Saturday, 03 October 2015 10:09

‘ሁለት እግር አለኝ ተብሎ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(10 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እዚህ አገር በቃ ወሬና ተግባር እንዲህ ደመኛ ጠላቶች ሆነው አረፉት! ሀሳብ አለን… ‘የአደባባዩ እከሌ…’ ‘የጓዳው እከሌ’ እየተባለ የአደባባይና የጓዳ ባህሪያቶቻችን ይለዩልንማ! ከዛ በኋላ…አለ አይደል… “አንተ እኔ እንደዚሀ አይነት ሰው መሆኑን አላውቅም ነበር…” ምናምን አንባባልም፡
ስሙኝማ…የሆነ ነገር ሌላ ሰው ላይ ሲደርስ… አለ አይደል… ወይ ጀርባችንን እናዞራለን፣ ወይ “ቢሆንስ ምን አለበት!” ምናምን እንላለን፡ እኛ ላይ ሲደርስ ግን… ምን አለፋችሁ… የዓለም ጦርነት ምናምን ለመጀመር ምንም አይቀረንም፡፡
እናላችሁ፣ እሱዬው… “መቶ ብር እንኳን መጨመር አቅቷቸው ይኸው በአንድ ሺህ ብር ስንትና ስንት ዓመት እያሹኝ ነው…” እያለ እስኪሰለቻችሁ ይነዘንዛችኋል፡፡ “አሁንማ ባሪያቸው አደረጉን! የልጆቼ ነገር ሆኖብኝ ነው እንጂ…” ምናምን ይላል፡፡
ታዲያላችሁ ይኸው ሰውዬ ጫማውን አስጠርጎ ሁለት ብር ያወጣል፡ ሊስትሮውም… “ጋሼ፣ ዋጋው አራት ብር ሆኗል…” ይለዋል፡፡ ምን አለፋችሁ…ዓለም በጭንቅላቷ ትቆማለች፡፡
“እንዴት ያለ ዘረፋ ነው…ለፍርድ መቅረብ ያለባችሁ እናንተ እንጂ የጋዳፊ  ልጅ አይደለም…” አይነት ዲስኩር ያደርጋል፡፡ ለእኛ ሲሆን ‘ይገባናል’…ለሌላ ሲሆን ‘አይገባቸውም፡፡’
እግረ መንገዴን ይቺን እዩልኝማ… ሴትዮዋ የእንስሳት መብት ተከራካሪ ነኝ ባይ ነች፡፡ እሱዬው ደግሞ ቆዳ ጃኬቱን ግጥም አድርጎ በከተማው ሲወዛወዝ ፊት ለፊት ይገጣጠማሉ፡፡ እናላችሁ… እሷዬዋ ታቆመዋለች፡፡
“ትንሽ እንኳን ሀዘን አይሰማህም!” ትለዋለች፡፡
እሱም ደንግጦ “ለምን ብዬ ነው ሀዘን የሚሰማኝ! ምን አደረግሁና…” ምናምን ይላታል፡፡
እሷዬዋ ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ለለበስከው ቆዳ ጃኬት እኮ የአንዲት ምስኪን ላም ህይወት ጠፍቷል!”
እሷ እኮ ያደረገችው ቆዳ ጫማ ነው!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ልብ ብላችሁ እንደሆነ አንድ ሰሞን “ለምንድነው የአገር ውስጥ ምርት የማትገዙት?”
“እዚሀ አገር ከበቂ በላይ እየተመረተ ሰዉ የውጪውን ነው የሚፈልገው…” ምናምን አይነት ከቁንጥጫ መለስ ያለ ወቀሳ ይደርስብን ነበር፡፡
 እናላችሁ… ነገርዬው “የኢትዮጵያን ብቻ ግዙ…” አይነት ነገር መሆኑ ነው፡፡ (እኔ የምለው…እንዲብራራልን ስለምንፈልግ ነው፡፡ የቻይናም ዕቃ እንደ ‘ውጪ ዕቃ’ ነው እንዴ የሚቆጠረው! ቂ…ቂ…ቂ… ግራ ገባና!)
ኮሚኩ ነገር ግን እኛን የውጪ ምርቶች በማግበስበስ የሚወቅሰን ሰው መድረክ ላይ ተኮፍሶ የሚናገረው የአርማኒ ሱፍና የክላርክ ጫማ ግጥም አድርጎ እኮ ነው!
አንድ ጊዜ ሌኒን ሽክ ብሎ ንግግር ሲያደርግ… አለ አይደል… “አንተ ሽክ ብለህ፣ እኛ…” ምናምን እያሉ ምስኪኖች ያጉረመርማሉ መሰለኝ፡፡ እናላችሁ…ሌኒን ሆዬም፤ “የእኔ ትግል እናንተን ወደ እኔ ለማምጣት እንጂ ራሴን ወደ እናንተ ለማውረድ አይደለም…” አይነት ነገር ተናገረ ይባላል፡፡ ዘንድሮም በብዙ ነገር…“እናንተን እኛ ዘንድ ለማምጣት እንጂ ራሳችንን ወደ እናንተ ለማውረድ አይደለም አይነት ነገሮች በየቦታው ትሰማላችሁ፡፡
ደግሞላችሁ… “ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ህጻናት እየተበላሹ ነው…” ምናምን እያለ በየወርክሾፑ አንደኛ ተናጋሪ ነው፡፡ “መንግሥትም፣ ህዝብም ዝም ብለው እያዩ ነው…” ምናምን አይነት እርግማን ቢጤ ያደርሳል፡፡
ከዛማ… ሞባይሉን ያወጣና ምን ይላል መሰላችሁ… “ስዊቲ እንደምን ነሽልኝ! ከአራት ወር በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላሽ ትልቅ ውሻ የሚያስር የወርቅ ሀብል ነው የምገዛልሽ፡፡ ማታ እዛው ቦታ እጠብቅሻለሁ…” ይልላችኋል፡፡ በጀትን በዕቅድ ስለመጠቀምና አላስፈላጊ ወጪዎችን ስለማስቀረት የሚካሄደ ስብሰባ እኮ ድል ባለና ውስኪ እንደ ውሀ በሚረጭበት ኮክቴል የሚጠቃለልበት ዘመን ላይ ነን እኮ!
ስሙኝማ…የበጀት ምናምን ነገር ሲነሳ…አለ አይደል… በዛ ሰሞን በየቦታው ጎደለ የተባለው ያ ሁሉ ፍራንክ ወዴየት እንደሚሄድ ግርም አይላችሁም! ደግሞ ኮሌጆቹ መባሳቸው! አሀ…ኤኮኖሚስቶች አንድ ነገር በሉና! ለነገሩ እኮ…ዘንድሮ የኤኮኖሚስቶች ትንታኔ እኮ እንደ ‘ተጨባጭ’ ሁኔታ ነው ይባላል፡፡
 አለ አይደል… “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” ሲባል “ስንት እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለ እንደተባለው ኤኮኖሚስት ነገር ነው፡፡
በኤኮኖሚስቶች ላይ እንደ ቀልድም፣ እንደ ቁም ነገርም የሚነገሩ መአት ነገሮች አሉ፡፡ ይቺን እዩልኝማ…አንድ ሲቪል ኢንጂነር፣ አንድ ኬሚስትና አንድ ኤኮኖሚስት ገጠር ጉዞ ላይ ናቸው፡፡
 መሸት ሲል ከመኪና ወርደው አንድ ሆቴል ይገቡና መኝታ ይጠይቃሉ፡፡ የሆቴሉ ባለቤትም…“ያለኝ አልጋ ሁለት ነው፣ አንዳችሁ በረት ውስጥ ማደር አለባችሁ…” ይላቸዋል፡፡
እናላችሁ…ሲቪል ኢንጂነሩ ቀድሞ በረት ውስጥ ለማደር ፈቃደኛ ሆኖ ወደዛው ሲያመራ ሁለቱ ወደ አልጋቸው ይሄዳሉ፡፡
ብዙም ሳይቆይ የተኙበት ክፍል ይንኳኳል፡፡ ያንኳኳው ኢንጂነሩ ነው፡፡ እናማ… ገና ሳይጠይቁት ማውራት ጀመረ፡፡
“በረት ውስጥ አንዲት ላም አለች፡ እኔ ደግሞ እምነቴ ሂንዱ ስለሆነ ከተባረከችው እንስሳ ጋር ማደር አልችልም፣” ይላል፡፡ ኬሚስቱ ሊተካው ፈቃደኛ ይሆንና ወደ በረት ይሄዳል፡፡ ትንሽ ቆይቶ የመኝታ ቤቱ በር ይንኳኳል፡ ኬሚስቱ ሆዬ ገና ሳይጠየቅ ይዘረዝረው ጀመር፡፡
“በረት ውስጥ አሳማ አለ፡፡ እኔ ደግሞ ይሁዲ ስለሆንኩ ንጹህ ካልሆነ እንስሳ ጎን መተኛት አልፈልግም፡፡”  “ኤኮኖሚስቱ በተራው ወደ በረቱ ይሄዳል፡፡ ትንሽ ቆይቶ በሩ ይንኳኳል፡፡ በሩ ሲከፈት ማን ቢሆን ጥሩ ነው…ላሚቷኗ አሳማው! ምን አሉ መሰላችሁ… “ከኤኮኖሚስት አጠገብማ አንተኛም!”
እናም እንኳን እኛ አሳማና ላሚቱም ኤኮኖሚስቶችን አያምኑም፡ ቂ…ቂ…ቂ…
አንድ መጽሐፍ ላይ ያነበብኳትን ከዚህ በፊት ያወራኋትን ስሙኝማ… “እያወቀ እንዳላወቀ ሆኖ ዝም የሚል ሰው አለ፡፡ የማያውቅ ሆኖ ዝም የሚልም አለ፣ እያወቀ ጊዜ እስኪያገኝለት ድረስ የማይናገርም አለ፡፡ ያመጣለትን የሚቀባጥርም አለ፣” ይላል፡፡
እናላችሁ…አሁን ‘ቦተሊካ’ ውስጥ አይታችሁ እንደሁ ኮሚክ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ አለላችሁ አንዳንዱ በአንድ በኩል በቀን ብርሀን… “ይቺን አገር የት እንደሚያደርሷት ብቻ አይቼ…” ምናምን እያለ የ“ስምንተኛው ሺህ መጣላችሁ” አይነት ነገር ሲሰብክ ይውላል፡፡
 ሰዉ ደግሞ… “እሱ እኮ የአገር ነገር እንዴት እንደሚያንገበግበው…” ምናምን እያለ ሌሎች የሚቀኑበት አይነት ‘አድናቂ ነን’ ያዥጎደጉዱለታል፡፡ ምን ያደርጋል… አድናቆት ብቻ ፈሳሽ ሆኖ ጉሮሮ አያረጥብ፡ ምግብ ሆኖ ሆድ አይሞላ!
እናላችሁ… ማታ ደግሞ ሌላኛው ሰፈር ይሄድና… “ባቡር ብሎ ዝም! ቀለበት መንገድ ብሎ ዝም! ህንጻ ብሎ ዝም! ምናምን ብሎ ዝም!” እያለላችሁ ጉሮሮውን በ‘ወርቅ ውሀ’ ያረጥባል፣ ሆዱንም ‘በዕቃ የተጨናነቀ ቤት’ ያደርገዋል፡፡
እናማ ሁለት እግር አለን ብለን ሁለት ዛፍ ለመውጣት እየሞከርን ያለን በዝተናል፡፡ ባህሪያችን በአደባባይ በምንሠራውና በአደባባይ በምንናገረው ብቻ የሚለይበትን ተአምር አንድዬ ያውርድልንማ! (“አንዳንዴ እንደ ቄስ ነገርም ያደርግሀል መሰለኝ!” ያልከኝ ወዳጄ…ዘንድሮ ፈረንካና ‘አንዳንድ ነገሮች’ እንደልብ የሚፈሱት በምን አይነት አቀራረብ እንደሆነ አታውቅም ማለት ነው!)
የቄስነት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ታሪክ ስሙኝማ…በአንዲት ትንሽ ከተማ አንድ ቄስ ጠዋት ወደ ቤተክርስትያናቸው ሲሄዱ በሩ ላይ የሞተ አጋሰስ ያገኛሉ፡፡ ለፖሊስ ደውለውም ያሳውቃሉ፡፡ ፖሊስም… “ምንም የተፈጸመ ወንጀል ስለሌለ እኛን አይመለከተንም፣” ብሎ ወደጤና መምሪያው ይልካቸዋል፡፡
የጤና መምሪያውም “ለህዝብ የሚያሰጋ የጤና ችግር ስለሌለ እኛን አይመለከትም…” ይልና ወደ ጽዳት መምሪያ ይልካቸዋል፡፡
የጽዳት መምሪያው ደግሞ “ከንቲባው ካለዘዘ በስተቀር ሬሳውን ማንሳት አንችልም፣” ይላል፡፡
የከተማዋ ከንቲባ ደግሞ በመጥፎ ባህሪይው የታወቀ ነው፡፡ ማንንም ቢሆን መስደብና ማንጓጠጥ ይቀነዋል ይባልለታል፡፡ ቄሱ ደግሞ አማራጭ ስላልነበራቸው ወደ ከንቲባው ሄደው ጉዳዩን ይነግሩታል፡፡ ከንቲባው እንደለመደው በስድብ ይወርድባቸዋል፡፡ “ለምንድነው እኔ ዘንድ የመጣኸው!  የሞተ መቅበር ያንተ ፈንታ አይደለም?” ይላቸዋል፡፡
ቄሱም ትንሽ ጸሎት ቢጤ ካደራረሱ በኋላ ምን ቢሉት ጥሩ ነው…
“አዎ፣ ጌታዬ የእኔ ተግባር የሞተ መቅበር ነው፡፡ ግን ወደ እርሶ የመጣሁት ከመቅበሬ በፊት ለቅርብ ዘመድ ማሳወቅ አለብኝ ብዬ ነው፣” ብለውት አረፉት፡፡
ከቄስ ቅኔ ይጠብቃችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3692 times