Saturday, 26 September 2015 09:12

የቡድን ስራን ከአዕዋፍ መማር፤ በአየር ከማሳበብ ቀድሞ ማገናዘብ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     ከእርሻና እና ደን  ተመራማሪው  አቶ ደቻሳ ጅሩ ጋር በኢትዮዽያ አትሌቲክስ ዙርያ  ያደረግነውን ቃለምልልስ ሰፊ ነበር፡፡ የመጀመርያውን ክፍል ባለፈው ሳምንት ማስነበባችን የሚታወስ ነው፡፡ አቶ ደቻሳን ተዋውቀናቸዋል፡፡ ስለሙያቸው  ገለፃ አድርገው፤ ከአትሌቲክስ ስፖርት እንዴት እንዳዛመዱት አብራርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሳይንስን በመቅረብ መንቀሳቀስ እንዳለበት የሚመክሩት ተመራማሪው፤  አትሌቲክሱን የሚመራው አካል ስፖርቱን በሚያጠናክሩ እና በሚያሳድጉ አቅጣጫዎች የሚሠራበትን ሁኔታን አነቃቅተዋል፡፡ በየዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ከስፖርቱ ጐን በመራመድ እንደ አማካሪ አካል ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም  አስገንዝበዋል፡፡
የአትሌቶችን ውጤት በመፈታተን ለከፍተኛ ውጣውረድ የሚዳርጉ በርካታ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ የጤና መጓደል፤ በስነልቦና ያለመረጋጋትን ጨምሮ፤የግል ብቃት፤ ከአሰለጣጠንና አቀባብል ጉድለትና ከመሳሰሉት የሚመነጩ ክፍተቶች ጉልህ ተፅእኖ በመፍጠር ከውድድር ውጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህን በተመለከተ አቶ ደቻሳ ጅሩ በቃለምልልሱ ሁለተኛ ክፍል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትኩረት ሊሰጣቸው  በሚያስፈልጉ አቅጣጫዎች ባደረጓቸው  አስደናቂ ምርምሮች ዙርያ ያተኩራሉ፡፡ መልካም ንባብ
ወደ ዋናው ጉዳያችን  ሳንገባ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ አስተዋፅኦ ለማድረግ የተነሳሱባቸው ተጨማሪ ሁኔታዎች ካሉ?
ለአትሌቶቻችን እንደፈለግኩት አስተዋፅኦ የማደርገው ምን አቅም ኖሮኝ ነው፡፡ አንድ የማስበው ጉዳይ ግን አለ፡፡ እንደኔው እድሜያቸው ለገፋና ለተዳከሙት አሰልጣኞች በሁሉም ዘርፍ ያለን ባለሙያዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ ከ1990 እስከ1994 እ.አ.ኤ በፈረስ ግልቢያ በምትታወቀው አውስትራሊያ የእርሻና ደን ጥምር ጥናት ላይ እንደነበርኩ ነግሬሃለሁ፡፡ ያኔ መላው ዓለም በረሃብተኛነት  መሳለቂያ ሲያደርገን  ክቡራን አርማዎቻችን የነበሩት አትሌቶቻችን ናቸው፡፡ ባንድ ወቅት በተካሄደ ውድድር ኢትዮጵያዊ አትሌት ካሸነፈ በኋላ እንደማስመለስ ሲያደርገው ሁኔታውን የተቀበለው አልነበረም፡፡  በወቅቱ እነከበደ ባልቻ ለውድድር ወደ አውስትራሊያ ሲመጡ እንደ ነገ ሊሮጡ በዋዜማው ነበር የሰማነው፡፡  በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ ንፋሱ ሃይለኛ ከመሆኑ ባሻገር ከቅዝቃዜ ጋር ተዳምሮ መሰናክልነቱ ከበድ ይል ነበር፡፡ ምን ማድረግ እችላለሁ ብዬ በማሰብ  በለሊት ሩጫው በሚካሄድበት መንገድ በእግሬ ቀድሜ ደረስኩ፡፡ በውድድሩ ጎን ለጎን ተሩዋሩጬ ንፋሱን የሚከላከሉበትና ፋይዳቸውን የሚያጎሉበትን ዘዴ ለማቀበል  አቅጄ ነበረ፡፡ ተግባራዊ ላደርገው አልቻልኩም፡፡ እኔ ንፋስ እነሱ አውሎንፋስ ሆኑብኝ፡፡ ምናልባት ብስክሌት ቢኖረኝ ኖሮ መልእክቴ በትክክል ይተላለፍ ነበር፡፡ ግን ነጭ ልብስና ባርኔጣ አድርጌ በየአቁዋረጩ እየቀደምኩ ከረጅምና ወፍራም አትሌት ስር ገብታችሁ በጋሻነት እንደንፋስ መከላከያ ተጠቀሙባቸው እያልኩ የነበረ ቢሆንም አድናቂያቸውና ለማበረታታት የምጮህ ወገናቸው እንጂ የባለሙያ ድጋፍ ነው ብለው በፀጋ መልእክቴን መገንዘብ አልቻሉም፡፡ በመግቢያ አካባቢ ራሱን እየጠበቀ የሚሮጥ ለንፋስ ያልተጋለጠው  አሸነፋቸው፡፡ የኛ ከሁለት እከ 4 ተከታትለው ወጡ፡፡ እርስ በራስ ተፋጭተው ለውጪው እንደመሪ ወፍ ሃይላቸውን ጨረሱ፡፡ ከዚህ አጋጣሚ በኋላ በአትሌቲክሱ ሳይንሳዊና ጥበባዊ ግንዛቤን የማስፋፋት ቁጭት አደረብኝ፡፡ ይገርመሃል ያኔ የእኛ አትሌቶች ጫማቸው የተበጣጠሰና አሮጌ  ከመሆኑም በላይ ሰውነታቸውም የተጎሳቆለ ነበር፡፡  እኔ ማነኝ ተራ ሰው፡ አትሌቶቻችን አስደስተውናል ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ህይወት የሚሰዋላቸው ጀግኖች ናቸው፡፡ ያኮሩን  አንገት እንዳንደፋ ነፍስ የዘሩብን  ናቸው፡፡ ለእነሱ ምርምር በማድረግ ውሳኔዬ እጅግ ረካሁ፡፡ በቤቴም ሆነ በስራዬ ምርጥ ነገር መጠቀም እድሉ ቢኖርም ጨርሶ አልመኝም፡፡ በተሰለፍኩበት ውጤታማ ስሆን ብቻ ነው ውስጤ የሚቀበለው፡፡ ከአትሌቶቻችን ሁሉ በተለይ ጥሩዬን በጣም አደንቃታለሁ፡፡ ሎተሪ ቢደርሰኝ በቀድሞ ካራማራ ሆቴል ላይ ተጀምሮ ያዘገመውን ቤት ማስጨረሻ አዋጣላታለሁ፡፡ ገንዘብ ካላገኘሁ የምድረ ግቢ ውበት ላይ የሞያ እገዛ ላደርግላት እቅዱ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ከምትሰራው ሆቴል ፊት ለፊት ያለውን የወርልድ ባንክ ምድረግቢ ዛፍና የውስጥ ገነተ ድንጋይ መሬት (ሮክ ጋርደኑን) የሰራውት እኔ ነኝ፡፡ ለአትሌቶቻችን ያለኝ ፍቅር በዚህ የሚገለፅ ይመስለኛል፡፡ የአውስትራሊያ የትምህርት ቆይታዬ እንደጣሊያኑ ቆይታ የእውቀትና ልምድ ግብይት ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡ ተሰደው ከአገር የወጡት በመንገዱ የሚደርስባቸው በየጊዜው ሲያገጥመኝ ናለዬን ያዞረው ነበር፡፡ ባጭሩ እራሴን ከተሰቃዩት ጋር አሰቃየሁ፡፡ በስፖርቱ ባለኝ ፍቅር ብቻ ሳልወሰን በትምህርትም በማህበራዊ ችግርም ቀንደኛ ተሳታፊ ሆኜ በባህርማዶ የነበረኝን ህይወት አልፌበታለሁ፡፡  ጺሜን አሳድጌ የምትመለከተው ይህ አይነቱ ብሄራዊ ፍቅር ለመግለፅ ነው፡፡ ሌላው ያለእድሜው እየሸበተ  ጥቁር ቀለም ሲቀባ የኔ ራስ ገባ ከማለት ውጭ ፀጉሬ አልሸብት አለኝ፡፡ ጺሜን ነጭ ቀለም ለመቀባት ሁሉ ሞክሬ ነበር፡፡  የተፈጥሮ አልመስል ሲለኝ መልሼ አጠቆርኩትና ተንዠርጎ ቀረ፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት መዳከም ከሚጠቀሱ ችግሮች አንዱ የቡድን ስራ መጥፋት ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለሚበላሹ ውጤቶችም እንደ ዋና ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ እርሶም ደግሞ የቡድን ስራ ከአዕዋፍ ስለመማር ይናገራሉ?
እንደ አዕዋፍ የቡድን ስራ ቢኖረን ብዙ ውጤት በተቀየረ፤ በጨመረ ነበር፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጣችሁ ብትመለከቱ እጅብ ብለው ከሚበሩት ወፎች የሚገርም ተመክሮ ትገነዘባላችሁ፡፡ በረራቸውን ሁሌም ስናስተውል አንዲት መሪ ወፍ ቀድማ ትበራለች፡፡ ከፍተኛ የግፊት ችግርን ተቁዋቁማ ነው ሙሉ ሃይልዋን ተጠቅማ አየሩን እየሰነጠቀች ትበራለች፡፡ ክንፍዋም ዕረፍት የለውም፡፡ የቀሩት ግን ስራቸው ተከታዮች መሆን ነው፡፡ ተከታዮች በግምት የከ20-3ዐ ዲግሪ የሚሆን ማዕዘን  ሰርተው ቀጥ ባለ የመስመር ጉዞ ይከተላሉ፡፡ ክንፋቸውን ብዙ አያወዛውዙም፡፡ መሪዋ በቀደደችላቸዉና ባመቻቸችላቸዉ የአየር መንገድ እየተዝናኑ ይበራሉ፡፡ የመሪነቱ ቦታ በጣም አድካሚ በመሆኑ በአንድ ፈር ቀዳጅ በሆነ በተወሰነ ወፍ የሚደረገው በረራ አስቸጋሪ በመሆኑ ቶሎ ቶሎ ይፈራረቃሉ፡፡ በአትሌቲክሱ ልንተረጉመው የምንችል ተመክሮ ነው፡፡ በሰው በኩል ይህ አይነት ዘዴ በቀጥታ የሚጠቅመን ንፋሱ ሃይለኛ ሆኖ ሲያሰናክለን ብቻ ነው፡፡ ንፋሱ ሲከፋ እጅግ ለጥቃት የሚጋለጡት ረጃጅም አትሌቶች ናቸው፡፡ ፊትም ቀደሙ መሃል ወይም ከሁዋላ ቢከተሉ ወሳኝ የሆነው ራሳቸው በኩል ልክ እንደ ረጅም ማሽላ ..አንድም ለወፍ አሊያም ለወንጭፍ.. እንደሚባለው ተጠቂ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በማራቶን ያለው አማራጭ በቁመት የሚመጥነውን ፈልጎ ወደንፋስ አቅጣጫ አድርጎ እንደጋሻ መከለከያ ማድረግ የሚቻልበትን ታክቲክ መቀመር ያስፈልጋል፡፡ ወደ አዕዋፍቱ ስንመለስ የምንገነዘበውም ይህንኑ ነው፡፡ በመሪ በመሆን የሚደረገው መስዋዕትነት አቀጣጣይና ተቃጣይ በሚባሉት የሯጮቻችን የቡድን ሥራ ድርሻ ጋር የሚዛመድ ይሆናል፡፡ በሕብረት ስራነቱ ግን መጠቀም ይቻላል፡፡   ይህንን የቴክኒክ እድል እስከዛሬ በትክክል መገንዘባችንን አልፎም መጠቀማችንን ወይም ያለመጠቀማችን ለኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ብቸኛው አማራጭ ግን አይደለም፡፡ በቁመቱ ረዘም ካለ ተፎካካሪ የውጪ ሯጭ ኋላ መከተልና ቀዳሚውን በንፋስ መከላከያነት መጠቀሚያ አድርጎ ለራስ የምቾት እድልን በማስፋት የመስራት ታክቲክን እንደምረዳው የሚጠቅም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ዝርዝር የቴክኒክ ዘዴ በሜትሮሎጂ ከአየር ሃይል የኤሮኖቲክስ ባለሞያ ጋር በመገናኘት የየበኩላችንን ብሄራዊ አስተዋጽኦ በማድረግ በምርምሩና በትግበራው መስራት አለብን፡፡ እዚህ ጋር የንፋስን መሰናክልነት፤ የመከላከል ሳይንሳዊ ቴክኒክ ከተቀበልንና ከተገበርን ነው፡፡ ይሁንና በረራው ውጤቱን ቀኝ ኋላ እንዳይዞርብን አበክሬ ለማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡
ሌላው በአትሌቲክሱ ውጤት መዳከም የሚቀርብ ማመካኛ የ“አየሩ ከበደኝ” ሁኔታ ነው፡፡  የአየር ተስማሚነት በአትሌቲክሱ ላይ የሚፈጥረው ጫናን እንዴት ያብራሩታል?
የአየር ተስማሚነት መረጃ እንኳንስ ገና በእድገት ላይ ለምትገኘው ኢትዮዽያ ቀርቶ በሳይንሱ መጥቀዋል የተባሉትንም አገራት ያን ያህል አልጠቀመም፡፡ መረጃዎችን ሰብስቦ፤ አቀናጅቶ እና አገናዝቦ  ወደ መሬት በማውረድ ለመስራት ቢያስፈልግም ያሉት ክፍተቶች በተመጣጠነ መልኩ አልጠበቡም፡፡ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ በአየር ትንበያ ዙርያ በመገናኛ ብዙሐናት የሚሰራጩት የሙቀት፣ ንፋስና ርጥበት፣ መረጃዎች ከመለኪያ መሳሪያዎች በቀጥታ የሚነበቡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቢቢሲ ትንበያ መሰረት የአዲስ አበባ የአየር ሁኔታ ሲገለፅ ከፍተኛው ሙቀት 19 ዲግሪ ሴቲግሬድ ነው ተባለ፡፡ በመንገድ ላይ የሙቀት መለኪያ መሳሪያውን በክፍት መኪና ላይ ይዘን ብንሄድ ተመሳሳይ  መጠን ያሳየናል፡፡ አብሮን ያለ ተሳፋሪ ሰው ግን ብርድ ይመታኛል በማለት መስኮት ይዘጋል፡፡ ብርድ በሚበረታበት የግጦሽ ቦታ፤ ከብቶችን ከንፋስ ለመከለል፣ መከላከያ ዛፍ በመጠቀም ተስማሚ የሙቀት ሁኔታን በመፍጠር የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የተገናዘበ መረጃን አመንጭተዋል፡፡ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት የኢኮኖሚያቸው ዋና ምንጭ በሆኑት የሱፍ በጐች ላይ የደረሰው እልቂት መነሻቸው ነበር፡፡ 40ሺ የሱፍ በጐቻቸው ጸጉራቸውን በተሸለቱበት ዕለት በአንድ ሌለት የንፋስ አቅጣጫ ተለውጦ በሙሉ አልቀዋል፡፡ የሳይንቲስቶቹ የፈጠራ ግኝት ይህን አይነት አደጋ ለመከላከል ያገዘ ነው፡፡
ንፋስ  20 ኪ.ሜ. በሰአት ከነፈሰ ለሰውም ሆነ ለእንስሳ 8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የቀነሰ የሙቀት ስሜትን ያስከትላል፡፡  ለምሳሌ የአዲስ አበባ አየር ጸጥ ያለ እንቅስቃሴ 0.0 ቢሆንና ገንዘቤ በ20 ኪ. ሜ በሰአት ፍጥነት ብትሮጥ ወደ ራስዋ ተመሳሳይ ፍጥነት ያለውን ነፋስ አነፈሰች ወይም ፈጠረች ማለት ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን ቴርሞሜትር የሚያነበው በተለምዶ የምናየውና የምንሰማውን 19 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው፡፡ ገንዘቤን የሚሰማት ግን ወደ ታች የወረደውን 11 ወይም የ12 ዲግሪ ሴንትሬድ ነው፡፡ በመሆኑም ንፋስ በቀዝቃዛ ቦታ ጫና ሲሆን በሙቀት ቦታ ፋታ ይሆናል የሚለው ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ርጥበት (Humidity) በሙቀት ቦታ አስጨናቂና መሰናክል ሲሆን በቀዝቃዛ ቦታ ደግሞ አያሰናክልም ፡፡ ለምሳሌ በአገራችን የሜትሮሎጂ ሰዎች ከአሜሪካ ሳይንቲስት የሳይንስ ጆርናል በመውሰድ ለጤና ጥበቃ በተለይ ለወባና ለሌሎችም ጫናን በመገመት መፍትሔ በመፈለግ ላይ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ዙሪያ በእንስሳ ላይ የተሰሩ ዋናው ነገር መሠረታዊ መረጃዎችን ተንትኖ አቀናጅቶና አጠናቅሮ የአየር ተስማሚነትን በመተንበይ መስራት ነው፡፡ በአትሌቲክስ ሲተረጎም ለአትሌት ወደፊት የሚሮጥበት ቦታ መሰናክሉንና ፋይዳ እድሉን ማወቅ ነው፡፡ የትኛው አትሌት ይፈይድበታል፤ የትኛውስ ይጠቃል፤ በምንስ ያህል፤ የሚለውን የአገራችን ብቻ ሳይሆን አስጊ ተፎካካሪን ለይቶና አውቆ በማስቀመጥና በመስራት ስልት መተለም ይቻላል፡፡
የዛሬ 11 ዓመት በግሪክ ኦሎምፒክ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቶች አሰልጣኝ የአየር ጫና ለሁሉም ተወዳዳሪ እኩል ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሌላ ታዋቂ አትሌትም ይህንኑ አባባል መድገሙን አስታውሳለሁ፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ዛሬም ሳይንሳዊ መረጃ አያስፈልግም የሚል አመለካከት እንደሰፈነ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች  በሳይንስ እውቀት የገዘፉትን  አገራት አሸንፈናል የሚለው አመለካከት ሊቀየር አለመቻሉ ከፍተኛው መሰናክል እንደሆነ ማመልከት እፈልጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ይወክለናል ፤ ያገባናል የምንል ሰዎች ደግሞ ይህ አይነቱን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ለማስቀረት ጫና መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡ የአየር ሁኔታ፤ የምግብ፤ የጤና፤ የስነልቦና፤ የዘረመል፤ እንዲሁም የስነ ምዳር ባለሙያዎችና የመሳሰሉት በጥናት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን የማቀበል ድርሻቸው መጠናከር አለበት፡፡ ሁላችንም ሃላፊነትና ግዴታም አለብን፡፡ ማንኛውንም ተግባር በጥራትና ለማከናወንና ፉክክር ባለበት ሰብሮ ለመውጣት የተፎካካሪን የብቃት ደረጃና ደካማ ጐኑን ማወቅ ግድ ይላል፡፡ በዚህ ሰላማዊ ፍልሚያ ሳይንሱን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከመገንዘብ አልፎ ማገነዛዘብም ይጠይቃል፡፡ የተቀናጀ የመረጃ አሃዝ እንደአየሩ ሁኔታ ስለሚለዋወጥ የሚወጣው ተለዋዋጭ ስልት በተዋኙ/ተዋኝዋ አትሌት ግንዛቤው መጨበጥ የግድና የግድ ይላል፡፡ ካልሆነማ ምኑን ተፋለሙ ማለት ይችላል፡፡
የአገራችን ስነምህዳር በፍጥነት ለሚሮጥ ወይም ለሚከንፍ ሰውም ሆነ እንስሳ እጅግ በጣም ግርድፍ ነው፡፡ የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የአገራቸውን አየር ሲከፋፍሉ የቀረውንም አለም ከራሳቸው አከፋፈል አኳያ አገናዝበውታል፡፡ ለአገራቸው ተስማሚ የሆነውን እንስሳ፤ ለምሳሌ ፈረስ ከየት ብናመጣ የተሻለ ተመችቶት ይሮጣል ብሎ ለመወሰን ስለሚያስችላቸው የቀረውን ዓለም ሁኔታዎች በማጥናት ምርምር አድርገዋል፡፡ ከሜልቦርንና ታዝማንያ የመጣው ነጭ ባህርዛፍ በአዲስ አበባ ላይ ውጤት ማሳየቱን ከዛፍ ዘረመል ሳይንቲስቶች ጋር በአንድ አጋጣሚ አብረን በሰራንበት ወቅት የተረዳሁት ነው፡፡ ከበቆጂ 10 ኪ.ሜ ርቃ በስተሰሜን ከምትገኘው ሊሙ የተባለች የተስማማውን ዘረመል አግኝተናል፡፡ በአየር ንብረት ምስስል የአገራችን ከፍተኛ ተራራ ደጋው አካባቢ ማለት ነው፤ ከነሱ አከፋፈልና ግንዛቤ በላይ መሆኑን በዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ከአየር ተስማሚነቱ በተገናኘ የቦታ ስምምነትም ለአትሌቲክስ ውጤት ፋይዳ አለው ማለት ነው?
እሱን ለመረዳት በ2000 እ.ኤ.አ በሲድኒ ኦሎምፒክ የተመዘገበውን ውጤት ማስታወስ ይበቃል፡፡  በ5ሺ ሜትር ወንዶች ሚሊዬን ወልዴ በሲድኒ ኦሎምፒክ ላይ በወጣትነት የወሰደውን የወርቅ ሜዳልያ ለምን አልደገመም? የደራርቱ ብቃት ምንም እንኳን ጥያቄ ውስጥ ባይገባም፤ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ የተጐናፀፈችው ከአራስነት ተነስታ መሆኑስ፤ እነዚህን ሁኔታዎች በማስተዋል የቀረበ ምርምር የለም፡፡ ለእነዚያ አስደናቂ ውጤቶች የአየሩ እጅግ ተስማሚ መሆን አስተዋጽኦ እንደነበረው በርግጠኝነት መመስከር ይችላል፡፡ በሲድኒ ኦሎምፒክ 2000 እ.ኤ.አ ላይ አራት ወርቅ የተገኘው በአራት የተለያዩ አትሌቶች ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በኦሎምፒክና ዓለም ሻምፒዮና ሁለት ታዋቂ አትሌቶች በልዩ ብቃት የወርቅ ሜዳልያዎችን እያስመዘገቡ ቆይተዋል፡፡ የተለየ ለውጥ ማየት እና የስኬታማ አትሌቶች ብዛት ማየት ግን አልተቻለም፡፡ በእኔ አስተያየት በሲዲኒ ኦሎምፒክ በአራት የተለያዩ አትሌቶች 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች መሰብሰብ የተቻለው በዋናነት የቦታውን ተስማሚነት የፈጠረው እድል ነው፡፡  በ2004 እ.ኤ.አ ግሪክ ባስተናገደችው ኦሎምፒክ የነበረው አየር በጣም በመሞቁና ወበቅ ስላለው ቀነኒሳን በአንድ ወርቅ አስቀረው፡፡ በአንፃሩ የሞሮኮው ኢል ጋሩዥ ከተመሳሳይ ቦታ ተነስቶ የተወዳደረ ስለነበር የወርቅ ሜዳልያውን ነጥቆታል፡፡ የግሪኳ ከተማ አቴንስ በክረምት ፀሐይ ሰሜን ንፍቀ ክበብ ላይ ስለሆነች ሙቀቱም ሆነ እርጥበቱ ተዳምሮ መሰናክሉ ይከፋል፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ጫና ነው፡፡ በአውስትራሊያዋ በሲድኒ ግን በተቃራኒው ተመሳሳይ አየርና ቦታ ላይ ስለሆነ ፋይዳ በፋይዳ ሆናልናለች፡፡ አየር ሙቀትና እርጥበት ለሁሉም እኩል ነው ተብሎ የሚሰጠው አስተያየት  የስህተት ድግግሞሽ ነው፡፡ በስንት ሳይንቲስት የሚታገዙትን የውጭ አትሌቶችን በራሳችን መንገድ አሸነፍን እየተባለም ነበር፡፡ እስቲ በሳይንስ የሚታገዙትን እንይ አሜሪካ ቅርብ ጊዜ ማራቶን እያሸነፈች አይደለም ወይ?  ….. ይቀጥላል

Read 3864 times