Saturday, 19 September 2015 09:00

ደረቁ ከበደኝ እያልኩ እርጥብ ትጨምርበታለች

Written by 
Rate this item
(25 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ዓመት በዓል ወቅት፣ አንድ አባት ልጁን ይዞ ወደ አንድ ሆቴል ቤት ጎራ ይላል፡፡ ለልጁ ለስላሳ ለሱ ነጭ አረቄ አዞ መጠጣት ይጀምራል፡፡ ያን አረቄ በላይ በላዩ ሲጨማምርበት ወደ ሞቅታው ተጠጋ፡፡
አረቄውን ልትቀዱለት የምትመላለሰው ቆንጆ ሴት እየተሞናደለችና ሽንጧን እያተራመሰች ስትመላለስበት ዐይኑ ከሱዋ አልላቀቅ አለ፡፡
“አንቺም ጠጪ፣ ለኔም አምጪ” ማለት ጀመረ፡፡ ቆንጆይቱም መጎንጨት ጀመረች፡፡ ሞቅ አላቸው ሁለቱም፡፡ ተጠቃቀሱና ተራ በተራ ወደ ጓዳ ገቡ፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን ልጅየው ለስላሳውን ትንሽ በትንሽ እየጠጣ ሲያስተውል ቆይቷል፡፡ አባቱ ሳይመለስ ብዙ የቆየ ስለመሰለው፣ ወደሄደበት አቅጣጫ ሄደ፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ ተኝተዋል ለካ! ደንግጦ ቶሎ ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፡፡
አባትዬው ተመለሰ፡፡ አንድ ደግሞ ሂሳብ ከፈለና ወጡ፡፡
ቤት ደርሰው የሚበላ ቀርቦ በልተው እንደጨረሱ ጨዋታ መጣ፡፡
እናት - “እሺ ዙረታችሁ እንዴት ነበር?” አለች ወደ ልጁ እያየች፡፡
ልጁም - “መጀመሪያ ወደ ሆቴል ሄድን”
እናት - “እሺ?”
ልጅ - “አባዬ አረቄ አዘዘ፡፡ ለእኔ ለስላሳ ሰጠኝ”
እናት - “ከዛስ?”
ልጅ - “ከዛማ አባዬ ደጋገመ”
አባት - “በቃህ እንግዲህ! ወሬ አታብዛ”
እናት - “ተወው እንጂ ይንገረኝ”
ልጅ - “ከዛ የምታስተናግደንን ሴትዮ ጋበዛት”
እናት - ጉጉቷ ጨመረ፡፡ “እሺ ከዛስ?”
ልጅ - “ከዛ ሴትዮዋ ወደ ጓዳ ሄደች”
አባት - “አንተ ልጅ! ሁለተኛ ሽርሽር አልወስድህም!”
እናት - “ተወው ይጨርስልኝ!”
ልጅ - “ከዛ አባዬም ወደ ውስጥ ገባ”
እናት  - በችኮላ፤ “እሺ? ከዛስ?”
ልጅ - “አባዬ ሲቆይብኝ የት ሄደ ብዬ ወደዛ ሄድኩ”
እናት - “ከዛስ?”
ልጅ - “ከዛ አይቼ ተመለስኩ”
እናት - “ምን አየህ?”
ልጅ - አመነታ!
እናት ሁኔታው ገብቷት - “አይዞህ ንገረኝ”
ልጅ፤ እናቱንም አባቱንም አየና፤
“ያየሁትማ አንቺና ዘበኛችን እንደምትተኙት ዓይነት ነው!” አለ፡፡  
*           *          *
የሌላውን ዐይን ጉድፍ ለማሳየት ከመጣጣር የራስን ጉድፍ አስቀድሞ ማየት፣ አስቀድሞ ማውጣት ታላቅ ብልህነት ነው፡፡ ሁሉም ለስህተት በሚጋለጥበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ አንዱ ባንዱ ላይ ጣቱን ቢቀስር ውጤቱ ሲቀሳሰሩ መዋል ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን የወጣ አንድ ካርቱን ስዕል ባሳየው ምስል፣ ባለስልጣናት ወይም ሚኒስትሮች በትልቅ የኮንፈረንስ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዋል፡፡ እያንዳንዳቸው፣ አንዱ ባንዱ ላይ በሌባ ጣቱ ይጠቁማል፡፡ ማንም በማንም ላይ ጣቱን ሳይቀስር የሚታይ የለም፡፡ ሁሉም ጥፋተኛ ነው እንደማለት ነው፡፡ ግምገማዎች ምን ያህል ሀቀኛ ናቸው? ስህተትን ለማረም የሚያስችል ምን ያህል ቅን ልቦና አለ? የተገመገሙት ሁሉ እርምጃ ይወሰድባቸዋልን? ያንንስ ማን ይቆጣጠራል? ግምገማ ከእከክልኝ ልከክልህ ነፃ ነውን? ከየአንዳንዱ ግምገማ ምን ያህል ተምረናል? የሚገመገምና የማይገመገም፣ ይነኬና አይነኬ ሰው የለምን? ግምገማ ራሱ መገምገም የለበትምን? ባለፈው ዘመን የኮሚቴ መብዛት ትልቅ ችግር ሆኖ ተሰበሰቡና አሉ፤ ይህንኑ የሚያጠና ኮሚቴ አቋቁመው ተለያዩ! ሀገራችን አባዜዋ ብዙ ነው፡፡ አንድ ተገምጋሚ፤ ስለሀገራችን የስድስት መስመር የህዝብ መዝሙር ፃፍ ተብሎ አሥር ገፅ ያህል የዓላማ ፅሁፍ ተሰጠው፡፡ ቢለው ቢለው ያን ሁሉ ዓላማ በስድስት መስመር ማጠናቀቅ እንደማይመች ታወቀውና፤
“እንኳን ስድስት መስመር፣ መቶም አይበቃሽ እንደው በደፈናው፣ ዕንቆቅልሽ ነሽ    !”ብሎ ደመደመ ይባላል፡፡
በግምገማ ንፍቀ - ክበብ ዋና ጉዳይ የሚሆነው አዎንታዊነት (Positivism) ነው፡፡ በአዎንታዊነት ውስጥ ተስፋ አለ፡፡ በአሉታዊነት ውስጥ ጨለምተኝነት ነው ያለው፡፡ ሰውን ማነፅ አገርን ማልማት ነው፡፡ ሙያን ማክበር ሙያተኛን ማበልፀግ ነው! ይህም አዎንታዊነት ነው፡፡ መንገድ መሥራት ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ሀዲድ መዘርጋት ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ባቡር ማስኬድ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ በባቡር መሄድ ደግሞ ስልጣኔ ይፈልጋል፡፡ የባቡሩን መነሻና መድረሻ ደግሞ መረጃ ጆሮ ነው የሚፈልገው፡፡ አዎንታዊነት ውስጥ ሟርትን እንዳንከት መጠንቀቅ ያንድ የሰለጠነ ህዝብ ብልህነት ነው፡፡ ብዙ የሰራን እያስመሰልን ውስጡ ውስብስብ መክተት አሉታዊነት ነው! አገር ገንዘብ ይኖራት ዘንድ ሁለት ሶስት ያለው ቢላ መጠቀምም አሉታዊነት ነው፡፡ አገር አቀናለሁ ብሎ ደፋ - ቀና የሚለው ዜጋ፣ በንፁህ ስሜት፣ በቀና ልቦና ሲወድቅ ሲነሳ፤ ሌላው ወገን በአጭር - አቋራጭ (Short-cut)፣ አየር ባየር ከባለሥልጣን በመመሳጠር፣ በቀጭን ቢሮክራሲያዊ ትዕዛዝ ወዘተ… ሀብቱን ሲያከማችና ፎቁን ሰማይ ሲያስነካ ማየት ዘግናኝ ነው! ጉዳይ አስፈፃሚ የሆነ ባለዘመድ (መንገድ አዋቂ) ከባለ ጉዳዩ በላይ የሚያገኝበት አገር ውስጥ ለአስተዋይ ሰው ከኮሜዲው ትራጀዲው ማየሉ አይገርምም፡፡ በየቀኑ ነገር የባሰበት ዜጋ፤ “ደረቁ ከበደኝ እያልኩ፣ እርጥብ ትጨምርበታለች” የሚለው ለዚህ ነው! ከዚህ ያውጣን!!

Read 6246 times