Saturday, 03 October 2015 10:29

“ቴኳንዶ ማለት ህይወት ነው”

Written by 
Rate this item
(22 votes)

     በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ በቴኳንዶ ሙያ ኮሪያ ድረስ ሄዶ ቴኳንዶ የተማረ ብቸኛው አፍሪካዊ ኢትዮጵያዊ ብቸኛው የማስተር ማዕረግ ያለው አሰልጣኝ ነው - ማስተር አብዲ ከድር፡፡ ባለፈው ነሐሴ ወር በቡልጋሪያ ሶፊያ ዓለም አቀፉ-የቴኳንዶ ፌዴሬሽን (ITF) የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ሲያከብር ለሙያው ላበረከተው የላቀ አስተዋፅኦ የወርቅ ሽልማት ተበርክቶለታል”” የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በህይወቱና በቴኳLዶ ሙያው ዙሪያ ከማስተር አብዲ ከድር ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡

    አንድ ሰው በቴኳንዶ ምን ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው “ማስተር” የሚለውን ማዕረግ የሚያገኘው?
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ማስተር ለመባል የራሱ እርከን አለው፡፡ አንድ የቴኳንዶ ተማሪ ትምህርቱን ሲጀምር ከቢጫ ቀበቶ እስከ ጥቁር ቀበቶ ድረስ የራሱ ሂደቶች አሉት፡፡ ከጥቁር ቀበቶ በኋላ ፈርስት ዳን፣ ሰከንድ ዳን፣ ፎርዝ ዳን፣ እያለ ሲክዝ ዳን (6ኛ ዳን) ላይ ሲደርስ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር የሚል ማዕረግ ያገኛል፡፡ ሰባተኛ ዳን ላይ ሲደርስ ማስተር የሚለውን ማዕረግ ያገኛል ማለት ነው፡፡ እኔም በዚሁ ሂደት ውስጥ አልፌ ነው ማስተር የሚለውን ማዕረግ ያገኘሁት፡፡
በቴኳንዶ ሙያ ለምን ያህል ጊዜ ሰራህ?
ላለፉት 40 ዓመታት ህይወቴ ከቴኳንዶ ጋር ተቆራኝቶ ነው ያለው፡፡ አላህ ከፈቀደ ወደፊትም በሚሰጠኝ ዕድሜ በዚሁ ሙያ እቀጥላለሁ፡፡
በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ በሙያው ያደረግሃቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች እስኪ አስረዳኝ…
በዚህ አርባ ዓመት ውስጥ ራሴ ከመማር አልፌ በኢትዮጵያና በአፍሪካ እንዲሁም በሌላው የዓለም ክፍል እየተዘዋወርኩ አስተምሬአለሁ፡፡ ኮሪያ ድረስ ሄጄ በከፍተኛ ማዕረግ የተማርኩ የመጀመሪያው አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በሙያው ያሳለፍኩት ውጣ ውረድ ከፍተኛ ነው፤ በተለይም በደርግ ጊዜ ፈተናው ከባድ ነበር፡፡ ዘርፉ እንዳሁኑ በመንግስት እውቅና ተሰጥቶት በይፋ ሊሰራ ቀርቶ እኛም እየተደበቅን ነበር የምንሰራው፡፡ ያ ሁሉ አልፎ በአሁኑ ሰዓት አገራችን በአሶሴሽን ደረጃ ተቋቁሞ የዓለም አቀፉ የቴኳንዶ ፌዴሬሽን አባል ለመሆን በቅተናል፤ እስካሁን ልጆች በማስተማር ክለቦችን በማቋቋም፣ አሶሴሽኑን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ብቸኛው 7ኛ ዳን ያለኝ ነኝ፤ በዚህ በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ከ7ኛ ዳን ወይም ማስተር ከሚለው ማዕረግ በላይስ ሌላ ማዕረግ አለ? ካለስ ወደዚያ ደረጃ ለማደግ ምን አይነት እንቅስቃሴ እያደረግህ ትገኛለህ?
በጣም ጥሩ! ከ7ኛ ዳን ቀጥሎ ያለው 8ኛ ዳን ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ 7ኛ ዳን ላይ ሲደረስ “ማስተር” እንደሚባል ሁሉ፣ 8ኛ ዳን ላይ ሲደረስ “ሲኒየር ማስተር” የተሰኘ ማዕረግ ይሰጣል፡፡ እኔም አላህ ፈቃዱ ሆኖ ከደረስኩ (እንደምደርስ ተስፋ አለኝ) ከስድስት ወራት በኋላ 8ኛ ዳን በማግኘት ደረጃዬን ወደ ሲኒየር ማስተርነት አሳድጋለሁ፡፡
ወደቴኳንዶ እንዴት ነው የገባኸው?
ቴኳንዶን የጀመርኩት ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሆኜ ነው፡፡ እንዴት ጀመርክ ላልሺው ከአባቴ የወረስኩት ነው፡፡ አባቴ የቴኳንዶ ባለሙያ ነበር፡፡ እንግዲህ የአላህ ስጦታ ሆኖ እድሜዬን ሙሉ በስፖርቱ አሳልፌያለሁ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚቀጥለው ጥቅምት 1 60ኛ ዓመቴን አከብራለሁ፡፡ ከአምስት ዓመቴ ጀምሮ ከስፖርቱ ጋር ነኝ፤ እንደነገርኩሽ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራሁ እየተማርኩ፣ በዓለምና በአፍሪካ እየተዘዋወርኩ 40 ዓመታትን አሳልፌያለሁ ማለት ነው፡፡
አሁን 60 ዓመትህ ነው ማለት ነው፤ ግን የ30 ዓመት ወጣት ነው የምትመስለው…
የማልደብቅሽ ነገር ስፖርቱ በራሱ ለአሁኑ የሰውነት አቋሜ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እጅግ የማከብራት፣ የምወዳትና የማፈቅራት ሰላም የሆነች ሚስት አላህ ሰጥቶኛል፤ በኑሮዬ ደስተኛ ነኝ፡፡ ፈጣሪ፤ ሚስት የምትሰራው ከግራ ጎን ነው ይላል አይደል፤ የኔ ሚስት ግን ከሁሉም ጎኔ ነው የተሰራችው፡፡ እህቴም፣ ሚስቴም፣ እናቴም፣ አማካሪዬም… ብቻ ሁሉም ነገሬ ናት፡፡ ከእሷ የማገኘው ድጋፍ፣ እንክብካቤና ፍቅርም በራሱ ከእድሜዬ በታች ወጣት መስዬ ኧረ እንዲያውም ሆኜ እንድታይ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡
በትዳር ምን ያህል ጊዜ ቆያችሁ? ልጆችስ አፍርታችኋል?
ላለፉት 31 ዓመታት አብረን በትዳር እየኖር ነው፡፡ በእድሜ ከእኔ በጣም ታንሳለች፤ ገንዬን አሳድጌያታለሁ ማለት ይቻላል፡፡ ልጆች አልወለድንም፤ ወደተለያዩ የውጭ አገራት ሄደን ምርመራ አድርገን፣ መውለድ ትችላላችሁ ተብለናል፡፡ አንድ ቀን ልጅ እንደሚኖረን ተስፋ አለን፡፡ ሆኖም በአሁን ሰዓት የልጅ ጉዳይ በኑሯችን ውስጥ እንደ እንከን ተጠቅሶ አያውቅም፡፡ በዙሪያችን ያሉ የማስተምራቸው ልጆች ሁሉ ልጆቼ ናቸው፡፡ አንድም ቀን በዚህ ቅር ተሰኝቼ፣ በትዳሬና በፍቅሬ ላይ እንቅፋት ሆኖብኝ አያውቅም፡፡ ገኒ ለእኔ ልጄም ጭምር ናት፤ እንዴት እድለኛ እንደሆንኩ አልነግርሽም፡፡
እስኪ ቡልጋሪያ ላይ ባለፈው ነሐሴ ወር ስላገኘኸው ሽልማት ንገረኝ…
ባለፈው ኦገስት በተካሄደው የኢንተርናሽናል የቴኳንዶ ፌደሬሽን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴኳንዶ ከፍተኛ እንቅስቃሴና አስተዋፅኦ ያበረከቱ 60 ሰዎች ተሸልመው ነበር፡፡ በዚህ ሽልማት ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ብሆንም እንደምሸለምና እጩ እንደነበርኩ ግን አላውቅም ነበር፡፡ የኢትዮ ዮናይትድ ቴኳንዶ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት እንደመሆኔ፣ 60ኛ ዓመት በዓሉን ለማክበር ወደ ቡልጋሪያ ሶፊያ ከተማ ሄጄ ነበር፡፡ ሽልማቱ ሲካሄድ ግን ብቸኛው አፍሪካ ኢትዮጵያዊ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኔን ድንገት ሰማሁኝ፡፡ ይሄ እንግዲህ ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ ሽልማትና ኩራት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ሽልማት ወደ 180 ያህል የዓለም አገራት ተሳታፊ ሆነውበት፣ ከነዚህ ሁሉ አገራት ነው ብቸኛው አፍሪካ ኢትዮጵያዊ የወርቅ ተሸላሚ የሆንኩት፡፡ ፈረንጆቹ ተሳሳቱ የምለው ሽልማቱን ለሚስቴ ለገነት ሀብተማሪያም ባለመስጠታቸው ብቻ ነው፡፡
እንዴት ማለት?
እኔ በጣም ተደባዳቢ፣ አስቸጋሪ ባህሪ የነበረኝና የማልረባ ሰው ነበርኩ፤ እርሷ ናት ለዚህ ማንነት ያበቃችኝ፤ የለወጠችኝ፡፡ በዚያ ላይ እርሷ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ስትሆን እኔ ሙስሊም ነኝ፡፡ የእርሷን ፆም እፆማለሁ፤ የእኔን ፆም ትፆማለች፡፡ የመቻቻል የመፋቀር ተምሳሌቶችም ነን፡፡ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለን ነው ከ30 ዓመት በላይ የዘለቅነው፡፡ የእርሷ ድጋፍና ፍቅር ገና ለብዙ ሽልማቶች ያበቃኛል፡፡ አንድ ነገር ልንገርሽ፤ 35ኛ የጋብቻ በዓላችን ላይ እንደገና ሰርግ ደግሰን ለመጋባትና ትዳራችንን ለማደስ እቅድ ይዘናል፤ አላህ ይርዳን፡፡
ኮሪያ ሄዶ ከፍተኛ የቴኳንዶ ትምህርት በመማር የመጀመሪያው አፍሪካዊ ኢትዮጵያዊ ነህ፡፡ ከኮሪያ ውጭ የት የት ተምረሃል?
ከዚያ በኋላ ያልሄድኩበትና ኮርስ ያልወሰድኩበት የዓለም ክፍል የለም፡፡ ለምሳሌ ጀርመን፤ እንግሊዝ፣ ስውዲንና ሌሎችም አገሮች ሄጄ በዘርፉ አሉ የተባሉ ኮርሶችን በመውሰድ እውቀቴን አዳብሬያለሁ፡፡ ሌላው ህንድ አገር በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፊዚካል ኢጁኬሽን ተምሬአለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅት ቴኳንዶ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?
ዘርፉ በደርግ ጊዜ የነበረበትን ሁኔታ ነግሬሻለሁ፤ በመንግስት አካላትና በተፈቀደላቸው ወገኖች ብቻ በገደብ የሚሰጥ ትምህርት ነበር፡፡ ቴኳንዶ በአሁኑ ሰዓት ጥሩ እውቅና አለው፡፡ ከመንግስትም በኩል እገዛ ይደረጋል፤ ነገር ግን እገዛው በቂ አይደለም፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በቴኳንዶ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በማርሻል አርት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልሎችም በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ዩናይትድ ቴኳንዶ አሶሴሽን ስር ምን ያህል ተማሪዎች አሉ?
በአሶሴሽናችን ስር ብቻ 37 ሺህ ሰልጣኞች ይገኛሉ፡፡ ወደ 200 ያህል ክለቦችም እናስተዳድራለን፡፡
እስኪ ስለቴኳንዶ ሳይንስና ዲሲፕሊን በአጭሩ ንገረኝ…
በአጠቃላይ ቴኳንዶ ማለት ህይወት ነው፤ ሰዎች ስለቴኳንዶ ሲያስቡ እግርና እጅ ማወናጨፍ ብቻ ነው ብለው ካሰቡ በጣም ተሳስተዋል፡፡ ነገር ግን ሰው ከእግርና እጅ እንቅስቃሴ በፊት በመልካም ስነ ምግባርና ጥሩ ሰብዕና ጭንቅላቱ ይገነባል፡፡ ታጋሽ፣ ሰው አክባሪ፣ ማህበራዊ ኑሮ አዋቂ፣ በጎ አድራጊ… በአጠቃላይ የጥሩ ስብዕና ባለቤት እንዲሆን ተደርጎ ይቀረፃል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ወደ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚገባው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የስብዕና መሰረቶች ውጭ ሆኖ የቴኳንዶ ባለሙያ ነኝ የሚል ካለ፣ ጨርሶ የቴኳንዶን ሳይንስም ሆነ ዲሲፕሊን አያውቀውም ማለት ነው፡፡ ቴኳንዶ ማለት እጅ እግርና አዕምሮ የተቀናጁበት ጥበብ ማለት ነው፡፡ ቴኳንዶ፡- ሰላም፣ ፍቅር አንድነት ነው፡፡ እነዚህ ናቸው በቴኳንዶ ውስጥ ያሉት መሰረታዊ ነገሮች፡፡
በአገራችን በተለይም በመዲናችን በተለያዩ ቦታዎች በርካታ የቴኳንዶ ማሰልጠኛዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ማሰልጠኛዎች ቃኝተሃቸው ታውቃለህ? ማሰልጠኛዎቹ ምን ያህል ትክክለኛውን የቴኳንዶ ስልጠና እየሰጡ ነው ትላለህ?
 የቴኳንዶ ትምህርት የሚያልቅ አይደለም፡፡ በሂደቱ ውስጥ ብዙ ስህተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሂደትም ይስተካከላሉ፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ዋነኛ ዓላማቸው መልካም ዜጋን ማፍራት ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ከሞላ ጎደል ትምህርቱን እየሰጡ ይገኛሉ፤ በዚያው መጠን ግን ችግር ያለባቸው የሉም ማለት አይቻልም፡፡ ግን በሂደት ሊቀረፉ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ አሁን በየቦታው ለዘርፉ ፈቃድ እየተሰጠ ነው፤ በዚያው መጠን ያሉባቸውን ችግሮች እንዲቀርፉ ማስጠንቀቂያዎችም ይሰጣሉ፡፡
ቴኳንዶ በጥበብና በዲሲፕሊን ካልተሰራ፣ ጋንግስተሮችን የምናፈራበትና ፈቃድ የሌለው መሳሪያ የምናስታጥቅበት ይሆናል፡፡ ቴኳንዶ ደግሞ ጋንግስተሮችን የምናፈራበት ሳይሆን ጋንግስተሮችን የምናጠፋበት ነው መሆን ያለበት፡
ቴኳንዶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ደረጃ ስለሚሰጥበት ሁኔታ የታሰበ ነገር አለ?
ትምህርቱ በመንግስት በኩል በመምህራን ኮሌጅ ደረጃ እየተሰጠ ነው፡፡
 ዩኒቨርሲቲ ውስጥም እንደ አርት ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ ወደፊት ራሱን የቻለ ዩኒቨርሲቲ እንዲኖረው ከውጭዎቹ ጋር በመነጋገር ላይ ነን፡፡ ይህ የሚሳካ ይመስለኛል፡፡
በርከት ያሉ የቴኳንዶ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዳሉህ ሰምቻለሁ፡፡ ምን ያህል ናቸው? የት የት ነው የሚገኙት?
በርካታ ተቋማት አሉኝ፡፡ ለምሳሌ አፍሪካ ህብረት ውስጥ፣ ኢሲኤ፣ ጁቬንቱስ ጣሊያን ክለብ ውስጥ፣ ሳር ቤት አዳምስ ፓቪሊዮን ህንፃ እንዲሁም፣ ፍፁም በላይ ሆቴል ውስጥ የማሰልጠኛ ተቋማት አሉኝ፡፡
በኢትዮ ዮናይትድ ቴኳንዶ አሶሴሽን ስር ደግሞ እንደ ፕሬዚደንትነቴ በስሬ ወደ 200 ያህል ክለቦች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን እኔ ነኝ የምመራቸው፡፡
እነዚህ ክለቦች ተምረው ከፍተኛ ደረጃ ሲደርሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ቀበቶዎች (ዳኖች) ፈርሜ ከውጭ የማስመጣቸው እኔ ነኝ፡፡ ዳኖቹ የሚመጡት ከዋና ጽ/ቤታችን ከኦስትሪያ ቪዬና ነው፡፡
እስኪ ማርሻል አርት በሚባሉት እነካራቴ ጁዶ፣ ውሹ ቴኳንዶና ሌሎችም ስፖርቶች መካከል ስላለው አንድነትና ልዩነት በአጭሩ ንገረኝ?
ማርሻል አርቶች በኢንተርናሽናልና በወርልድ ቴኳንዶዎች የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ የሚገርመው የነዚህ ማርሻል አርቶች ልዩነት የእንቅስቃሴ ልዩነት ነው፡፡ ውሹ የቻይና ስፖርት ሲሆን በብዛት በአክሮባትና ሰውነትን እንደልብ በማዘዝ (Flexibility) ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በብዛት ታይገር ስታይል፣ ስኔክ ስታይል በማለት በእንስሳት እንቅስቃሴ ይከፋፍሏቸዋል፡፡ ካራቴ የምንለው የጃፓንና የፈረንሳይ ስፖርት ነው፡፡ ጃፓኖች እንቅስቃሴውን ልዩ አድርገው ስለቀመሩት ከቴኳንዶ ትንሽ ይለያል፡፡ ጁዶ ደግሞ በመያዝና በመጣል እንደ ትግል አይነት ስፖርት ሲሆን ብዙ ጊዜ ወታደሮች የሚያዘወትሩት ነው፡፡
በመጨረሻ የምታክለው ይኖርሃል?
የሚገርመውና ልጨምርልሽ የምፈልገው እስከዛሬ በኦሎምፒክ ውስጥ ወርልድ ቴኳንዶ ነበር ለውድድር የሚቀርበው፡፡
አሁን ግን በ2016 ሪዮ ዲጄነሪዮ በሚካሄደው 31ኛው ኦሎምፒክ ላይ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ከወርልድ ቴኳንዶ ጋር በጋራ ለውድድር ይቀርባል፡
በዚህም ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ወክለው የሚቀርቡ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ትልቅ የምስራች ነውና እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን፡፡

Read 12037 times