Saturday, 10 October 2015 16:38

የሩዋንዳ ፍ/ ቤት ህገመንግስት ተሻሽሎ ካጋሜ በምርጫ እንዲሳተፉ ወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    - ተቃዋሚዎች ህጉ እንዳይሻሻል ዘመቻ እናደርጋለን ብለዋል
   የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ህጉ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ለ3ኛ ዙር የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው  ውዝግብ መፍጠሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ፓርላማ ህገ መንግስቱ ተሻሽሎ ካጋሜ በምርጫ ይወዳደሩ በሚል ያቀረበውን ሃሳብ፣ የሩዋንዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዳጸደቀው ኒውዮርክ ታይምስ ዘገበ፡፡
ፍርድ ቤቱ ዲሞክራቲክ ግሪን ፓርቲ የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ፕሬዚዳንት ካጋሜን በስልጣን ላይ ለማቆየት ሲባል በህገ መንግስቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንዳይደረግ ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ፣ በህገ መንግስቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ መወሰኑን ዘገባው ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፓርላማ አባላት ባለፈው ሃምሌ ህገ መንግስቱ እንዲሻሻልና ጉዳዩ በህዝበ ውሳኔ እልባት እንዲያገኝ መስማማታቸውን  የዘገበው አይቢ ታይምስ በበኩሉ፣ ድምጻቸውን ከሰጡ ሩዋንዳውያን መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ወይም 3.7 ሚሊዮን ያህሉ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት የስልጣን ዘመን የሚገድበው የህገ መንግስቱ አንቀጽ እንዲሻሻል ድጋፍ መስጠታቸውን ገልጧል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን በርካታ ሩዋንዳውያን ህገመንግስቱ ይሻሻል የሚል ድምጽ የሰጡት በመንግስት ሃይሎች ተገደው ነው ሲሉ ውሳኔውን የነቀፉ ሲሆን፣ የተቃዋሚው ዲሞክራቲክ ግሪን ፓርቲ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ሃቢኔዛ በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤቱን ይግባኝ እንደሚጠይቁ ጠቁመው፣ በህገ መንግስቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ እንዳይደረግና ካጋሜ ዳግም በምርጫ እንዳይወዳደሩ ለመገደብ ዘመቻ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡

Read 1535 times