Saturday, 26 September 2015 09:08

ሃኪምና ፋርማሲስት አልተግባቡም

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በአገራችን ከአምስት ህሙማን አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል
የሃኪሙን የእጅ ፅሁፍ ማንበብ የሚያዳግታቸው ፋርማሲስቶች በዝተዋል

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በተደረገለት ሙሉ ምርመራ የጉበት ህመምተኛ መሆኑ ሲነገረው ድንጋጤው ልክ አልነበረውም፡፡ ህመሙ ዕለት ከዕለት እየተባባሰበት በመሄዱ ምክንያት ወደ ሆስፒታል ሄዶ ምርመራ ለማድረግ ሲወስን፣ ሃኪሙ ህመሙን አውቆለት ፈዋሽ መድሃኒት እንደሚያዝለት፣ ከበሽታውም እንደሚያገግም ጽኑ እምነት ነበረው፡፡
ከሃኪሙ የተፃፈለትን የመድሃኒት ማዘዣ ይዞ መድሃኒቱን ፍለጋ ወጣ፡፡ በከተማው ውስጥ ያሉ በርካታ መድሃኒት ቤቶችን ቢያስስም መድሃኒቱን ማግኘት አልቻለም፡፡ ቆይቶ ግን መድሃኒቱ በአንድ ፋርማሲ ውስጥ እንደሚገኝ ሰማ፡፡ ለመድሃኒቱ የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ገዛ፡፡ ችግሩ ግን ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ ፋርማሲስቱ የነገረው ነገር አልነበረም፡፡ የገዛውን መድሃኒት ይዞ ወዳዘዘለት ሃኪም ሄደ፡፡ ሃኪሙ ዘንድ ቀርቦ መድሃኒቱን በብዙ ፍለጋ ማግኘቱን በመግለጽ፣ ስለአወሳሰዱ እንዲነግረው ጠየቀው፡፡ ሃኪሙ በጣም ተገርሞ፤
“ለመሆኑ መድሃኒቱ የተገዛው ከፋርማሲ ውስጥ ነው?” ጠየቀው
“አዎ” አለ ታካሚው፡፡
“ታዲያ እንዴት ፋርሚሲስቱ ስለአወሳሰዱ ሳይነግርህ ቀረ?” በማለት መድሃኒቱን ከነማዘዣው ከህመምተኛው ላይ ተቀብሎ አየው፡፡ ታካሚው በሃኪሙ ፊት ላይ ያየው ከፍተኛ ድንጋጤ እሱኑ ይበልጥ አስደነገጠው፡፡
“ችግር አለ?” ሲል ጠየቀው ሃኪሙን
“እርግጠኛ ነህ እኔ ላዘዝኩልህ የተሰጠህ መድሃኒት ይሄ ነው?” ሲል ጠየቀው ታማሚውን፡፡
“ጌታዬ 486 ብር የከፈልኩበት መድሃኒት እኮ ነው እንዴት ብዬ ከሌላ መድሃኒት ጋር እቀላቅለዋለሁ”
ለዚህ መድሃኒት መግዣ ያወጣውን 486 ብር ለማግኘት የተጋፈጠውን ውጣ ውረድ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፡፡ ሃኪሙ በጣም አዘነ፡፡
ታካሚው ከፋርማሲ ገዝቶ ያመጣው መድሃኒት፤ ለማህፀን ህክምና የሚያገለግልና ለሴቶች ብቻ የሚታዘዝ ነበር፡፡ ሁኔታው እጅግ ቢያስደነግጠውም ለመድሃኒቱ ያወጣው ገንዘብ ኪሣራ ላይ ሊወድቅ መሆኑ ይበልጥ አበሳጨው፡፡ ወደ ፋርማሲው ሄዶ ስለጉዳዩ በመንገር፣ ገንዘቡን እንዲመልሱለት ለማድረግ መድሃኒቱን ተቀብሎ ወደዚያው አመራ፡፡ ፋርማሲው ውስጥ ላገኘው ሰውም ሁኔታውን አስረዳ፡፡ በወቅቱ የተገኘው ባለሙያ፤ ከሰውየው ላይ መድሃኒቱን ተቀብሎ አየው፡፡ ምናልባት የፋርማሲ ባለሙያው በስህተት ሰጥቶት ሊሆን እንደሚችል ነግሮ፣ በማዘዣው ላይ የተፃፈውን መድሃኒት ሊሰጠው እንደሚችል አግባባው፡፡ ይሁን እንጂ ይህኛውም ሰው በመድሃኒት ማዘዣው ላይ የተፃፈውን ጽሑፍ በአግባቡ በማንበብ ተገቢውን መድሃኒት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ ይልቁንም “መድሃኒቱ እኛ ጋ የለም ሲል” ማዘዣውንና ታማሚው ቀደም ሲል የከፈለውን 486 ብር መልሶ በመስጠት አሰናበተው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ይህንን መረጃ ያገኘሁት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለህክምና መጥቶ ካገኘሁት አንድ ታካሚ ነው፡፡ ታካሚው ከሃኪሙ የተፃፈለትን መድሃኒት በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ከሚገኘው የመድሃኒት መሸጫ ፋርማሲ ለማግኘት ባለመቻሉ ነበር መድሃኒቱን ፍለጋ ከተማውን ሲያስስ የከረመው፤ ይሁን እንጂ በአብዛኛው መድሃኒት ቤቶች ውስጥ መድሃኒቱን ለማግኘት አልቻለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከበሽታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝና ምናልባትም ለከፋ ችግር ሊያጋልጠው የሚችል መድሃኒት ባለሙያ ነኝ ብሎ ከተቀመጠ የመድሃኒት ቤት ሰራተኛ መሰጠቱ ነው፡
ወደ ሆስፒታሉ ተመልሶ የመጣው ሃኪሙ መድሃኒቱን በሌላ መድሃኒት ቀይሮ እንዲፅፍለት ለመጠየቅ መሆኑን አጫውቶኛል፡፡ ለፍለጋው በተዘዋወረባቸው በርካታ መድሃኒት ቤቶች ውስጥ ያገኛቸው የፋርማሲ ባለሙያዎች፤ በማዘዣው ላይ የተፃፈው የሃኪሙ የእጅ ጽሑፍ ፈጽሞ የማይነበብ መሆኑንም ነግረውታል፡፡ ስለዚህም ሃኪሙ ሊነበብ በሚችል መልኩ ማዘዣውን እንዲፅፍለት እንደሚጠይቀውም ገልፆልኛል፡፡
አለም አቀፉ የጤና ድርጅት (WHO) ለፋርማሲ ሙያ በሰጠው ትርጓሜ፤ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት፣ ከሃኪም በሚሰጠው ትዕዛዝና መመሪያ መሠረት፣ መድሃኒቶችን ለህሙማን ማደል፣ ስለመድሃኒቱ አወሳሰድ፣ መድሃኒቱ ስለሚኖረው የጐንዮሽ ጉዳትና ከመድሃኒቱ ጋር ሊወሰዱና ላይወሰዱ ስለሚችሉ ምግብና መጠጦች በግልጽ ለህመምተኛው የሚያሳውቅ ሰው ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያው መድሃኒቶችን ለህሙማን ከማደል በዘለለ ከህሙማኑ ጋር ጥብቅ መግባባትን ማድረግ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ባለሙያው ሁልጊዜም ከህመምተኛው ጀርባ ሆኖ ስለህመምተኛው የሚጨነቅና የሚያስብ ሰው ነው፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ት/ቤት መምህር ዶክተር ተስፋዬ ታረቀኝ እንደሚናገሩት፤ “የፋርማሲ ሙያ እንደ ህክምና ሙያ ሁሉ ትልቅ ከበሬታ ሊሰጠው የሚገባና በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ሃይልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎች ከህክምና ባለሙያዎች ጋር ጥብቅ ትስስር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የፋርማሲ ባለሙያ ማለት ከሃኪሙ በሚሰጠው ማዘዣ መሠረት ታማሚው መድሃኒቱን በአግባቡ መውሰድ እንዲችል ተገቢውን መመሪያ የሚያስተላልፍ ሙያተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የሚታየው ነገር ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ታካሚው መድሃኒት ፍለጋ በሚሄድባቸው ፋርማሲዎች ውስጥ ያሉ ሰዎች ሙያውን በሚገባ ያውቁታል ለማለት ፈፅሞ አያስደፍርም፡፡ አንዳንድ ፋርማሲስቶች፤ የመድሃኒት ማዘዣዎች አልነበብ ሲላቸው፣ በደንበኞች ፊት ሃኪሞችን ከፍ ዝቅ አድርገው ሲሳደቡና ሲያዋርዱ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ለሙያው የሚሰጠውን ግምት በእጅጉ የሚያወርድና በሃኪሙና በህመምተኛው መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚያደርግ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመድሃኒት ማዘዣዎችን በሚገባ አንብቦና ተረድቶ መድሃኒቶችን ለህሙማን የሚያድል የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘቱ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው”
በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሃኪም መድሃኒት ከታዘዘላቸው ታካሚዎች ከአምስቱ አንዱ መድሃኒቶችን በስህተት ይወስዳል፡፡ ሃኪሞችን የፋርማሲ ባለሙያዎችን፣ ነርሶችንና ህሙማንን ያካተተው ጥናቱ፤ በመድሃኒት አስተዛዘዝ ዙሪያ ከባድ ችግር እየተከሰተ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች የሚጽፉት የመድሃኒት ማዘዣ የማይነበብና የተሟላ መረጃ የሌለው ሲሆን የሃኪሙን የእጅ ጽሑፍ በሚገባ አንብቦና ተረድቶ ተገቢውን መድሃኒት ለህመመተኛው የሚሰጥ የፋርማሲ ባለሙያ ማግኘትም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
ህሙማኑም ስለታዘዘላቸው መድሃኒት አወሳሰድ ሃኪማቸውን አይጠይቁም፡፡ የፋርማሲ ባለሙያዎቹም፤ ለህሙማኑ መድሃኒቱን ሲሰጡ ስለአወሳሰዱ፣ ስለመድሃኒቱ ባህሪያትና ስለጐንዮሽ ጉዳቱ አይናገሩም፡፡
ይህ የሚያሳየው ደግሞ ህመምተኛው ስለሚወስደው መድሃኒት ምንነትና አወሳሰድ ሳያውቅ በስህተት መድሃኒቶችን ለመውሰድ መገደዱን ነው፡፡
በጥናቱ እንደተመለከተው፤ ብዙውን ጊዜ ህሙማን መድሃኒት ፍለጋ ከፋርማሲ ፋርማሲ የሚንከራተቱት መድሃኒቱ በፋርማሲው ሳይገኝ ቀርቶ ሳይሆን የፋርማሲ ባለሙያው ማዘዣውን አንብቦ መረዳት ባለመቻሉ ምክንያት መሆኑን አመላክቷል፡፡ ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና ሁሉም ሙያተኞች የሙያውን ሥነምግባር አክብረው፣ ተገቢውን ህክምናና መድሃኒት ለህመምተኛው መስጠት እንዳለባቸው ይኸው ጥናት ይገልፃል፡፡
በሰለጠነው ዓለም የመድሃኒት ማዘዣዎች በዲጂታል ማሽኖች እየተተኩ ነው፡፡
ልክ እንደ ባንክ ኤቲኤም ማሽን፣ በደንበኞቹ በቀረበለት የመድሃኒት ማዘዣ መሠረት ትክክለኛውን መድሃኒት አውጥቶ ከነአወሳሰድ መመሪያው ለህሙማኑ መስጠት የሚችል መሣሪያ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡
መድሃኒቶች ከበሽታ በመፈወስ ነፍስን የመታደጋቸውን ያህል በአግባቡ ካልተያዙና አገልግሎት ላይ ካልዋሉ አጥፊ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ስለዚህ ለህይወት ደህንነት የተሰራልን መድሃኒት አጥፊያችን እንዳይሆን፣ እራሳችንን ጨምሮ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡       

Read 6316 times