Saturday, 26 September 2015 08:20

ሹም ለሹም ይጐራረሳሉ፤ ድሃ ለድሃ ይላቀሳሉ

Written by 
Rate this item
(29 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን ሚያሚ ለሚባለው ጋዜጣ፣ የቀብር ሥነስርዓት ክፍል ስልክ ተደወለ አሉ፡፡
ደዋይዋ ሴት ናት፡፡
“የአንድን ሰው የህይወት ታሪክ በመቃብሩ ላይ ፅፎ ለመቅረፅ ምን ያህል ይፈጃል?” አለች ሴትዮዋ፡፡
የጋዜጣው ሠራተኛ በትህትና፤
“ለአንድ ቃል አምስት ዶላር ያስፈልጋል እመቤት”
“ጥሩ” አለችና ሴትዮዋ ከጥቂት ጊዜ እረፍት በኋላ፤
“እርሳስ ይዘሃል?”
“አዎን እመቤት”
“ወረቀትስ ከአጠገብህ አለ?”
“አዎን እመቤት”
“እሺ እንግዲያው የምታፅፊለትን ቃል ልምረጥ”
“መልካም”
“እንግዲያው የእኔ እመቤት፤ ቦጋለ ሞቷል” ብለህ ፃፍ፡፡
“ይኸው ነው? በቃ?” አለ ፀሐፊው ባለማመን፡፡
“አዎን ይሄው ነው” አለች ሴትዮዋ
“እመቤቴ በስህተት አንድ ቁም ነገር ሳልነግርዎ ዘንግቻለሁ”
“ምንድን ነው የዘነጋኸው?”
“ከአምስት ቃላት በታች መናገር ክልክል ነው፡፡ አምስት ወይም ከአምስት በላይ መጠየቅ ነበረብዎ”
“እሺ፤ ጥቂት ደቂቃ እንዳስብ ፍቀድልኝ” ብላ ፍቃዱን ጠየቀች፡፡”
ጥቂት ደቂቃ አሰበችና
“እሺ እርሳስና ወረቀት ይዘሃል?”
“አዎን፤ እመቤት፤ ይዣለሁ!”
“እንግዲያው ፃፍ”
“እሺ እመቤት”
“እንግዲያው ቦጋለ ሞቷል - የሚሸጥ ካዲላኩ መኪናው እንዳለ አለ - አሁንም አልተሸጠም” ብለህ አክልበት አለችው፡፡
*   *   *
እንደሁኔታው ተስተካክሎ ቀዳዳዎችን መጠቀም አስተዋይነት ነው፡፡ መንገዶች ሁሉ በአንድ በኩል ብቻ ነው የሚሄዱት ብሎ ግትር አለመሆን ታላቅነት ነው!
ዕውቀት እያነሰ በመጣ ቁጥር ሐሜትና ስለሰው መተቸት እጅግ የሚዘወተር ነገር እየሆነ ይመጣል፡፡ በዚህም ሳቢያ ችግርን በመላ ከመፍታት ይልቅ ከአፍ አፍ ማዛመት ዋና ሥራ እየሆነ ይሄዳል፡፡
“በነገር በተተበተበ ማህበረሰብ ውስጥ ለብልሆች ስድቦች የጋራ ይደረጋሉ፡፡ ሐሜትንም ከሰው ሰው ይለዋወጡታል፡፡ (insults are shared and gossip is exchange) ይሄ የሆነበት ምክንያት ሐሜትን ማዛመት ከመቅለሉም የበለጠ አዝናኝና አስደሳች በመሆኑ ሲሆን፣ መቼም ቢሆን መቼ የሌሎችን ስህተት መለየትና ታርጋ መስጠት የራስን ህፀፅ ከማየት የቀለለ በመሆኑ ነው” ይሉናል ፀሐፍት፡፡
በየጊዜው ስለሚዲያዎች ክፉ ክፉው ይወሳል፡፡ ሚዲያዎች እንደአስፈሪ ጠላቶች መታየታቸው በየትኛውም ሥርዓት የሚከሰት ጉዳይ ነው፡፡ ያለነገር አይደለም፡፡ መረጃዎች ህብረተሰብን ያነቃሉ፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን በአዎንታዊም በአሉታዊም ውጤት ሊፈረጅ ይችላል፡፡
“ፈላጭ - ቆራጭ መንግሥታት ሁነኛ ጫና በግል ሚዲያዎች ላይ ማሳረፋቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የህዝብ ፍላጐት ብዙውን ጊዜ የሚቀሰቀሰው በድራማዊ ክስተቶችና ስማቸው በገነነ የተከበሩ ሰዎች እንዲሁም ሚዲያውን እንደራሳቸው ቤት ርስተ - ጉልት ባደረጉ ግለሰቦች ነው ይለናል - ዳንኤል ካህኔማን (Thinking, Fast and Slow)”
የአዕምሮአችንን ውሱንነት መዘንጋት የሚከሰተው እናውቃለን ብለን ባመንበት ነገር ያለን ለከት የለሽ በራስ መተማመን እና የድንቁርናችንን ሙሉ ገጽታ ለመረዳት ብቃት ማጣት እንዲሁም የምንኖርበትን ዓለም በጥርጣሬ መሞላት ልብ አለማለት ነው! በመጨረሻ የአገራችን የኢኮኖሚ ጣጣ ዛሬም መንገድም ኖሮ፣ አበባም ኖሮ፣ ባቡርም ኖሮ፤ ምን ሆነ? የሚለው ነው፡፡ ሙሰኛና ሙሰኛ ጀርባቸውን በሚተሻሹበት አገር ልማት ይኖራል ወይ? የሚለው ጥያቄ መልሱ አንድና አንድ ነው
ሹም ለሹም ይጐራረሳሉ፤
ድሃ ለድሃ ይላቀሳሉ!!
የልማት መርሀ - ግብር ሙስናን አይሽረውም እንደማለት ነው!!

Read 7322 times