Saturday, 26 September 2015 09:16

የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚዳንት በሳምንታቸው ወደ ስልጣናቸው ተመለሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ወታደራዊው ሃይል ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባካሄደው መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን የወረዱትና በግዞት የቆዩት የቡርኪና ፋሶው የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ረቡዕ ዕለት ወደ ስልጣናቸው መመለሳቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ሚሼል ካፋንዶ ወደስልጣናቸው መመለሳቸውን ይፋ ያደረጉት፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪና ለአንድ ሳምንት በስልጣን ላይ የቆዩት የአገሪቱ መሪ  ጄኔራል ጊልበርት ዴንድሬ የስልጣን ሽግግሩን ለመታዘብ ወደ አገሪቱ በመግባት ላይ የነበሩ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ለመቀበል ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ባመሩበት ወቅት ነው ብሏል ዘገባው፡፡
የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኢኮአስ በሽግግር መንግስቱና በወታደራዊው ሃይል መካከል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት ያስችላል በሚል ባቀረበው የድርድር ሃሳብ መሰረት፣ አገሪቱ ወደ ብጥብጥ እንዳትገባ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከቤተ መንግስቱ እንዲርቁ መደረጋቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ኮፋንዶ ወደ ስልጣናቸው እንደተመለሱ ማወጃቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡በወታደራዊው ሃይልና መፈንቅለ መንግስቱን በተቃወሙ የአገሪቱ ዜጎች መካከል በተነሳው ግጭት ከ10 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎችም መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር ላይ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ከስልጣናቸው የወረዱትን የቀድሞውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ብሌስ ኮምፓዎሬን ተክቶ መንበረ መንግስቱን የተረከበው የቡርኪና ፋሶ የሽግግር መንግስት፣ በመጪው ጥቅምት ወር በሚደረግ ምርጫ ስልጣኑን ለማስረከብ እቅድ እንደነበረውም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1582 times