Saturday, 19 September 2015 09:17

አዲሱን ዓመት በፖለቲካ ቀልዶች (ቁ.2)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(28 votes)

አትጠራጠሩ፤ቀልድ የማያውቁ ፓርቲዎች ለዛ ቢስ ናቸው!

    ባለፈው ሳምንት ለእናንተ ብቻ ሹክ ባልኳችሁ መሰረት፤ዘንድሮ የፖለቲካ ቶክ ሾው (በቲቪ) የመጀመር ዕቅዴ ከተሳካ፣ በአገሪቱ አሉ የተባሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች  (ነቄዎቹን ነው ታዲያ!) እየጋበዝኩ ቀልዳቸውን እንደማስኮመኩማችሁ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡ (አትስጉ! እንደ ፖለቲከኞች ቃል አባይ አይደለሁም!)
በእርግጥ ከአቅሜ በላይ የሆነ ችግር ሊገጥመኝ እንደሚችል አልክድም፡፡ (ብዙ “አጼ በጉልበቱዎች” አሉ እኮ!) ለምሳሌ ኢቢሲ ዓይነውሃዬን ብቻ አይቶ፣ “የፖለቲካ ቶክ ሾው አይቻልም; ቢለኝ ምን አደርጋለሁ? (ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የህዝብ ንብረት ነው አይደል?!) እንዲያም ሆኖ ግን ምርጫ የለም፡፡ “አንድዬ ያክብርልኝ፤እቤቴ በቲቪ መስኮት አልጣችሁ” ብዬ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ውልቅ ብቻ ነው፡፡
መቼም ቶክ ሾው ተከለከልኩ ብዬ ብቻዬን የተቃውሞ ሰልፍ አልወጣ!! ልውጣም ብል እኮ ላይሳካ ይችላል፡፡ ወይ የምንፈቀድልህ ከቀበና ጃንሜዳ ድረስ ነው ይሉኝና በሳቅ ያፈርሱኝ  ይሆናል፡፡ (ፓርቲ እመስላለሁ እንዴ?) እኔ እኮ ተቃውሞ ያለኝ ግለሰብ እንጂ ተቃዋሚ ፓርቲ አይደለሁም፡፡ (የህዝብ አጀንዳ ሳይሆን የራሴን አጀንዳ ነው የማራምደው!) እናም ተቃውሞዬን ማሰማት የምፈልገው ------ ቤተመንግስቱ ደጃፍ ላይ ብቻ ነው፡፡ ዋናው የአገሪቱ መሪ፣ ወደ ቤተመንግስቱ ሲገቡ ወይም ግቢያቸው ውስጥ ነፋስ ለመቀበል ሲዘዋወሩ፣ አይተው በደሌን እንዲጠይቁኝ  እንጂ ጭር ባለ ሜዳ የመቃወም ሃራራ የለብኝም፡፡ (ዓላማዬም ትግል ሳይሆን የፖለቲካ ቶክ ሾው በቲቪ የማቅረብ ህገመንግስታዊ መብቴ እንዲከበርልኝ መጠየቅ ብቻ ነው!)
ወይ ደግሞ የመከልከል አባዜ የተጠናወተው የሚመለከተው አካል፤(ኢህአዴግ በ10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ “ኪራይ ሰብሳቢዎች;-- ያላቸውን ማለቴ ነው!)፤ “በቂ የጸጥታ ኃይል ስለሌለ ሰልፉን ለሌላ ጊዜ አስተላልፈው” ሊሉኝ ሁሉ ይችላሉ፡፡ ይሄን ጊዜ አንድ ግለሰብ መሆኔን ማስታወስ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉደቱ ያመዝናል፡፡ (#ካፈርኩ አይመልሰኝ” አለ አበሻ!)  
ወዳጆቼ፤እስካሁን የነገርኳችሁ ሁሉ የቀድሞ ዘመን ስጋት እንጂ የዛሬ ስጋት እንዳይመስላችሁ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ብዙዎቹ ስጋቶች የአዲሱ ዓመት  እንደማይሆኑ ተስፋ አድርጉ፡፡ ለምሳሌ ልማቱ ተጠናቆ ከመጪው እሁድ ጀምሮ ባቡሩ አገልግሎት መስጠት ስለሚጀምር፣ ከዚህ በኋላ መስቀል አደባባይ ለተቃውሞ ሰልፍ የሚከለከልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ (ቋሚ የልማት ጣቢያ ነው ካልተባለ በቀር!)
የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣንም ባለፈው ዓመት ከ20 የማያንሱ አዳዲስ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችና ቻናሎች እንደሚከፈቱ መግለጹን አስታውሳለሁ፡፡ (እንደውም ዘግይቷል!)
 እናም----ከብዙ ሁኔታዎች አንጻር ኢቢሲ የፖለቲካ ቶክ ሾው እንደማይከለክለኝ እተማመናለሁ፡፡ ከከለከለኝም ደግሞ ችግር የለም፡፡ (በኋላ የሚቆጨው ራሱ ነው!) ከአዳዲሶቹ ጣቢያዎች አንዱ፣ እጄን ስሞ ይቀበለኛል፡፡ (ከኢቢሲ ጋር አልቆረብኩ!)
አሁን ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ?  በየፓርቲያቸው በይፋም ሆነ ውስጥ ለውስጥ  የተነገሩና የተፈጠሩ ቀልዶችን፣ ቆመንለታል ለሚሉት ህዝባቸው ለማጋራትና ዘና ለማድረግ ፈቃደኛ የሆኑ ፓርቲዎችን ወይም ፖለቲከኞችን መመልመል ነው፡፡
ለመሆኑ በራሱ ላይ አብዝቶ የሚቀልድ የአገራችን ፓርቲ የትኛው ይሆን? ኢህአዴግ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ፣ (ብዙ መከራ ስላየ ተስፋ ያለው ይመስለኛል!) መድረክ፣ ወይስ ማን ይሆን?
  እርግጠኛ ነኝ ----- ከኢህአዴግም ከተቃዋሚዎችም ብዙ በሳቅ የሚያፈርሱ ቀልዶችን እንሰማለን፡፡ (የቶክ ሾው ሞቶ፡- ቀልድ የማያውቁ ፓርቲዎች ለዛ ቢስ ናቸው! የሚል ነው) አንዴ ይጀመር እንጂ በህዝብ የተፈጠሩ ቀልዶችም ይጎርፋሉ፡፡ ይኸውላችሁ--- አዲስ የቀልድ ባህል በመጀመር ዘና ከማለታችንም ባሻገር የከረረውን ፖለቲካችንንም ለዘብ እናደርገዋለን፡፡ ጨዋታ አዋቂና ቀልደኛ ሰው እኮ ምን ቢበሽቅ ፈጥኖ አይሳደብም፤ አንዳንዴ ተርቦ ወይ ቀልዶ ያልፋል፡፡ ቀልድ የማያውቅ ከሆነ ግን ቶሎ ያመራል፡፡ ለጠብ ይጣደፋል፡፡ በ21ኛው ክ/ዘመን ደግሞ ዱላ ከኋላ ቀሮች ተርታ ያሰልፋል፡፡ እናም በቀልድ እናባብለው ብዬ እኮ ነው (ኋላ ቀርነታችንን!!)
አሁን የአሜሪካ የፖለቲካ ቀልዶች ምን እንደሚመስሉ እንቃኝ ዘንድ አንድ ሁለት ሦስቱን ልጋብዛችሁ፡፡ ለአገር በቀሉ የፖለቲካ ሾው መዳረሻ ይሆኑናል፡፡ ወደ ቀልዶቹ፡-
*          *        *
የዋይት ሃውስ ጨረታ
የዋይት ሃውስን አጥር ለማደስ 3 ኮንትራክተሮች ይጫረታሉ፡፡ አንደኛው ከቺካጎ፣ ሌላኛው ከቴኒዝ፣ ሦስተኛው ከሚኔሶታ የመጡ ናቸው፡፡ ሦስቱም ከአንድ የዋይት ሃውስ ሹም ጋር ተያይዘው የአጥሩን ሁኔታ ለማየት ይሄዳሉ፡፡
የሚኔሶታው ኮንትራክተር ወዲያው ሜትሩን አወጣና አጥሩን ለካው፡፡ ከዚያም በእርሳስ ሂሳቡን ጫር ጫር አደረገና፤ “ሥራው 900 ዶላር ገደማ ይፈጃል፤ 400 ዶላር ለቁሳቁስ፣ 400 ዶላር ለሰራተኞቼ፣ 100 ዶላር ትርፍ ለእኔ” ሲል አስረዳ፡፡
የቴኒዙም ኮንትራክተር ለካክቶ ሲያበቃ፣ የሰራውን ሂሳብ ተናገረ፤ “ይሄን ሥራ በ700 ዶላር እሰራዋለሁ፡፡ 300 ዶላር ለቁሳቁስ፣ 300 ዶላር ለሰራተኞቼ፣ 100 ዶላር ትርፍ ለእኔ”
 አሁን ተራው የቺካጎው ኮንትራክተር ነው፡፡ እሱ ግን የለካውም ሆነ ያሰላው ሂሳብ የለም፡፡ ወደ ዋይት ሀውሱ ኃላፊ ጠጋ አለና በሹክሹክታ፤ “2,700 ዶላር!” አለው፡፡ ሹሙም በመጠራጠር እያየው፤ “እንደሌሎቹ ስትለካ እንኳን አላየሁህም፤ እንዴት ነው ይሄን የሚያህል ቁጥር ላይ የደረስከው?” ሲል ጠየቀው፡፡ የቺካጎው ኮንትራክተር አሁንም በሹክሹክታ፤ “1ሺ ዶላር ለእኔ፣ 1ሺ ዶላር ለአንተ፣ በቀረው ገንዘብ የቴኒዙን ኮንትራክተር ቀጥረን አጥሩ ይታደሳል፡፡” በማለት አስረዳው፡፡ የዋይት ሀውሱ ሹሙም ምንም ሳያቅማማ፤ “ጨርሰናል!” ሲል መስማማቱን ገለፀለት፡፡
(ወዳጆቼ፤ የበጀት ማነቃቂያ ዕቅዱም ተግባራዊ የሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡)
*        *      *
ባለቀ ሰዓት ማሊያ መቀየር?!
በህይወት ዘመኑ ሁሉ  የሪፐብሊካን ፓርቲን በመደገፍ የሚታወቅ ጽኑ ሰው ታሞ አልጋ ይዟል፡፡ ህመሙ እየተባባሰ ሊሞት ማጣጣር ጀመረ፡፡ ከመሞቱ በፊት በነበረች ሽርፍራፊ  ደቂቃ እንደምንም ትንፋሹን አሰባሰበና፤ #ከአሁን ሰዓት ጀምሮ ሪፐብሊካንን ትቼ የዲሞክራት  ደጋፊ ሆኛለሁ; ሲል አስታወቀ - በኑዛዜ ቃና፡፡ (ዕድሜ ልኩን ኢህአዴግ ወይም ሞት ሲል የነበረ አባል፣ባለቀ ሰዓት ላይ ተቃዋሚ ሆኛለሁ ሲል አስቡት!)
አጠገቡ የነበረ ጓደኛው በእጅጉ እንደተናደደበት ገጽታው ይመሰክራል፡፡ ሥሩ ተገታትሮ ከደቂቃ በፊት ማሊያ ለውጫለሁ ያለውን የቀድሞ የሪፐብሊካን ደጋፊ ባልንጀራውን አፋጠጠው፤ “እኔ ፈጽሞ የምትለው ነገር አልገባኝም፤ ህይወትህን ሙሉ ፍንክች የማትል ብርቱ የሪፐብሊካን ደጋፊ ነበርክ፤ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ድንገት ተነስተህ ዲሞክራት ለመሆን የፈለግኸው?!”
በሞት ጣር ላይ የነበረው ሰውዬ ለመልስ የሚሆን ትንፋሽ አላጣም፤ “ለምን መሰለህ … የእኛ ፓርቲ ሰው ከሚሞት የእነሱ ቢሞት ስለምመርጥ ነው!” አለው፡፡
 (እቺ በሃበሽኛ ስትተረጎም … “ጠላትን ደስ አይበለው!”)
*          *        *
“ገንዘቤን ቁጭ አድርጋት”
አንድ ሌባ አንድ ትልቅ ሰውን አሳቻ ቦታ ላይ ሽጉጥ  ይደግንበትና፤ “ያለህን ገንዘብ በሙሉ ቁጭ አድርጋት!” ሲል ያስፈራራዋል፡፡ በድንገተኛው የዘረፋ ጥቃት የተደናገጠው ሰውዬም፤ “በእኔ ላይ ይሄን ልትፈጽም አትችልም … እኔ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ነኝ” ይለዋል፡፡ ሌባውም መለስ ብሎ፤ “እንዲያ ከሆነማ … በል ገንዘቤን ቁጭ አድርጋት” አለው፡፡
(የኮንግረስ አባል ከሆንክማ የራሴው ገንዘብ ነው እንደማለት …!)
*          *        *
ተጋባዡ ፖለቲከኛ
የጎልፍ ክለብ እራት ላይ አንድ ፖለቲከኛ ንግግር እንዲያደርግ ይጋበዛል፡፡ ፖለቲከኛው መድረክ ላይ ወጥቶ ንግግሩን ሲጀምር፣ ጥቂት ታዳሚዎች አጋጣሚዋን በመጠቀም ሹልክ እያሉ ወደ ባሩ አመሩ … አልኮል ለመጎንጨት፡፡
ከአንድ ሰዓት በኋላ ሌላ አንድ ታዳሚ ወደ ባሩ መጥቶ ይቀላቀላቸዋል፡፡ ወዲያው ቀድመው የወጡት ታዳሚዎች በጥያቄ ያጣድፉታል፡-
“አሁንም ሰውየው ንግግሩን አልጨረሰም?”
“አዎ፤ አልጨረሰም”
“ለመሆኑ ምንድነው የሚዘባርቀው?”
“ምን አውቃለሁ፤ ገና ራሱን አስተዋውቆ አልጨረሰም እኮ”
(ኮንሰርት የሚያቀርብ መሰለው እንዴ?)

Read 7035 times