Saturday, 26 September 2015 09:17

ሩስያዊው ባለጸጋ የአገራቸውን መንግስት በ10 ቢ. ዶላር ከሰሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 መንግስት በበኩሉ፣ ከ700 ሚ ዶላር በላይ በመዝረፍ ከሷቸዋል
   ሩስያዊው ቢሊየነር ሰርጊ ፑጋቼቭ፣ ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን እና ታማኞቻቸው በህገወጥ መንገድ በሸረቡብኝ ሴራ ግዙፉን የባንክ ኩባንያዬን ለኪሳራና ለውድቀት ዳርገውታል፣ የአገሪቱ መንግስት 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ሊሰጠኝ ይገባል ሲሉ ክስ መመስረታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ከታዋቂ የአገሪቱ ባንኮች አንዱ የነበረው ሜዝፕሮም ባንክ ድንገት ተንኮታኩቶ የወደቀባቸውና በባንኩ ዘርፍ ከሚታወቁ የአገሪቱ ባለጸጎች አንዱ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሰርጊ ፑጋቼቭ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲንና ታማኞቻቸው ዋና ዋናዎቹን ንብረቶቼን ነጥቀው ኩባንያዬን ለውድቀት ዳርገውታል ሲሉ፣ ባለፈው ሰኞ ዘ ሄግ በሚገኘው ቋሚ የግልግል ፍርድ ቤት ላይ ክስ መመስረታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የሩስያ መንግስት በበኩሉ፤ እ.ኤ.አ በ2008 ተከስቶ የነበረውን የገንዘብ ቀውስ ተከትሎ ሜዝፕሮም የተባለውን የግለሰቡን ባንክ ለመደጎም በማሰብ የመደበውን ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዘርፈው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል፣ በስደት እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙት ሰርጊ ፑጋቼቭ ላይ ክስ መመስረቱንና ግለሰቡ ተላልፈው እንዲሰጡት የእንግሊዝን መንግስት እንደጠየቀ ያስታወሰው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን እያጣራ ባለበት ሁኔታ ላይ በመሃል ቢሊየነሩ ከእንግሊዝ መውጣታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሩስያን መንግስት ክስ ተከትሎ የእንግሊዝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተለያዩ የአለም አገራት ውስጥ የሚገኙና 1.3 ቢሊዮን ፓውንድ የሚያወጡ የሰርጊ ፑጋቼቭ ሃብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያዘዘ ሲሆን ቢሊየነሩ ግን ከሩስያ የተሰነዘረባቸውን ክስ፣ መሰረተ ቢስና ፖለቲካዊ መነሻ ያለው ውንጀላ ነው ሲሉ ማጣጣላቸው ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንት ብላድሚር ፑቲን ወደ ስልጣን እንዲወጡ በማገዝ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ቢሊየነሩ ፑጋቼቭ፣ ከእንግሊዝ ከወጡ በኋላ ወደ ፈረንሳይ ሳይሄዱ እንዳልቀሩ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1979 times