቅ፣ 28 የብር፣ 18 የነሐስ) ሜዳሊያዎች፣ ራሽያ በ71 (26 የወርቅ፣ 24 የብር፣ 21 የነሐስ)  ሜዳልያዎች፣  እንዲሁም ጀርመን በ47 (18 የወርቅ፣ 15 የብር እና 14 የነሐስ) ሜዳልያዎች እስከ አራት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይወስዳሉ ተብሏል፡፡  

Read 4210 times