Saturday, 26 September 2015 09:04

የ‘ምስኪን ሀበሻ’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(15 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁማ!
ምስኪን ሀበሻ በቀጠሮው መሠረት ዛሬም ለአንድዬ አቤቱታውን እያቀረበ ነው፡፡
አንድዬ፡— አጅሬ፣ መጣህ! እኔ ረሳኸው ብዬ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እንዴት እረሳለሁ፣ ይህን ያህል ዝንጉ አልሆንኩም እኮ!
አንድዬ፡— እሱን እንኳን ተወው፡፡ ሌላው ህዝብ የተቀበረ ታሪኩን እንዳይረሳ ከየትም እየፈለገ ያወጣል እናንተ ያላችሁን ታሪክ እንኳን ሆነ ብላችሁ እየረሳችሁ ይህን ያህል ዝንጉ አልሆንኩም ትለኛለህ!… ተወው፣ እኔ እኮ ዝም ብዬ ነው ለማይሆን ነገር የምለፈልፈው፡፡ እና አሁንስ ምን ሁን ልትለኝ ነው…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ሳምንት እንደነገርኩህ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች እያሳሰቡን፣ እያስጨነቁን፣ እያሰጉን ስለሆነ እንደ ሌላው ጊዜ እንዳትረሳን ከአሁኑ ለመለመን ነው፡፡
አንድዬ፡— እኔ እኮ ግራ የገባኝ ምን ሁን እንደምትሉኝ ነው! ሥሩበት፣ ዘርታችሁ እጨዱበት ብዬ ለም መሬት ብሰጣችሁ እናንተ ትዘፍኑልኛላችሁ፡፡ ‘ወተቱ ከጓዳ እሸቱ ከጓሮ’ ስትሉ ያው አሁንም በሬ እንደጠመዳችሁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ አተቆጣ እንጂ!
አንድዬ፡— ለምን አልቆጣ! ለምን አልቆጣ! የወንዝ መአት ሰጠኋችሁ፡፡ ያንን እንደመጠቀም አንዴ ‘ግንድ ይዞ ይዞራል፣ አንዴ ‘ቢሞላ መሻገሪያው ሌላ’ እያላችሁ ስትዘፍኑለት ግብጽ ደግሞ እየጠለፈ በረሀውን አለማ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱን እንኳን አሁን እያስተካከልን ነው፡፡
አንድዬ፡— አይ ማስተካከል…ሌሎቹንስ ወንዞች ለጌጥ ነው የሰጠኋችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ያው እንደምታውቀው እኛ ብዙ ዘመን እርስ በእርሳችን…
አንድዬ፡— ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ዕድል አግኝቼ ነው አንድዬ!
አንድዬ፡— በየዘመናቱ ዓለም እርስ በእርስ ተላልቋል፡፡ እናንተም ስትተላለቁ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ትክክል አንድዬ፣ ትክክል….
አንድዬ፡— ይኸው አሜሪካን ጃፓንን ዶጋ አመድ አድርጋ ስንት መቶ ሺህ ህዝብ ገድላ አልነበረም…
ምስኪን ሀበሻ፡— አዎ አንድዬ…
አንድዬ፡— ታዲያ አሁን ጃፓን አሜሪካንን ‘ያኔ ዜጎቼን በቦምብ ፈጅተሽ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም’ ስትል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ ጌታዬ እንደውም በጣም ወዳጆች ናቸው፡፡
አንድዬ፡— ጀርመን እነኛን ስንት ሚሊዮን አይሁዶች — ያውም የእኔን ህዝቦች — ፈጅታ ስንት ዘመን ሲንከራተቱ ኖሩ፡፡ ‘አሁን ያኔ የፈጃችሁንን ብንረሳ ብረሳ ሞት ይርሳን’ ምናምን ሲሉ ሰምታችሁ ታውቃላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ኧረ እንደውም ወዳጆች ናቸው!
አንድዬ፡— ታዲያ እናንተ ዘላለም ዓለም ትንሹንም ትልቁንም እያነሳችሁ፣ ‘ያኔ እንዲህ አድረግኸኝ’ ‘እንደዛ ስታደርጊኝ የነበረው’ ..እያላችሁ እናንተስ አይሰለቻችሁም፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን እናድርግ፣ አንድዬ…ቂም በቀል ተጣባን! ትንሹም ትልቁ በሆነ ባልሆነው ቂም መቋጠር፣ መበቀል ነው የያዝነው፡፡
አንድዬ፡— እኮ፣ ዘላለማችሁን ጠብ ያለሽ በዳቦ የት አደረሳችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ…
አንድዬ፡— ታዲያ ለራሳችሁ ሳታውቁ እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ልቦና ስጠና፣ ዲያብሎስን አባርልና!
አንድዬ፡— አሁንማ ነገረ ሥራችሁን ሳያችሁ፣ በክፋታችሁ ራሱ ዲያብሎስ የሚፈራችሁ ነው የሚመስለኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እዚህ ደረጃማ አልደረስንም፡፡
አንድዬ፡— ያኔ አባቶቻችሁ ድሀ ቢሆኑም ለፈረንጅ አልተንበረከኩም፡፡ አሁን እናንተ ነጭ ባያችሁ ቁጥር የምትሆኑትን ሳይ እኔም አዘንኩባችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ከዚህ በፊት ነግሬህ የለ…እንግዳ አክባሪዎች ስለሆንን እኮ ነው፡፡
አንድዬ፡— የራሳችሁን ሰው እየናቃችሁ፣ ራሳችሁ ሰው ላይ እንደ አንበሳ እየተጎማለላችሁ፣ ለራሳችሁ ሰው ግንባራችሁን እየቋጠራችሁ ፈረንጅ ስታዩ እንደዛ ስድሳ ስድስት ጥርስ የሚያደርጋችሁ፣ ግንባራችሁ መሬት የሚነካው… እንኳንም እነኛ እኔን ከልባቸው የሚወዱ አያቶቻችሁ አላዩ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንተ ጋ ሆነው ማየታቸው ይቀራል!
አንድዬ፡— አያዩም፣ እሱ የሚታይበትን ቻነል ጃም አድርጌዋለሁ፡፡ (ከት ብሎ ይስቃል፡፡) አሁንስ ደጋግሜ እናንተን ሳናግር፣ እናንተን ሆኜ ቁጭ ልል ነው፡፡ ይልቅ ዓለምን በወሬ ሳይሆን በሥራ ድረሱበት፡፡ ትናንትና ከእናንተ እኩል የነበሩት አገሮች የትና የት ደርሰዋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱን ነገር ካነሳኸው አይቀር… ለምሳሌ ከሀምሳ ዓመት በፊት ከእነኮሪያ ጋር እኩል ነበርን ይባላል፡፡ አሁን እነሱ ያሉበትና እኛ ያለንበት ፍትሀዊ ነው? አንድዬ፣ እንደ ልጅና እንደ እንጀራ ልጅ ትለየናለህ!
አንድዬ፡— እነሱ እዚህ የደረሱት ሠርተው ነዋ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እኛም እኮ እንለፋለን፡፡
አንድዬ፡— እውነት! አሁንማ አንደኛችሁን ከማለዳ ጀምሮ መጠጥ ላይ ተቀምጣችሁ መዋል ጀምራችኋል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ችግራችንን ማስረሻ ነዋ አንድዬ፡፡ ስንስቅ ደልቶን መስሎህ ነው እንዴ!
አንድዬ፡— ደልቷችኋል እንጂ፣ በጣም ነው የደላችሁ፡ በቀደም ቁልቁል ሳይ በየቦታው ተሰልፋችኋል፡፡ አንዱን መልአኬን ጠራሁና እነኚህ ሰዎች እንዲህ የተሰለፉት አሁንም ስንዴና ጤፍ ላክልን ሊሉ ነው ወይ አልኩና አጣርቶ እንዲመጣ ላክሁት፡ መጥቶ የነገረኝ ነገር አሳዘነኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን አለህ አንድዬ?
አንድዬ፡— ለፍልሰታ ጾም ሊቀበሉ ሥጋ ለመግዛትና ለመብላት ተሰልፈው ነው አለኝ፡፡ እንደው ምን ባደርጋችሁ ይሻላል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን አለበት ዞሮ፣ ዞሮ አንተን ለማስታወስ ስንዘጋጅ ነው፡፡
አንድዬ፡— ሥጋ በሰልፍ እየገዛችሁና እየበላችሁ ነው እኔን የምታስቡት…
ምስኪን ሀበሻ፡— እንምሰል ብለን ነዋ! ኪሳችን ሞልቶ መሰለህ! ይኸው ያኔ የተሰለፍነው እስከዛሬ ድረስ መሶባችንን የተለቀቀ ቤት አስመስሎታል፡፡ ከዚች ከዛች እያልን ነው እኮ ከወር ወር የምንደርሰው፡፡
አንድዬ፡— ከዚች ከዛች ማለት…
ምስኪን ሀበሻ፡— በቃ ከሥራ ማስኬጃዋም ከምኗም እየቆነጠጣርን…
አንድዬ፡— እየሰረቃችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— መስረቅ አይደለም አንድዬ፡፡ እንደውም አንድ ነገር አስታወስከኝ፡፡ አንድዬ በቀደም የጀመርኩልህን የአሥርቱ ትዕዛዛት ነገር… አንድዬ፣ አትስረቅ የሚለው ህግ ሲወጣ እኮ ያኔ ካዝና ምናምን የሚባል ነገር አልነበረም፡፡
አንድዬ፡— እና…
ምስኪን ሀበሻ፡— እናማ መለወጥ አለበት፡፡ በቃ ሲቸግረን ከካዝናው ወጣ አድርገን እናሯርጠውና ቦታው እንመልሳለን፡፡ ማንም ኪስ አልገባን!
አንድዬ፡— ቢሆንስ…የእናንተ ያልሆነውን ነዋ የምትወስዱት፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ማንም ሳያውቅ እኮ ነው፡፡ ብሩ ዝም ብሎ ካዝና ከሚያሞቅ የእኛን ኑሮ ሞቅ ያድርግልን ብለን ነው፡፡
አንድዬ፡— ሞቅ ያድርግልን ነው ያልከው፡ አሁን ገና ሸጋ አማርኛ ተናገርክ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ደግሞ ምን አድርገንህ ነው ዝናቡን እንዲህ ያጠፋህብን?
አንድዬ፡— አሁንም ዝናብ ላይ ናችሁ? ስንቱ የዓለም ህዝብ በረሀውን አረንጓዴ እያደረገ ተትረፍርፎታል! እኔ ግን እናንተን ሁሉ ጊዜ እንደ አራስ እየፈተፈትኩ ማጉረስ አለብኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እኛም እኮ እንለፋለን፡
አንድዬ፡— በአፋችሁማ ትለፋላችሁ… በመፈክርማ ትለፋላችሁ… ያኛው ይውደም፣ ይሄኛው አፈር ይብላ በማለትማ ትለፋላችሁ…ምናለ ትንሽ ምላሳችሁን አሳርፋችሁ አእምሯችሁን ብታሠሩት!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ ቢሆንስ እንደገና ዝናብ ያጠፋህብን የዓለም መዘባበቻ ልታደርገን ነው! በስንቱ ነገር ከዓለም ምናምነኛ… ከአፍሪካ አንደኛ እያልን… ዓለም በስንቱ ነገር እያደነቀን ነው እያልን…ጤፍ የዓለም አንደኛ ሆነች ብለን እየፎከርን…እንደገና መዘባበቻ ልታደርገን ነው!
አንድዬ፡— መጀመሪያ ያላችሁትን ሁሉ ዓለም ሲያምናችሁ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንዲህማ አትለንም፡፡ በቀደም ኦባማ እኮ እስክስታ ሞከሩ፡
አንድዬ፡— እና…
ምስኪን ሀበሻ፡— እናማ በዓለም ተቀባይነታችን ለመጨመሩ ማሳያ ነዋ፡
አንድዬ፡— (በሀዘኔታ ራሱን ወዘወዘ) ይሄን ያህል ራሳችሁን ዝቅ ታደርጋላችሁ ብዬ ጠርጥሬም አላውቅ፡፡ ሰውየው እስክስታ ስለወረደ ነው ተቀባይነታችሁ የጨመረው! በል፣ በል አንተን መስማቱ እኔኑ ወደእናንተ እየጎተተኝ ስለሆነ ይብቃን፡፡ ወይ እስክስታ ሞከረ ብሎ ነገር!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ…
አንድዬ፡— በቃ፣ በቃ…ሌላ ጊዜ፡፡ ደህና ክረም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6204 times