Saturday, 26 September 2015 09:18

ሳምሰንግ ከአይፎን መኮረጅህን አቁም ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሳምሰንግ ምርቶቼ በስፋት መቸብቸባቸውን ይቀጥላሉ ብሏል

      በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ቀዳሚዎቹ ተፎካካሪዎች ሆነው ለአመታት የዘለቁት ሳምሰንግ እና አይፎን፣ ፉክክራቸው ከገበያ አልፎ ችሎት የደረሰ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባላንጣዎች ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡
“ሳምሰንግ የራሱን ፈጠራ እንደመስራት የእኔን እያየ ይኮርጃል” በሚል ሲማረርና ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ለመሰረተው ክስ፣ ተገቢ ውሳኔ የሚያገኝባትን ዕለት ለአመታት በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው አይፎን ከሰሞኑ በለስ ቀንቶታል፡፡
በዋሽንግተን የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሃሙስ የተሰየመው ችሎት፣ “ከአሁን በኋላ ከአይፎን እያየህ መኮረጅህን እንድታቆም፤ ከዚህ በፊት የኮረጅካቸውን ሶፍትዌሮችም ዛሬ ነገ ሳትል መጠቀም እንድታቆም” ሲል ለሳምሰንግ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል - ሲኤንኤን እንደዘገበው፡፡
ሳምሰንግ በበኩሉ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ በሰጠው መግለጫ፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በምርቶቹ ተወዳጅነት ላይ ይህ ነው የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይፈጥር ገልጾ፣ ጋላክሲ በሚል መጠሪያ የሚያመርታቸው ስማርት ፎኖቹ በቀጣይም በአለም ዙሪያ በስፋት መቸብቸባቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል፡፡
አይፎን ፈጠራዎቼን እየኮረጀ አስቸግሮኛል በሚል በሳምሰንግ ላይ ክስ የመሰረተው ከ3 አመታት በፊት እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ወቅቱ ሳምሰንግ ኩባንያ ጋላክሲ ኤስ 2 የተሰኘውን ስማርት ፎን ለገበያ ያበቃበት እንደነበርና ከዚያ በኋላም፣ በዚህ አመት ለገበያ ያበቃውን ጋላክሲ ኤስ 6 ጨምሮ የተለያዩ አይነት የተሻሻሉ የጋላክሲ ምርቶቹን ማውጣቱን ጠቁሟል፡፡
አይፎን ክሱን የመሰረተው በጋላክሲ ኤስ 2 ላይ ሲሆን፣ ክሱ ሳምሰንግ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ያመረታቸውን ስማርት ፎኖች የማይመለከት በመሆኑ የፍርድ ቤቱ  ውሳኔ ለአይፎን ያን ያህልም ተጠቃሚ እንደማያደርገው ተዘግቧል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች በፈጠራ ባለቤትነት ጉዳይ መካሰስ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው የታወቀ ሲሆን በቅርቡም “ሳምሰንግ ከአይፎን ኮርጀሃል” በሚል 980 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበት እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

Read 3155 times