Print this page
Saturday, 19 September 2015 09:27

ሻወር የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል?!

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

   ሻወር የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል ሲባል፣ እንዴት የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ በገላ መታጠቢያ ቤቶች ውስጥ የሚገኘው የሻወር ቧንቧ ጭንቅላት (Shower heads) እጅግ አደገኛ ለሆኑ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች በሚያጋልጡ ባክቴሪያዎች የተሞላ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የአሜሪካ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
በመተንፈሻ አካላት ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ያስከትላሉ የተባሉት microbacterium በሚል ስያሜ የሚታወቁት ባክቴሪያዎች በተለይም የጋራ መጠቀሚያ በሆኑ መታጠቢያ ቤቶች ባሉ የሻወር ቧንቧ ጭንቅላቶች ውስጥ በስፋት የሚገኙ ሲሆን ቀዝቃዛ ውሃ የሚያወርዱ ሻወሮች ሙቅ ውሃ ከሚያወርዱት በበለጠ በባክቴሪያዎቹ የተሞሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች ታዲያ ሰዎች ሻወር ለመውሰድ ቧንቧውን ሲከፍቱ፣ በአየር ውስጥ በመሰራጨት በመተንፈሻ አካላቶቻችን ውስጥ ገብተው ለበሽታ ይዳርጉናል፡፡
ለዚህ መፍትሄው ንፅህና ነው ይላሉ - ባለሙያዎቹ፡፡ የሻወር ቧንቧ ጭንቅላቶች ቶሎ ቶሎ መታጠብና በተወሰነ የጊዜ ገደብ መቀየር እንደሚኖርባቸው የሚናገሩት የህክምና ባለሙያዎቹ፤ እንደ ሆስፒታሎች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ሊቀየሩ እንደሚገባም ይገልፃሉ፡፡ በዓይን የማይታዩት እነዚህ በሽታ አምጪ ባክቴሪያዎች፤ በተለይ ህመምተኞችን፣ ህፃናትንና አቅመ ደካሞችን በይበልጥ ያጠቃሉ፡፡ የህክምና ባለሙያዎቹ፤ ከእነዚህ የጤና ችግሮች ለመጠበቅ ሻወር በምንወስድበት ጊዜ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ይገልፃሉ፡-
የገላ መታጠቢያ ስፍራና የሻወር ቧንቧ ማውረጃ ጭንቅላቱ ሁልጊዜም ንፅህናው የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሻወር በሚወስዱበት ወቅት በመጀመሪያ የሚወርደውን ውሃ ገላዎ ላይ አያሳርፉ፡፡  ጥቂት ውሃ ከፈሰሰ በኋላ መታጠብ ይጀምሩ፡፡
የሻወር ቧንቧን ጭንቅላት በየጊዜው እያወረዱ፣ በሞቀ ውሃ ሙልጭ አድርገው ይጠቡት፡
አልፎ አልፎ የፈላ ውሃ በቧንቧው ውስጥ እንዲያልፍ ያድርጉ፡፡
በተለይ በተለያዩ በሽታዎች የሚሰቃዩ ሰዎች ገላቸውን በቁም ሻወር ከመታጠብ ይልቅ በገንዳ ቢታጠቡ ይመረጣል፡፡ ባክቴሪያዎቹ በህመም የተጐዳን ሰውነት በይበልጥ ያጠቃሉና!!

Read 6646 times