Saturday, 10 October 2015 16:05

የ“ቤንዚኑን ማን ይሙላው!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(29 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሷዬዋ እጮኛዋን ቤት አምጥታ ከወላጆቿ ጋር ታስተዋውቅዋለች፡፡ ወላጆቿ ደግሞ ‘ፏ’ ያሉ ሀብታሞች ነበሩ፡፡ አባትየው የልጁን እጮኛ ወደ ባዶ ክፍል ወስዶ ያዋራዋል፡፡ “ለመሆኑ ዕቅድህ ምንድነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “እኔ የኃይማኖቶች ምሁር ነኝ፡ ጥናቶች አጠናለሁ…”ይላል፡፡ አባትየውም… “ግሩም ነው፣ ግን ልጄ ጥሩ መኖሪያ ቤት እንዲኖራት ምን አስበሀል?” ይለዋል፡፡
እጮኛ ሆዬም… “እኔ ምርምሬን አካሂዳለሁ፣ በተረፈ እግዚአብሔር ያሟላልናል፣” ይላል፡፡
አባትም “ለልጄ ቆንጆ የጋብቻ ቀለበት በምን መልክ ልትገዛላት ነው ያሰብከው?” ብሎ ይጠይቃል፡
እጮኛ ሆዬም… “እኔ ምርምሬን አካሂዳለሁ፣ በተረፈ እግዚአብሔር ያሟላልናል፣” ይላል፡፡
ውይይቱ በዚህ መልክ ይቀጥልና እጮኝዬው ለሁሉም ጥያቄ… “እኔ ምርምሬን አካሂዳለሁ፣ በተረፈ እግዚአብሔር ያሟላልናል፣” ይላል፡፡
ልጅቷ አባቷን… “ለመሆኑ ውይይታችሁ እንዴት ነበር?” ብላ ትጠይቀዋለች፡፡ አባት ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ሥራም የለው፣ ዕቅዶችም የሉትም፡፡ ጥሩው ዜና ምን መሰለሽ…እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩ ያስባል፡፡”
አማቾቻቸውን “እግዚአብሔር ናቸው” ብለው የሚያስቡ መአት ይኖራሉ፡፡ ልክ ነዋ… “ለቤተሰቦቿ ሀብት ሲል ነው ያገባት…” “ለሀብት ስትል ነው ያገባችው…” ማለት የበዛው ለዚህ መሆን አለበት፡፡
ስሙኝማ…የምር ግን የሆነ የተበላሸ ነገር አለ፡፡ የጥቅም ግንኙነት እየበዛ ነው ይባላል፡፡ ገና አንደኛ ዓመታቸውን ሳያከብሩ የሚለያዩ ጥንዶች መብዛታቸው የሆነ የተበላሸ ነገር እንዳለ ያሳያል፡፡
ባልና ሚስቱ 45 ዓመታት በትዳር ኖረዋል፡፡ 11 ልጆችና 22 የልጅ ልጆች አላቸው፡፡ እና አንዱ ምን ብሎ ይጠይቃቸዋል…
“ለመሆኑ ሰዉ ሁሉ በየጊዜው ሲፋታ እናንተ ይህን ሁሉ ዘመን አብራችሁ የቆያችሁበት ምስጢር ምንድነው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
ሚስትየዋ ምን ብላ ብትመልስ ጥሩ ነው… “የተጋባን ጊዜ ‘ትዳር በቃኝ’ ብሎ መጀመሪያ ከዚህ ቤት የሚወጣ ሰው ልጆቹን ሁሉ ይዞ ይሄዳል…” በሚል ተስማምተን ነበር፡፡ አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ… ማን ሙሉ የእግር ኳስ ቡድን አስከትሎ ይወጣል!
እናማ… ልጆች በርከት ካሉ ‘ቀድሞ የወጣ ይዞ ይወጣል’ ምናምን ከተባለ ትዳር ተረፈ ማለት አይደል!
እኔ የምለው…የመኪናና የቤት ጥሎሽ በዛሳ! የምር…እኛ እኮ እነኚህ ሁሉ እንትናዬዎች ቪትዙንና ያሪሱን ሲያሽከረከሩ ስናይ መገረም ትተናል፡፡ አሀ…በቃ እንጠረጥራለና!
አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን ስሙኝማ…እሱዬው ዳያስፖራ ነው፡፡ (እኔ የምለው…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ “የተያዘልን ሆቴል አልጋና ምግብ አልተስማማንም…” ምናምን ነገር ብላችሁ ‘ያስደነገጣችሁን’ ዳያስፖራዎች…የሆነ ‘የአልጋና ምግብ ሪቮሉሽን’ አስባችሁ ነበር እንዴ! አሀ…በሌለን ፈረንካ ‘ክው’ አደረጋችሁና! እኛ ድግስ አማረልን ብለን ‘ገጽታችን’ ላይ ጥቁር ነጥብ ምናምን ልትጥሉ ነበራ!)
እናላችሁ…ዳያስፖራው ሆዬ ለእሷዬዋ ያቺ የፈረደባትን ቪትዝ የሚሏትን መኪና ይገዛላታል፡፡ ለትንሽ ቀናት ቪትዝ ሆዬ ብታንስም ጠጅ ስለሆነች የሚታሰቡና በእሷ ስፋት’ የማይታሰቡ አገልግሎቶች’ ትሰጣለች፡፡ ታዲያላችሁ… ከተወሰኑ ቀናት በኋላ እሱዬው ‘ለባለቪትዟ’ ደጋግሞ ቢደውልላት፣ የጽሁፍ መልእክት ቢልክላት አትመልስም፡፡ በኋላ ግራ ሲገባው ሰተት ብሎ ቤቷ ይሄዳል አሉ፡፡
ታዲያላችሁ…ቤቷ እንደ ደረሰ በሩ ገርበብ ስላለ ሳያንኳኳ ድንገት ዘው ብሎ መግባት፡፡ ዳያስፖራ ሆዬ ባየው ለ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ መሟሟቂያ ትርኢት ክው ይልላችኋል፡፡ ለካስ… አለ አይደል… በአውሮፕላን የመጣ ዳያስፖራ ይሁን፡ ‘አገር በቀል’ ዳያስፖራ ይሁን ያልታወቀ ሌላ ጎረምሳ ከእሷዬዋ ጋር የታይታኒክ አይነት ‘ኪሶሎጂ’ ያጦፋሉ፡፡’ (እኔ የምለው አንዳንዶቹ ‘ኪሶሎጂ’ ሲያጦፉ እጆቻቸው ማርሽ ፍለጋ ይመስል ምንድነው ቁም ምልክትን እየጣሱ የሚሄዱት! ልጄ ዘንድሮ አንደኛ፣ አምስተኛ ቅብጥርስዮ ማርሽ ምናምን በአውቶማቲክ እንደተተካ አላወቁ  ቂ…ቂ…ቂ…)ዳያስፖራ ሆዬ ‘አቧራው ቡን’ ይልና (‘የፈረንጅ አቧሯ’ ለማለት ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ተመልሶ ሊወጣ ሲል እሷዬዋ…
“ግባ እንጂ የት ትሄዳለህ?” ትለዋለች፡፡
እሱም ምንተእፍረቱን መለስ ይልና… “አይ እቸኩላለሁ፣” ይልና ዝም ብሎ መሄዱ አላስችል ብሎት “አንዴ ውጪ ላናግርሽ…” ይላታል፡፡
እሷዬዋም…“ኧረ ችግር የለውም፣ እዚሁ አናግረኝ፣” ትለዋለች፡፡
እናላችሁ… “እወድሃለሁ ስትዪኝ አልነበር…” ይላታል፡፡
“አሁንም እወድሀለሁ፣” ትለዋለች፡፡  
“ታዲያ ከወደደሽኝ መኪና ገዝቼልሽ እንዴት ከሌላ ሰው ጋር እንዲህ አይነት ነገር ታደርጊያለሽ?” ይላታል፡፡
እሷዬዋ ምን ብትል ጥሩ ነው… “ታዲያ አንተ መኪናውን ብትገዛ ቤንዚኑን ማን ይሙላው!”
አሪፍ አይደል! እሷዬዋ ልክ ነቻ…አሀ፣ ሥጋ ሰጥቶ ቢላ መንሳት አለ እንዴ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ… ቪትዝም ሆነ ሌላ መኪና ለእንትናዬዎቻችሁ የምትገዙ እንትናዎች የቤንዚኑንም አብራችሁ አስቡበት፡፡ አለበለዛ የ‘ኤስኮርት ጎማ’ አይነት አገልግሎት የሚሰጥ እንትና በ‘ጋራ ተጠቃሚነት መርህ’ የመብት ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ ልጄ… ዘመኑ የ“ቤንዚኑን ማን ይሙላው!” ሆኗል፡፡
ስሙኝማ…ዘንድሮ ወላጆች ራሳቸው የሚዳሩ ልጆቻቸውን ‘ገንዘብ ላይ እንዲወድቁ’ ይፈልጋሉ፡፡ እናማ…ድሮም አማቶች ስንት ይወራባቸዋል፤ ዘንድሮ ደግሞ የባሰበት ይመስላል፡፡ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…በትንሽ ትልቁ “ዓይንሽ ለአፈር” “ዓይንህ ለአፈር” መባባል የበዛው… አለ አይደል…
“እንደምንም ብለሽ ችግርም ቢኖር ትዳርሽን አጥብቀሽ ያዢ…”
“እንኳን ባልና ሚስት፣ እግርና እግርም ይጋጫል…” ምናምን አይነት ምክሮች ስለቀነሱ ይመስለኛል፡፡ ይልቁኑም…
“ወንድ ሞልቶ በተረፈበት፣ ጥለሽው ውጪያ!…”
“አንተ ከእሷ ጋር ቆርበሀል እንዴ!” ምናምን አይነት ‘ምክሮች’ የበዙ ይመስለኛል፡፡
የአማቶች ነገር ካነሳን አይቀር… ይቺን ስሙኝማ…ሁለት ሴቶች ንጉሥ ሰለሞን ፊት ይቀርባሉ፡፡ መሀላቸው አንድ ወጣት ነበር፡፡ አንደኛዋ…
“ይህ ሰውዬ ሴት ልጄን ሊያገባ ተስማምቷል…” ትላለች፡፡
ሁለተኛዋም “ውሸቷን ነው፡፡ የእኔን ልጅ ሊያገባ ነው የተስማማው፣” ትላለች፡፡
ንጉሡም አንድ ጊዜ ጸጥታ እንዲሆን አዘዘ፡፡ ለሎሌዎቹም እንዲህ አላቸው፡፡
 “ትልቁን ጎራዴዬን አምጡልኝ፡፡ ወጣቱን ሁለት ቦታ እቆርጠውና አካፍላችኋለሁ፣” አላቸው፡
አንደኛዋ ሴትዮ “እስማማለሁ፣  ይቆረጥና እንካፈለው…” አለች፡፡
ሁለተኛዋ ግን “ጌታዬ የንጹህ ደም አይፍሰስ፡፡ ወጣቱ የእሷን ልጅ እንዲያገባ እስማማለሁ…” ትላለች፡፡
ንጉሥ ሰለሞንም ምንም ሳያመነታ… “ይህ ሰው የመጀመሪያዋን ሴት ልጅ ማግባት አለበት፣” አለ፡፡ ከረዳቶቹም አንዱ… “ንጉሥ ሆይ ይቺ እኮ ‘ለሁለት ይቆረጥና እንካፈለው’ ያለችው ነች!” ሲለው ንጉሥ ሰለሞን ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እኮ፣ እውነተኛ አማት መሆኗን አስመስክራለች…” አለውና አረፈው፡፡
የሁለት ጓደኛሞች ወግ…
“ትናንትና አማቴን ውሻ ነከሳት፡፡”
“አሁን በምን ሁኔታ ላይ ላይ ይገኛሉ?”
“እሷ ደህና ነች፡ ውሻው ግን ሞቷል፡፡”
አንድ የአማቶች ወሬ እንጨምርማ…ሰውየው ጓደኛውን “ዛሬ ሠፈራችን ብርዱ አጥንት ይሰረስር ነበር፣” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም…
“ምን ያህል ቢቀዘቅዝ ነው እንዲህ ያማረረህ” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም “አማትህ ጉንጭህ ላይ ስማህ ታውቃለች?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
“አዎ፣” ሲል ይመልስለታል፡፡ ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው፣
“ያን ያህል ይቀዘቅዝ ነበር፡፡”
አሪፍ አይደል!
እናላችሁ…በተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር… “ቤንዚኑን ማን ይሙላው!” አይነት አስተሳሰብን በሩቁ ያድርግልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4982 times