Saturday, 10 October 2015 16:39

አትሌቲክስ ከፆታ፤ አለባበስ ፤ቁመትና ክብደት አንጻር

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የእርሻና ግብርና ጥምር ተመራማሪው አቶ ደቻሳ ጅሩ ከሳምንት በፊት በቀረበው ቃለምልልስ በአትሌቲክስ የቡድን ስራን ከወፎች በረራ መማር እንደሚቻል በምሳሌነት አንስተው ያደረጉትን ምርምር አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም የአየር ሁኔታና የቦታ ተስማማሚነት በተመለከተ አጭር ገለፃም ነበራቸው፡፡  በዓለም አቀፍ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች በሚኖራቸው  ውጤታማነት የአየር ሁኔታን በሳይንሳዊ መረጃዎች አገናዝቦ ስልጠና እና ዝግጅት ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ደቻሳ ጅሩ ከስፖርት አድማስ ያደረጉት ሰፊ ቃለምምልስ እነሆ በ3ኛ ክፍል ይቀጥላል፡፡ አትሌቲክስ ከፆታ፤ አለባበስ፣ ቀለማት፤ ቁመትና ክብደት አንፃር ምርምሮቻቸውን በመጠቃቀስ ያስረዳሉ፡፡
ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ ቡድን ወንድ አትሌቶች ብዙም ስኬታማ አልነበሩም ማለት ይቻላል፡፡ ሴቶቹ ግን  የተሻሻለ ውጤት እያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ልዩነቱ ከምን እንደመጣ ብዙ ግልፅ አይደለም፡፡ ለመሆኑ አትሌቲክስ  ከፆታ እና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች አንፃር እንዴት ይመለከቱታል?
በአትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማነት የሚገኘው የፆታ ሁኔታዎችን በሳይንሳዊ ምርምሮች አገናዝቦ በሚሠራ መዋቅር ነው፡፡ የፆታ ልዩነት በስልጠና እና በማንኛውም የውድድር ዝግጅቶች የሚኖረው ተፅእኖ  በትኩረት የምንሰራበት አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡  ወንድ ቅዝቃዜ ይስማማዋል፤ ሴት በሙቀት ውጤታማ ትሆናለች፡፡ ለምን? የስነተፈጥሮ ጉዳይ ነው፡፡ ቀነኒሳና ጥሩነሸ በ3000 ሜትር ከፍታ አድገዋል፡፡ ተመሳሳይ ውሃና አየር ጠጥተው እና ተንፍሰው ወደ አለም አትሌቲክስ የውጤት  ማማ ወጥተዋል፡፡  በ2007 እ.ኤ.አ በኬንያዋ የባህር ጠረፍ ከተማ ሞምባሳ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና መደረጉን ታስታውሳለህ፡፡ በዚያ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በነበረው ተሳትፎና ያልተጠበቀ ውጤት በምሳሌነት ላነሳልህ ነው፡፡ በሴቶች ምድብ በረጅም ርቀት ጥሩነሽ ዲባባ 2ኛ መሆኗ ትልቁ ውጤት ነበር፡፡ ሌሎች ሴት አትሌቶች  ደግሞ 3ኛና 4ኛ ደረጃዎችን አሳክተዋል፡፡ በአንፃሩ በወንዶቹ ምድብ ግን አትሌቶቻችን እስከነጭራሹ እንዳልነበሩ ሆነዋል፡፡ ወንዶቹ ያልተሳካላቸው በብቃት ማነስ አልነበረም፡፡ የፆታ ልዩነት የፈጠረው እድል ነው፡፡ ከተፈጥሮ አኳያ የአየር ምቾት በፆታዎች መካከል ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ለወንድ ቅዝቃዜ ስለሚስማማው ለሴት ሙቀት ፋይዳ ስለሚሆን ነው፡፡ በሌላ በኩል ሞምባሳ ላይ የኤርትራው ዘረሰናይ በወንዶች 1ኛ መውጣቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ዘረሰናይ ከሞምባሳ ጋር ተመሳሳይ በሆነ የአየር ሁኔታ  ባላት የምጽዋ ከተማ ዝግጅቱን በመስራቱ የተሻለ ብቃት ፈጥሮለታል፡፡ የምፅዋ አየር ከሞምባሳው ጋር መወራረሱ እና ጠንካራ ከሚባሉት አትሌቶች አንዱ ስለበር ብልጫ አሳይቶ አሸንፏል፡፡
የወንድና ሴት መሰረታዊ ልዩነቱ ከስነተዋልዶ አካል አፈጣጠር ይጀምራል፡፡ የወንድ ዘር መራቢያ 37.6 ድ.ሴ. ከሚሞቅ ሰውነት ወጣ ያደረገውና የሽፋን ቆዳውን ‹‹እንደ ቮልስ ራዲያቶር››  ቆዳውን የሸበበው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በውስን ዘር ፍሬ ቦታ ላይ የንፋስ(ማቀዝቀዣ) ቦታውን አብዝቶ) አስፍቶ በንፋስ እንዲቀዘቅዝ ነው፡፡ ስለዚህ ወንድ በተፈጥሮ እንደደጋ በግ ሙቀት አይችልም፡ በተቃራኒ ልክ እንደጾታዋ የሴትዋ እንቁላል በሙቀት ውስጥ/ሰውነትዋ ውስጥ/ ስለሆነ ሙቀት(እንፋሎትም) ትችላለች፡፡ ንፋስና ብርድ ግን አትችልም፡፡
ሁኔታውን በደንብ ለመረዳት እንዲያስችል ከምርምሮችዎ ሌላ የሚጠቅሱት የለም…?
አንድ ገጠመኝ ነበረኝ፡፡  የግብርና ምርምር ኢንስትቲውት በየዓመቱ የአለም ሴቶች ቀን ሲከበር ይጋብዘኛል፡፡  አንዲት ታጋይ የነበረች ኮለኔል ለታይ የምትባል ሴት የትግል ተመክሮዋን በመድረክ ስትገልፅ ታዳሚ ነበርኩ፡፡ ጥያቄዎች የማንሳት እድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ ከበረሃ እስከጉና ተራራ ባለው የትግል ወቅት ከወንድና ከሴት ማን በብርድ ተሰቃየ፤ በሙቀትስ? የሚል፡፡ ታጋይዋ በሚሰጡኝ ምላሽ  አትሌቲክስን በተመለከተ ላደረግኩት ሳይንሳዊ ጥናት አንድ  ተጨባጭ ፋይዳ ስለሚኖረው በደንብ ይታሰብበት አልኩ፡፡ ኮለኔል ለታይ ማብራርያቸውን ሲቀጥሉ ታጋዮች ባንድ ወቅት ወደ አሰብ መደራሻ የሚገኝ አካባቢ ላይ በደርግ ሰራዊት ተከበው ከውሃ ተቁዋርጠው በጥም እንዲሰው ተደረገ፡፡ መጨረሻ አንድ ወሳኝ ወንድ ታጋይ ሊሰዋ ሲል ጉሮሮውን አርሶ ትንሽ እድሜውን ለሰአታት ለማስረዘም ሽንት ቢፈለግ ጠፋ፡፡ መጨረሻ ከአንድ ሴት ተገኝቶ ወሳኝ ታጋያቸው ነፍስ ሲዘራ የታገዩ ሞራል ነፍስ ዘርቶ መልሰው ውሃውን ተቆጣጠርን በማለት አስገራሚውን የትግል ታሪክ አወጉ፡፡ እጅግ በመደነቅ አዳመጥኳቸው፡፡ ለሳይንሳዊ ግንዛቤ የሚረዳ ገጠመኝ ነበር፡፡ ኮለኔል ለታይንና ታሪኩን በምንጭነት ጠቅሸ ወደፊት በሚታተመው የአትሌትክስ መፅሃፌ በዝርዝር የማብራራው ይሆናል፡፡
የአየር ተስማሚነት ከአለባበስ እና ቀለማትም ጋር ይያዛል?
አለባበስ እና ቀለማት ከሚያመቻቸው ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች አንፃር በአጭሩ ላስረዳህ እችላለሁ፡፡ የሽፋን ቀለም እንደአየሩ ሁኔታ መለዋወጥ ተገቢ ነው፡፡ በቁርና ደጋ የምትኖር ንብ መልኳ ጥቁር ነው፡፡ ጥቁር ቀለም ሙቀት ሰብሳቢ ነውና፡፡ ወደ ወይና ደጋ ስንወርድ የንቧ ቀለም በከፊል እየፈጋ፤  ሞቃት ወይም በረሃ ሲሆን ነጭ እየሆነ ይመጣል፡፡ ለፍየሉም ለበጉ እንዲሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከዚህ በመነሳት  ጥቁር ሰዎች ለምን አልነጣንም ብለው ቢጠይቁ ምላሽ የሚሆነው ሰዎች በተፈጥሯችን ተንቀሳቃሽ በመሆናችን ነው፡፡ እንደአየሩ ሁኔታ እንደእስስት መለዋወጥ የልብንም ነው፡፡  ብርዱንም መቀቱንም አስቀድመን በምናስብበት የመከላከል ግንዛቤ ስለምንኖር ነው፡፡ በተለይ ልብስ ስለምንለብስና ስለምንቀያይር እንደ አየሩ ሁኔታ ቀለሙንና የልብሱን ይዘት መወሰን እንችላለን፡፡ ጥቁሩን ጸጉር ሴቶች ከወንዶች በላይ አሳድገው ማጅራታቸው ላይ ማስተኛት ሌላው የመረመርኩት ሁኔታ ነው፡፡ በልምድና በሳይንሳዊ እውቀትም ብንለካው ለኔ የጠለቀና የዘለቀ ሳይንሳዊ ግንዛቤ ነው፡፡ የባህር ሃይል ዩኒፎርም ልብስ መንጣትም እንዲሁ፡፡ በእኔ በኩል  የእርሻ፤ የደንና ዱር እንስሳት ባለሙያ በመሆኔ እነዚህን ሳይንሳዊ ሁኔታዎች ብዙ ምርምሮች አድርጌባቸዋለሁ፡፡ በበግ የምሰራውን የአየር ምቾት ምርምር እንደየፆታው ወደ  አትሌቶች እያወራረስኩ እየተረጐምኩ ሲሆን  መረጃውን በመቀመርም ምርምሩን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ በመጽሐፍ ደረጃ በብዙ መልኩ ለማስረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ግን ሌላ መጨመር ይቻላል፡፡ የቆላም ሆነ የደጋ ወንድ አጋዘኖች በተፈጥሮ የሚያበቁሏቸው ቀንዶች  ቅዝቃዜ በመሳብ እንዲያግዛቸው ነው፡፡ በአንፃሩ ሴትዋን አጋዘን በተፈጥሮ ቀንድ የነሳት ደግሞ እንዳይቀዝዛት ነው፡፡ በሌላ በኩል ጥቁር ቀለም ሙቀት ይስባል የሚለውን መመልከት ይቻላል፡፡ የደጋ ከብት ጥቁር ሲሆን፤ የቆላ ግን ነጭ ነው፡፡ ይህን በሰው ልጅ ልንተረጉመው እንችላለን፡፡ በአለባበስ ደረጃም በሁለቱ ፆታዎች ሊኖር የሚያስፈልገውን ምቹነት በቀለማት ምርጫ ብቻ ሳይሆን በአለባበስ ፋሽን መወሰንም ይቻላል፡፡  በሙቀት ቦታ ወንድ ተነፋነፍ ወይም ሽርጥ ቢለብስ በተቃራኒው ደግሞ ሴት አጣብቂኝ ሱሬ መልበሷ ይበጃታል፡፡ የአለባበስ ሁኔታዎቹ አየሩን እንዲላመዱ እና እንዲቋቋሙ ያደርጋል፡፡  የሙቀት ወቅት አለባበስ ሳይንሳዊውን አቅጣጫ ከስነ-ተፈጥሮ የምቾት መጠበቅ ባህል ጋር አዛምዶ መስራቱን ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ በፆታ ልዩነት ፤ በተፈጥሮ ባህርይ፤ ከአለባበስ እና ቀለማት አንፃር በሚፈጠሩ ሁኔታዎች አትሌቲክሱን በምርምሮች እየደገፉ መስራት ያስፈልጋል ፡፡ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን በስፋት የምርምር ስራዎች ለመስራት  የሰጠኋቸው አጫጭር ምሳሌዎች መነቃቃት እንዲፈጥሩ ያህል ነው፡፡
የፆታ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ተክለሰውነትም በአትሌቲክስ ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ በምርምሮችዎ ይህን ጉዳይስ እንዴት አገናዝበውታል፡፡ በሰውነት መርዘምና ማጠር ፤ መክበድና መቅለል የውጤት ልዩነት ይፈጠራል?
የወንድና የሴት ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ስለቁመት ወሳኝነት በምሳሌ ረጅም አትሌት ልንወሰድ እንችላለን፡፡ በውድድር ላይ  ሙቀት ሲሆንና ሲዘቀዝቅ አትሌቱ ፋይዳና መሰናክል ይገጥመዋል፡፡ በሙቀት ከሁሉም ረዘም ብሎ ስለሚታይ በቂ ንፋስ እያገኘ ፋይዳ ይሆንለታል፡፡  የአየር ሁኔታ ብርዳማ ከሆነ ደግሞ  በቁመቱ መርዘም የበሳ ብርድማ ንፋስ አብዝቶ ስለሚያገኘው ተጎጂ ይሆናል፡፡
መክበድ መቅለልን የማየው ያው ከከናፊ ወፎች ጋርም ተዛምዶ ስላለው ነው፡፡ አውሮፕላንም እንደወፎቹ ሁሉ ቀላል ነው፡፡ በሩጫ የሚታወቁት አዳኝ እንስሳት ለምሳሌ ነብር እንደተነሳ 80 ኪ.ሜ. ፍጥነት ላይ የሚደርሰው ክብደቱ ቀላል በመሆኑ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በክብደት ጉዳይ ላይ ከአንድ ታዋቂ አሰልጣኝ ጋር ብዙ ተከራክረናል፡፡ አሰልጣኙ አትሌቶች ውጤታማ እንዲሆኑ አስከመጨረሻው መክሰትና መቅለል አለባቸው ነበር ያሉኝ፡፡ ከምሩጽ ጋር የሮጠውን ሙሃመድ ከዲርን እንደምሳሌ በማንሳት ነበር፡፡ ቅለትም ሆነ ክብደት የራሱ የታችና የላይ ክፍል አለው፡፡ በአሃዝ ተንትኖ ለማስቀመጥ የምርምር ውጤት ያስፈልጋል፡፤ እንደ ሰው ባህሪይ የሚመገበው ምግብና የብረት ክምምችትም ይወሰናል፡፡ አንበሳ ከባድ ሆኖም ፈጣን ሯጭም ነው፡፡  አንበሳና ነብር ደም ጠጥተው ስጋ በል ናቸው፡፡ የሚወዱት ስጋና ደም ደግሞ የአዋልዲጌሳ /መቃብር ቆፋሪ/ ምስጥን ነው፡፡ ምስጥ የክብደትዋን 10 እጅ መሸከም የምትችለው የበዛ የብረት ክምችት ስላላት ነው፡፡  በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ብረት(ፊርቲን) መርዛማ ያልሆነውና የሚሙዋማው ማለት ነው፤  በቀይ ደም ሴል ሄዶ ከሳንባ የሚወሰድ ኦክስጅን በማብዛት ትንፋሽ እንዳያጥረን ያረጋል፡፡ በመሆኑ በዚህ ዓይነት ተፈጥሮ የታደሉ ትንፋሽ ከመቁረጥ ተፋላሚያቸውን ትንፋሸ በማስቆረጥ የውጤት ፋይዳቸውን ይጨምራሉ፡፡
….. ይቀጥላል

Read 4138 times