Saturday, 10 October 2015 16:17

አሳሳቢው የዕይታ ችግር- በአገራችን!

Written by 
Rate this item
(6 votes)
  •   በአገሪቱ የሚገኙ የአይን ሐኪሞች 130 ብቻ ናቸው
  •       2.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እይታቸው የደከመ ነው
  •      በደቡብ ክልል ብቻ አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ አይነስውር የሚሆኑ 170ሺ ሰዎች አሉ

    የአለም የጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት፤ አንድ ሰው በሁለቱም አይኑ ከሶስት ሜትር ርቀት ላይ ጣት መቁጠር ካልቻለ አይነስውር ይባላል፡፡ አይነስውርነትን የሚያስከትሉ በርካታ አይነት በሽታዎችና ድንገተኛ አደጋዎች እጅግ በርካታ ሰዎችን ለአይነስውርነት እየዳረጉ ነው፡፡ እነዚህ የአይን እይታ አቅምን ችግር ላይ የሚጥሉ በሽታዎች የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የመከሰቻ ምክንያታቸውም የተለያየ ነው፡፡
አይነስውርነትን ከሚያስከትሉና የአይን የጤና ችግር በመሆን በስፋት ከማታወቁ በሽታዎች መካከል Cataract (የዓይን ሞራ ግርዶሽ) Trachomatous Corneal Opacity (ትራኮማ)፣ Retractive errors (የቅርብ ወይም የእርቀት የማየት ችግር) እና Glacoma (ግላኮማ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የዓለም የእይታ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለአስረኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ በአገር አቀፍ ደረጃ በአርባምንጭ ከተማ ተከብሯል፡፡ ይህንኑ የዓለም የእይታ ቀን አስመልክቶ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ለጋዜጠኞች የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ አገሪቱ በተለያዩ የዓይን በሽታዎች ሳቢያ በሚከሰቱ የዓይነ ስውርነት ችግሮች ምን የህል ጉዳት እንደደረሰባት የሚያሳይ በ2006 ዓ.ም የተደረገ ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡
በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር የኔነህ ሙሉጌታ የቀረበውና አገሪቱ በአይን ጤና ችግሮች፣ በመንስኤዎቻቸውና ችግሮቹ ያስከተሉአቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 1,200,456 አይነስውራን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ሙሉ በሙሉ የማየት ችሎታቸውን ካጡት ሰዎች በተጨማሪ 2,776,054 የሚሆኑት እይታቸው የቀነሰ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ሙሉ በሙሉ የማየት ችሎታቸውን በማጣት አይነስውር ከሆኑት ሰዎች መካከል 1,049,198 የሚሆኑት በቀላሉ ሊወገድ በሚችል ችግር ሳቢያ ለአይነስውርነት የተዳረጉ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙት አይነስውራን መካከል ግማሽ ያህሉ በአይን ሞራ ግርዶሽ (Cataract) ሳቢያ አይነስውር የሆኑ ሲሆን 9,034,93 የሚሆኑት ደግሞ የትራኮማ ተጠቂዎች መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በገጠራማው የአገሪቱ አካባቢ በስፋት የሚታየው የአይን ሞራ ግርዶሽ በሽታ፣ በአብዛኛው በአዋቂዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን አልፎ አልፎ በህፃናት ላይም እንደሚከሰትና ከቀዶ ጥገና ውጭ በሽታውን ለማዳን የሚያስችል ህክምናም የሌለው እንደሆነ ዶክተር የኔነህ ተናግረዋል፡፡
የአይን ሞራ ግርዶሽ በወቅቱ ህክምና ካላገኘ እይታን ከመቀነስ ጨርሶውኑ እስከማጥፋት የሚደርስ አደጋ የሚያስከትል በሽታ ነው ያሉት ዶክተር የኔነህ፤ ህክምናው በአገራችንም በስፋት እየተሰጠ መሆኑንና እጅግ በርካታ ሰዎችም ይህንኑ ህክምና ለማግኘት እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ህክምናውን ከሚጠባበቁ 2 ሚሊዮን ሰዎች ኦፕሬሽን የተደረጉት 50ሺ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ የቀዶ ጥገና ህክምናው ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ሊያድን የሚችል ህክምና እንደሆነም ዶክተሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በካታራክት (በአይን ሞራ ግርዶሽ) ሳቢያ 39 ሚሊዮን የሚሆኑ የአለማችን ሰዎች ለአይነ ስውርነት የተዳረጉ መሆናቸውን ይኸው ጥናት አመልክቷል፡፡
በአገራችን ለሚከሰተው የአይነስውርነት ችግር በሁለተኛ ደረጃ መንስኤነት የሚቆጠረው የትራኮማ በሽታም በአገሪቱ በስፋት የሚታይ ችግር መሆኑን ያመለከተው የ2006 ጥናቱ፤ በአገሪቱ ከ9 ሚሊዮን በላይ የትራኮማ ህሙማን የሚገኙ ሲሆን ከ800ሺ በላይ የሚሆኑት በትራኮማ ተይዘው አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ብቻ በትራኮማ የተያዙና አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ አይነስውር የሚሆኑ 170ሺ ሰዎች እንደሚገኙ አመላክቷል፡፡ በአለም ከሚገኙት የትራኮማ ህሙማን መካከል 1/8ኛው የሚሆኑት በአገራችን እንደሚገኙና በሽታው ከድህነት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልና በንፅህና ጉድለት ሳቢያ የሚመጣ በሽታ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ከትራኮማ በመቀጠል በአገሪቱ ለሚከሰተው የአይነስውርነት ችግር በሶስተኛ መንስኤነት የሚጠቀሰው ደግሞ የቅርብ ወይም የእርቀት እይታ ችግር ሲሆን ይህም በቀላሉ ሊታከሙት የሚችልና ሙሉ በሙሉ የዓይን የጤና ችግር ቢሆንም እጅግ በርካታ ሰዎች ለአይነስውርነት በመዳረግ ላይ የሚገኝ የጤና ችግር መሆኑን ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ጥናቱ በዝርዝር እንዳስቀመጠው፤ በአገሪቱ ከሚገኙት አይነስውራን መካከል 50% የሚሆኑት በአይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ለአይነስውርነት የተዳረጉ ሲሆን 11.5% የሚሆኑት ደግሞ ከትራኮማ ጋር ተያይዞ በሚመጣ የአይን ጠባሳ ምክንያት የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ናቸው፡፡ 7.8% የሚደርሱት የቅርበት ወይም የእርቀት መነፅር የሚያስፈልጋቸው ሆነው ይህንን በተለያዩ ምክንያቶች ሳያደርጉ በመቅረታቸው ሳቢያ አይናቸው የሰነፈባቸውና ለአይነስውርነት የተዳረጉ ናቸው፡፡ ግላኮማ በተባለው የአይን በሽታ ሳቢያ አይነስውር የሆኑ 5.2% ሲሆኑ በሌላ የተለያዩ ምክንያቶች የአይን ብርሃናቸውን ያጡ 13% የሚደርሱ እንደሆኑም ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡የችግሩን ስፋት በዝርዝር ያሳየው ይኸው ጥናት በአገሪቱ ያለው የባለሙያዎች እጥረት ለበሽታው መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁሞ በአሁኑ ወቅት በአሪቱ ያሉት የአይን ሃኪሞች ቁጥር 130 ብቻ እንደሆነና ይህም 2400 የዓይን ሐኪሞች ካሏት ግብፅ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ገልጿል፡፡  

Read 8871 times