Saturday, 26 September 2015 08:22

ለአዲስ አድማስ አዘጋጅ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     ባለፈው ቅዳሜ በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም ላይ፤ አደዳ ኃይለ ሥላሴ፤ “በአብነት ስሜ ላይ ለተሰነዘሩ ትችቶች የተሰጠ ምላሽ” በሚል ርዕስ የጻፉትን አነበብኩ። ደግሜም አነበብኩት። በዚሁ ጋዜጣ ላይ ወሪሳ ስለተባለው የአለማየሁ ገላጋይ መጽሐፍ አብነት ስሜ ባቀረቡት ሂሳዊ ጽሁፍ ላይ ለተሰጠ አስተያየት ምላሽ  ነው።
አንድ በ1960 ገደማ የደረሰብኝን ገጠመኝ አስታወሰኝ። በወቅቱ ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪ ነበርኩ። በአማርኛ ጋዜጦች በተለይ በ “አዲስ ዘመን” ሳምንታዊ አምድም ነበረኝ። አንዴ ለዚያ አምድ ያዘጋጀሁት ጽሁፍ አይወጣም ተብሎ ታገደ። አጋጁ ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ ነበሩ። የማስታውቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስቴርና የሳንሱር ሐላፊም ነበሩ። ከኔ ጋር ተቀራርብናል። አንድ ቀን ጠየኳቸው፤
 “ብላታ ይኸ የዘመኑ ሰው ብዙ እርስዎ ባልነበሩበት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊጽፍ ይችላል። አንዴት ለክተው ነው ያልፋል ይወድቃል የሚሉት?” አልኳቸው።
መለሱልኝ፤“ልጄ ሙት ቀላል ነው!” አሉኝ በጥሞና፤ “እኔ ካልገባኝና ካልተረዳሁት አያልፋትም!”
 ይህ የአደዳ ጽሁፍ ያንን አስታወሰኝ። መልእክቱ ካልገባን ካልተረዳን፥ (ሁሉንም ልናውቅና ልንረዳ አንችልምና)  ዞር- ዞር ብሎ መጠየቅና ማፈላለግ ነው። ካፈላለጉት ምንጩ (ጮቹ) እዚያው አሉልን። ሊገመት በሚችለው ምክንያት ሁሉ ብላታን እንዲያ አላልኩም። ልላቸው ተገቢም አልመሰለኝም።
ለምንናገረው፤ለምንጽፈው ሐላፊነትና ተጠያቂነት ለጀማው አንባቢ አለብን። ከሁሉም  በላይ ግን ተጠያቂነቱ ለራሳችን  መሆን   አለበት። ለራሳችን ታማኝ ከሆንን ለጀማውም ታማኝነቱ ከዚያ ይፈልቃል።  የሐምሌትን  በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀስ መሞክሬ ነው፡-
“This above all: to thine own self be true,
And it must follow, as the night the day,
Thou canst not then be false to any man.”
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን እንዴት እንደተረጎመው በቃሌ ማስታወስ አልቻልኩም። በሒስና ኂስ መካከል ያለውንም ልዩነት ተማርኩ። እንደኔ  እንደኔ፣ ይህ የአደዳ ጽሁፍ አልፎ አልፎ ደጋግሞ ቢወጣ ጥሩ ይመስለኛል። “ጠንቀቅ ነው ደጉ!”  የሚል ይመስለኛል። ቀይ መብራት እንዳንጥስ ደውል ሆኖ ሊያገልግል የሚችል ይመስለኛል። እኔኑ ጨምሮ!
ከአክብሮት ጋር
አሰፋ ጫቦ
Corpus Christi Texas USA

Read 2125 times